መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ:_ ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ አብርሃ ነዎት አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አዎ!
መቶ አለቃ:_ ተክላይ ኃይሉ፣ ጉኡሽ፣ …… ሁሉም የቂሊንጦ ኃላፊዎች ናቸው አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በ2008 የዞን 1 ኃላፊ ዘርኡ ነበር?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_የዞን 2 ደግሞ ኃይላይ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ የዞን 3 ኃላፊም ልዕላይ ነበር?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በሙሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች ናቸው አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
ዐቃቤ ሕግ:_ በክሱ ላይ ያልተጠቀሰና ከክሱ ጋር ግንኙነት የሌለው ጥያቄ በመሆኑ እንቃወማለን!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ክሳችን ላይ ትግርኛ ተናጋሪዎችን ልንገድል እንደነበር ተጠቅሷል። ምስክሩም መልስ ሰጥተውበታል። ያሳደገን ማህበረሰብና ባህል ይህን አይፈቅድም። ከ1ኛ እስከ 20ኛ የመሰከሩት ምስክሮች በተመሳሳይ ምስክርነት ሰጥተዋል። የፖለቲካ ይዘት ስላለው መስተካከል ስላለበት ነው። ለምሳሌ 31ኛ ተከሳሽ ክስ፣ ሁለተኛ ገፅ ላይ የእነተክላይ፣ ገብረማርያም፣ ጠሃ ስብሃቱ ሊገደሉ ነበር ተብሎ ስማቸው ተዘርዝሯል።
ፍርድ ቤቱ:_ከስም ዝርዝር ባለፈ ይህኛው ዘር ይህኛው ዘር ተብሎ አልተጠቀሰም። ሌላ ጥያቄ ይጠይቁ።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ነሃሴ 28 ጥይት እንዲተኮስ ትዕዛዝ የሰጠው ማን ነው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ቅድም ተናግሬያለሁ!
ፍርድቤቱ:_ ወደ ሌላ ጥያቄ እለፍ!
መቶ አለቃ:_ ኃላፊ ናቸው። እሳቸው ትዕዛዝ መስጠት አለመስጠታቸውን ለማረጋገጥ ነው።
ፍርደ ቤቱ:_ እርስዎ ትዕዛዝ ሰጥተዋል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ አልሰጠሁም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከግቢ ሊወጡ ሲሉ የተመቱ እስረኞች ስንት ናቸው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_2 ናቸው!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ 2 ብቻ ናቸው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ መቶ አለቃ ዳንኤል፣ ተመሰገን፣ ወዲ፣ ኩልፊ…… የተባሉ እስረኞች አልተመቱም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልተመቱም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በህይወት ያሉ በጥይት የተመቱ እስረኞች የሉም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ይኖራሉ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ አሉ ወይም የሉም ብለው እንዲመልሱልኝነው። እርግጠኛ ምስክርነት እንዲሰጡ እፈልጋሉ። እርግጠኛ ሆነው ካልሰጡ እንዲመዘገብ አልፈልግም።
ፍርድቤቱ:_ የተመቱ ሰዎች አሉ ወይስ የሉም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አሉ! ይኖራሉ!
ፍርድቤቱ:_ አሉ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ግቢ ውስጥ ያስተባብር ነበር ብለው መስክረዋል!
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ማስተባበር በምን ይገለፃል? በአካል ነው በወረቀት?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_በአካልም በወረቀትም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ በአካል አይተውኛል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላየሁም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ሰምተው ነው?
ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_………
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ:_ከዞን 2 መቼ ወጣሁ? ቀንና ወሩ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላስታውሰውም።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ጥር ወር ሊሆን ይችላል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላስታውስም።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከዞን 2 ወደ ቅጣት ቤት ስንሄድ የተሰጠን ምክንያት ነበር?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ቅጣት ቤት አይደለም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ማግለያ ማለት ነው?
ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_አንድ እስረኛ ግቢ ውስጥ ጥፋት ካጠፋ ይቀጣል። እኔ ቅጣት አልተቀጣሁም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ቅጣት አልቀጣንም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_በዚህ ጉዳይ፣ ጨለማ ቤት ስለገባን፣ ከቤተሰብ ጋር እንዳንገናኝ ተከልክለን፣ እኔ 4ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታ አቅርቤ እራስዎ መልስ አልሰጡበትም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ጨለማቤት የለም ብየ መልስ ሰጥቻለሁ። አሁንም የለም።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ያለንበት ቤት ግድግዳውም ጣራውም ሲምንቶ ነው አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ቤቱ አናት ላይ የጥበቃ ማማ አለ አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_በር ላይም ጥበቃ አለ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_የትም አለ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ታዲያ እኔ ከሌላ እስረኛ ጋር መገናኘት እችላለሁ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አትችልም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ሆስፒታል ሄጄ አውቃለሁ? (ምስክሩ እስረኞች ሆስፒታል ሲሄዱ ይገናኛሉ ብለው ስለመሰከሩ ነው)
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ:_እኔ ሆስፒታል ሄጄ አውቃለሁ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ፍርድቤት ስትሄዱ ነው የምትገናኙት!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_እኔ ሆስፒታልሄጀ አውቃለሁ?
ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:__ማንም ሰው ሲታመም ሆስፒታል ይሄዳል። በእርግጠኝነት ግን ፍርድ ቤት ሲሄዱ ይገናኛሉ።
ፍርድ ቤቱ:_ ተከሳሽ የተለያየ ጥያቄ መጠየቅ መብታቸው ነው። ስለሆስፒታል የተጠየቁትን ይመልሱ!
መቶ አለቃ:_ ፍርድ ቤት ከሰው ጋር እንዳልገናኝ እያደረጉ ራስዎ ሲያቀርቡኝ አልነበረም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አንድ ቀን መጥተሃል።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_አንድ መኪና መድበው፣ ከጎኔ የደህንነት ሰራተኛ መድበው ከአባሪዎቼ ጋር እንዳልገናኝ አድርገው ሲያመላልሱኝ ነበር!
ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_ነበር!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ወደ ፍርድቤት ስመላለስ የነበረው በከፍተኛ ጥበቃነው። እስር ቤቱ ሲቃጠል ማግለያ ክፍል ነበርኩ። ሰው ገድሏል ብለው የመሰከሩብኝ በምን መልኩ ነው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_መጀመርያ ታደራጅ ነበር።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ነሃሴ 28/2008 ዓም ዞን2 እና ዞን3 ሲቃጠል እኛ ያለንበት ክፍል ተከፍቶ፣መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ እና በቀለ ገርባ… እዛ ቤት ውስጥ የነበሩ እስረኞች በጥይት ይመቱ ብለው ትዕዛዝ አልሰጡም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልሰጠሁም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ቃጠሎው ከበረደ በኋላ ቤቱ ይከፈት ብለዋል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ ይከፈትላቸው ብያለሁ።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_በቃጠሎው ወቅት፣ እየተቃጠለ፣ ጭስ ታፍኖ በነበረበት ወቅት ቃጠሎ ይደርስባቸዋል ሳይሉ ቃጠሎው ከበረደ በኋላ ይከፈት ያሉት ለእኛ ደህንነት ብለው ነው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_:_መጀመርያ ይከፈት ሲባል እምብይ ስላላችሁ ነው።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ መጀመርያ ቃጠሎ ወቅት ሳትከፍቱልን ከበረደ በኋላ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_መጀመርያ እምብይ እንዳላችሁ አባሎች ነግረውኛል።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_እርስዎ እኔና በቀለ ገርባ እንድንገደል ትዕዛዝ ሰጥተው አባሎች (ፖሊሶች) አንከፍትም! አንገድልም አላሉዎትም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላዘዝኩም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_እስረኞች እንዲያመልጡ እቅድ እንደነበረኝ መስክረዋል። የእኔ እቅድ ማምለጥ ከነበር እንኳን ልክፈትልህ ተብዬ፣ ከፍቼ ለምን አልወጣሁም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ እሱን እርስዎ ነው የሚያውቁት!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_እሳት አደጋ ወደ ዞን 2 ገብቶ እሳቱን ለማጥፋት ሲጥር እርስዎ እሳቱን እንዳያጠፋ አስቁመውታል አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላስቆምኩም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ዞን 3 የተቃጠለው እስረኞች ከወጡ በኋላነው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ዞን2 በጥይት የተመቱትን ወንድሞቻችን ዞን 3 ወስዳችሁ አስከሬናቸውን በእሳት አላቃጠላችሁም?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላቃጠልኩም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_እሳቱ እስከ ስንት ሰዓት ቆየ?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አላውቅም።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ክቡር ፍርድ ቤት እንደ አባል፣ እንደ አመራር በወቅቱ ነበርኩ ስላሉ ሰዓቱን እንዲናገሩ ጣልቃ መግባት አለበት!
ፍርድ ቤቱ:_ ስንት ሰዓት ነበር? ይናገሩ!
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ከሰዓት
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከቃጠሎው ቀን በኋላ ቤቱ ሲፀዳ አስከሬን ተገኝቷል አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልተገኘም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_በቃጠሎው ቀን ነሃሴ 28 የሟቾች አስከሬን ስንት ሰዓት ተነሳ?
ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_እኔ ውጭ ነበርኩ። አላየሁም።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_እሳት ቃጠሎው ከቆመ በኋላ ነው የሞተውን ሰው ቁጥር ያወቃችሁት?
ዋና ኦፊሰርገ/ማርያም:_አዎ!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ከቀኑ 7 ሰዓት፣ ገና እሳት ቃጠሎው ሳይበርድ መንግስት በሚቆጣጠረው ኢቢሲ 23 ሰው ሞተ ተብሎ ተዘግቧል። የሀሰት መረጃ ሰጥተዋል ማለት ነው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_የሀሰት ማስረጃ አልተናገርኩም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ ታዲያ ከየት አምጥተው ዘገቡ? እሳቱ አልጠፋም። ለኢትዮጵያ ህዝብ የሀሰት ማስረጃ ሰጥተዋል ማለት ነው?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልሰጠሁም!
(መቃወሚያ ቀርቧል)
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ አንድ የዜና ወኪል ወይ ራሱ ተገኝቶ አሊያም ከመስርያ ቤቱ ጠይቆ ነው ዜና ሊሰራ የሚችለው። ምስክሩ ደግሞ በማረሚያ ቤቱ በኃላፊነት 2ኛ ሰው ናቸው።
ፍርድቤቱ:_ እሳቸው መረጃ ላይሰጡ ይችላሉ። በተለያየ መንገድ ልትጠይቅ ትችላለህ።
መቶ አለቃ:_ የሞቱ ወንድሞቻችንን አስከሬን ለቤተሰብ አስረክባችኋል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ለፖሊስ ሰጥተን። ፖሊስ ለቤተሰብ ሰጥቷል።
መቶ አለቃ ማስረሻ:_የተገደሉትን እስረኞች ሰብስባችሁ ከቀበራችሁ በኋላ፣ ላዩ ላይ አሁን ዞን 5 የሚባለውን እስር ቤት ሰርታችሁበታል አይደል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_አልሰበሰብንም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ግድግዳው በጥይት ተመትቷል ወይ ተብለው ሲጠየቁ ተቃጥሏል ብለዋል። ግድግዳው ሙሉ በሙሉ ተቃጥሏል?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_በጥይት መመታቱን አላየሁም!
መቶ አለቃ ማስረሻ:_ነሃሴ 28/2008 ዓም በቂሊንጦ ቃጠሎ ለጠፋው የሰው ህይወት እና ለወደመው ንብረት ተጠያቂ አይደለሁም ነው የሚሉት?
ዋና ኦፊሰር ገ/ማርያም:_ተጠያቂ አይደለሁም!