>

"ኮማንድ ፖስቱ ከታወጀ ጀምሮ 12 ሰዎች ተለይተን የግድያ ዛቻ እየተሰነዘረብን ነው!" (ጌታቸው ሽፈራው)

በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች 
ጌታቸው ሽፈራው
~”ይህ መንግስት 9 ሰው ገድሎና ከ10 በላይ ሰዎችን አቁስሎ በስህተት ነው ብሎ ይቅርታ የሚጠይቅ መንግስት ነው። ብዙ ህዝብ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲፈናቀሉ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያላወጀ መንግስት ነው።” 3ኛ ተከሳሽ አጥናፉ አበራ

~”ኮማንድ ፖስቱ ከታወጀ ጀምሮ 12 ሰዎች ተለይተን እንደምንገደል እነ ኦፊሰር ግርማ በመንገር እያስፈራሩን ነው።” 30ኛ ተከሳሽ አብዱልጋፋር አባራያ

~ “በኦፊሰር ግርማና በኦፊሰር ግዑሽ ተመሳሳይ ዛቻ እየተፈፀመብን ነው። እነዚህ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት በግቢው ውስጥ ሬሳ ሲቀበር ዋና ተዋናይ የነበሩ በመሆናቸው ይህ ሚስጥር እንዳይወጣ ለማድረግ ነው። የኔን መኖር የሚወስነው መድሀንያለም ነው” 36ኛ ተከሳሽ ካሳ መሃመድ

በቅሊንጦ ቃጠሎ የተጠረጠሩና በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠኝ የክስ መዝገብ የተከሰሱ 38 ተከሳሾች የፍርድ ቤት ውሎ

(ቴዎድሮስ አስፋው)

ዛሬ መጋቢት 3 ቀን 2010ዓ.ም የ38ቱ የክስ ጉዳይ ለዐቃቤ ህግ የምስክርና የማስረጃ ብይን ለመስጠት በተቀጠረው መሰረት ተከሳሾቹ የቀረቡ ሲሆን ችሎቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ የፍርድ ቤቱ ስርዐት አስከባሪ “የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ስራችንን እንዳንሰራ ቤተሰብ አይገባም እያሉ እንቅፋት ፈጥረውብናል” የሚል አቤቱታ አቅርበዋል በችሎቱ የተሰየሙት የመሀል ዳኛም የጉዳዩን በጽ/ቤት እንደሚመለከቱት በመግለፅ ችሎቱን ተከሳሾቹ መገኘታቸውን በስም ጥሪ በማረጋገጥ ጀምረዋል።
———–
ሁሉም ተከሳሾችና የተከሳሾች ጠበቆችና ዐቃቤ ህግ የተገኙ ሲሆን የመሀል ዳኛው ይህንን ካረጋገጡ በኋላ “ችሎቱ ባለው የስራ ብዛትና መዝገቡ ሰፊ በመሆኑ እንዲሁም ከመሀላችን አንድ ዳኛ በስልጠና ምክንያት ከሳምንት በላይ ያልነበሩ በመሆኑ አላየነውም። ስለዚህ አንድ የመጨረሻ ቀጠሮ ለመስጠት ወስነናል”። ካሉ በኋላ ጠበቆችና ተከሳሾች ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
———
በዚህም መሰረት ከተከሳሽ ጠብቆች አቶ ወንድሙ “26ኛ ተከሳሽ አቶ ቶሎሳ በህመም ላይ ሆነው በቃሊቲ ያሉ በመሆኑና ማስታገሻ ከመስጠት ውጭ በቂ ህክምና እያገኙ ባለመሆኑና ሌሎች ተከሳሾች ያሉበት ሁኔታ ስለሚታወቅ አጭር ቀጠሮ ቢሰጥ” እንዲሁም የ13ኛ ተከሳሽ የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ጠበቃ “የተከሳሽ ቤተሰቦች ከውጭ ለዚሁ ጉዳይ ስለሚመጡ የሳምንት ቀጠሮ ቢሰጥ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
———–
ከተከሳሾችም 3ኛ ተከሳሽ አሸናፊ አካሉ “አምስት አመት ታስሬያለው አሁንም በአንድ ፍራሽ ላይ ነው የምንተኛው በስቃይ ላይ ነንና ቀጠሮ መስጠቱ ተገቢ አይደለም” ብሏል።

በተጨማሪም” የሰብዐዊ መብት ኮሚሽን የደረሰብንን ስቃይና ቶርች ገልፆ ሪፖርት አድርጓል። ፍርድ ቤቱ ይህንን ጉዳይ ለምን ዝም ይላል?” ሲል ጨምሮ ሀሳቡን አቅርቧል።

30ኛ ተከሳሽ አብዱጋፋር አባራያ “ተከሰን እንደመጣን ለህይወታችን ዋስትና እንደሌለን ገልፀን ነበር። አሁንም ቢሆን ለህይወታችን ዋስትና የለንም። በተለይ ኮማንድ ፖስቱ ከታወጀ ጀምሮ 12 ሰዎች ተለይተን እንደምንገደል እነ ኦፊሰር ግርማ በመንገር እያስፈራሩን ነው። ለፍርድ ቤቱ ክሳችንን በሚመለከት አስተያየት የፃፍን ቢሆንም ማህተም አንመታም ብለውን ማውጣት አልቻልንም። የተለየ ክትትል ይደረግብናል። ይህ ሁሉ ሰቃይ የሚደርስብን ኦሮሞ ስለሆንን ብቻ ነው። የፈለገው ነገር ቢደርስብንም ይቺ አገር አገራችን ናትና የትም አንሄድም” ብሏል።

36ኛ ተከሳሽ ካሳ መሀመድ “ከዚህ በፊት ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰብን ገልፀን ነበር። አሁንም በኦፊሰር ግርማና በኦፊሰር ግዑሽ ተመሳሳይ ዛቻ እየተፈፀመብን ነው። እነዚህ ሰዎች ይህንን የሚያደርጉት በግቢው ውስጥ ሬሳ ሲቀበር ዋና ተዋናይ የነበሩ በመሆናቸው ይህ ሚስጥር እንዳይወጣ ለማድረግ ነው። የኔን መኖር የሚወስነው መድሀንያለም ነው። ሁላችንም የተከሰስነው ዘራችንና እምነታችን እየታየ ነው። የሌለብንን ብሔርተኝነት እየፈጠሩብን ነው ብሏል።

37ኛ ተከሳሽ ፍፁም ቸርነት ለረዥም ግዜ የታሰርን በመሆኑ ቀጠሮው ከአስራ አምስት ቀን ባይበልጥ ብሏል። 3ኛ ተከሳሽ አጥናፉ አበራ “ይህ መንግስት 9 ሰው ገድሎና ከ10 በላይ ሰዎችን አቁስሎ በስህተት ነው ብሎ ይቅርታ የሚጠይቅ መንግስት ነው። ብዙ ህዝብ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲፈናቀሉ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያላወጀ መንግስት ነው። እኔ ህወሃት/ ኢህአዴግን ባለመደገፌ ነው በሽብር የተከሰስኩት። አሁንም ከፍተኛ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰብኝ ነው። ወታደር ነበርኩ። ህግን ስለማከብር እንጂ አራቱን ብቻዬን አቆማቸዋለሁ። በብሔር እየተደራጁ የሚያደርጉብን ነገር ወደ ሌላ ጫፍ እየገፋን ነው። እኔ ሞትን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት አልመጣም። ፍርዴን እስር ቤት ላኩልኝ” ብሏል።
———-
አስተያየቶቹን ከሰሙ በኋላ የመሀል ዳኛው “ከተነሱት ውስጥ ከክሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ይመዘገባሉ። ሌሎቹን እንኳን መልስ መስጠት አይደለም እንዲደመጡም መፍቀድ አልነበረብንም። ለሌሎች ልምታነሷቸው ነገሮች መልስ እየሰጠን ነው። ለምሳሌ የሰብዐዊ መብት ሪፖርቱ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተደረገ ነው። ነገር ግን ችግሮቹ አንዴ ተፈተው ይቆማሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ከጠበቆቻቹ ጋር በመነጋገር መልስ መስጠት ተገቢ ስለሆነ ከጠበቆቻችሁ ጋር ተነጋገሩና በፅሁፍ አቅርቡልን። ስለዚህ መዝገቡን በአግባቡ መርምረን ተገቢውን ውሳኔ ለመስጠት ከመግባታችን በፊት የወሰነው ቀጠሮ ስላለ ለሚያዚያ 16 ለመጨረሻ ግዜ ተቀጥሯልዐ ብለዋል።
——-

ቴዎድሮስ አስፋው አለም በቦታው ተገኝቶ እንዳጠናቀረው!

Filed in: Amharic