
በዚያ ላይ “ሙስና የልማት ቅመም ነው” እሚሉ አስተሳሰቦች አሉ። ሙስና ጉዳይ አቀላጥፎ በቢሮክራሲ የታነቀ ሥራን ያቀለጣፋል።ጨረታን ያጣድፋል። የባንክን ካዝና ነድሎ ብሪቱን ያጎርፋል። ዋናው ሙስናን ልማታዊ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ኮሚሽን የለመዱ ጉቦን የፈቀዱ ሁሌም ፕሮጀክት እንዳቀዱ ይኖራሉ። ባለሥልጣናት አዲስ ፕሮጀክት ነፍሳቸው ነው። ያሰራቸው ይማራቸውና አል አሙዲ ራሳቸው በየቀኑ አዳዲስ የልማት መርሃ ግብር ነበራችው። ምክንያቱም ገንዘብ ይበደሩበታል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ነጋዴ ድርጅቶችም አሉ። ሰው በበሽታ ሊያልቅ ነው ፣ ውሃ ጥምም ሊገድለው ነው ፣ድንቁርናማ ለጉድ ነው መንገድም የለውም… እያሉ መአቱን አውርተው በጀት ያገኛሉ። መንግሥታትም ልማት አፋጠንን ኢኮኖሚውን አንቀሳቀስን እያሉ ፖለቲካቸውንና ኪሳቸውን ይሞላሉ። አበዳሪ ባንኮችም “እባካችሁ ፕሮጀከት የላችሁም?” እያሉ ይማጸናሉ። ከባለሥልጣናቱ የተዛመዱ ወይም በጎሳ የተጋመዱት ቤተሰቦች ደሞ ፕሮጀክት እያነፈነፉ ጨረታውን እያሸነፉ እየበሉ እያካፈሉ የልማት ወሬን ያዳምቃሉ። ገና ከበረሃ ጀምሮ ጠመንጃቸውን በንግድ አቀባብለው ጥይትና ገንዘብ እየተኮሱ የመጡ ድርጅቶችም አገር ወረው እንደበሉ ወሮ በሎች፣ ኤፈርትና ሜጋ ምናምን እያሉ ሜጋ ሜጋ ፕሮጀክትና ቢዝነሶችን ተቆጣጥረውታል። እና እነሱም አገር ያለማሉ። የአምስት ዓመት የዕድገት ልማትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንዲሁ በብላሽ ለጽድቅ አልታቀደም። ቢሆንማ ኖሮ ባቡር ጣቢያ ተሠርቶ ማቋራጫ መንገድ እንዴት ይረሳል። ቢሆንማ እዚህም እዚያም ከሞላው የግድብ ጋጋታና ጫጫታ የአንዲት አምፑል መብራት ማመንጨት እንዴት ያቅታል? መንገዶች ተሰርተው ለምን ይፈራርሳሉ? ስኳር ፋብሪካዎች ተከፍተው ስኳር ለምን ይጠፋል? ሲምንቶ ፋብሪካ ተቋቁሞ ያውም በአፍሪካ ትልቁ እየተባለ ሲምንቶን ሁላ ምን በልቶታል? ያ ሁሉ የዩኒቨርስቲ ሕንጻ ተገንብቶና ተከፍቶ እንደ ፓርላማው ሰውዬ አራቱን መደቦች መደመር መቀነስ ማባዛትና ማካፈል እሚያውቅ ተማሪ ማምረት እንደምን ያቅታል? የአገራችን አንድዬው የልማት ኢንቨርስተር በሰው አገር ሙስና ተብለው ስለምን ታሰሩ? መንግሥታችንስ ለዓመታት ታጥሮ የተቀመጠ ፣ ያን ሁሉ መሬታቸውን ለምን መልሶ ተረከበው? ጀኔራሎችን በሀብት ያንበሸበሹት ግዙፎቹ የሜይ ቴክ ፕሮጀክቶች ምነው እዚያም እዚያም እዳ ገብተው መነቃነቅ አቃታቸው? ምክንያቱም ፕሮጀከት ይወለዳል እንጂ እሚያሳድገው የለም። በአገራችን ፕሮጀከቶች ተወልደው ከመንገድ እንደሚጣሉ የጎዳና ተዳዳሪ ናቸው።
ሙስና ጥሩ ነው እያልኩ ባይሆንም እንደየደረጃውና ዓይነቱ የትም አገር ያለ ነው። ጥሩ ጥሩ ሌብነትና ዘራፊነት ያማሩ የቁልምጫ ስሞች እየተሰጠው ሎቢስት ኮንስልታንት አድቫይዘሪ…እየተባለ በተቋም ደረጃ ሳይቀር ይደራጃል። ታዲያ ይለማል የተባለው ነገር የተበላው ተበልቶለት በትክክል ይለማል። የአገራችን የልማታዊ ዴሞክራሲ ዓይነቱ ሙስና ግን የተለየ ነው። እየበሉ እየጠጡ ዝም የወያኔ ወንድም ….ዓይነት ነው። እና እነዚህ ሰዎች እኮ ስለ እውነት አገሪቱን አልምተዋል ሲባል…የባከነውን ሀብት፣ የቆለሉትን እዳ፣ እንደ አርከበ እቁባይ እዚህም እዚያም የጣዱትን ድስት ሁሉ ማሰብ ተገቢ ነው። እነ አቶ በረከት ወጥተው ልማት ልማት ስላሉ ብቻ ልማቱ በረከት አለው ማለት አይደለም። ይህን ለማለት ጊዜው ገና ነው።