>
5:13 pm - Wednesday April 18, 0323

መሪው ተገኝቷል! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

በድሮ ጊዜ ነው በዚያን ዘመን ወቅቱ ይፈቅደው በነበረ የአሥተዳደር ሥርዓት ትመራ በነበረ አንዲት ሀገር የሀገሩንና የሕዝቡን ህልውና ደኅንነትና ጥቅም ከራሱ በላይ የሚያይ፣ የሚያሳስበው፣ የሚያስጨንቀው አንድ ብልህ ንጉሥ ነበረ፡፡ በሱ ዘመን ሀገሪቱን ከቀደምቶቹ እጅግ በላቀ መልኩ እድገት ብልጽግና እንድታስመዘግብ አስችሏታል፣ ዙሪያውን የከበቡትን የሸፍጠኛ የሴረኛ ጠላት መንግሥታትን ሸፍጥና ሴራ እንዲሉም ጥቃትን በላቀና በረቀቀ የአጸፋ ምላሹ እያመከነ አንበርክኮ ሀገሩንና ሕዝቡን እነኝህ ጠላቶቹ ሊያደርሱበት ከሚችሉት መናቆር አደጋ ችግርና ፈተና በአስተማማኝ ሁኔታ ታድጓል፣ ሕዝቡን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በአንድ ሐሳብ አስማምቶና አግባብቶ ለፈለገው ዓላማ ሁሉ በአንድነት ማሰለፍ ችሏል ባጠቃላይ በሁሉም ረገድ ስኬታማ የነበረ ንጉሥ ነበረ፡፡

ይሄ ንጉሥ እያረጀ በሔደ ጊዜ የወራሴ መንግሥቱ ጉዳይ እጅግ ያሳስበው ነበር፡፡ እርግጥ ሁሉንም ልጆቹን የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጎ ነው ያሳደጋቸው፡፡ ይሁንና ብቃት ችሎታቸው የአንደኛው ከሌላኛው መለያየቱ አይቀርምና ንጉሡ እሱ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ሲሆን ሲሆን በበለጠ መልኩ ያም ባይሆን እንኳ ካለው ባላነሰ ደረጃ እንዲቀጥል ማድረግ የሚችለውን ልጅ ከልጆቹ መሀል ማግኘት አጥብቆ ይፈልጋል ይመኛል፡፡ ይሄ ለሥልጣን ተገቢው ልጅ ካልተገኘ የተገኘው ስኬት በሙሉ ገደል እንደሚገባ፣ በዙሪያቸው ያሉ ጠላቶቻቸው ቀረጣጥፈው እንደሚበሏቸው ያውቃልና ከልጆቹ መሀል ይተካኛል ብሎ የሚያስበውን ባያገኝ ከልጆቹ ውጭ ከሕዝቡ ፈልጎ እስከማንገሥ ድረስ ለመሔድ እራሱን አዘጋጅቷል፡፡ ከተገኘ ግን ቅድሚያ ፍላጎቱ ከልጆቹ እሱን ሊተካ የሚችል ላቅ ያለ ችሎታና ብቃት ያለውን ልጁን ማንገሥ ነው እንጅ ልማዳዊ በሆነው መንገድ ሔዶ የመጀመሪያ ልጁን ማንገሥ አይደለም፡፡

ስለሆነም አስቀድሞ የልጆቹን ብቃት ለመፈተን ከ12 ልጆቹ መሀል ብልህ የሆነ፣ ሀገርን በብቃትና በጽናት የሚሸከም ትከሻ ያለው፣ የችግር አፈታት ጥበብ የተካነ፣ ኃላፊነት ለመውሰድ ደፋርና ቆራጥ የሆነ፣ የሞራል (የቅስም) ልዕልና ያለው፣ የመሪ ሰብእና የተላበሰ ካለ እሱን መርጦ ለማንገሥ ከሌለ የልጆቹን ጉዳይ ዘግቶ ይሄንን ተፈላጊ ሰው ከሕዝብ ፈልጎ ለማግኘት በማሰብ አንድ ጥያቄ አዘጋጅቶ ሊቃውንቱን 12ቱንም ልጆቹን ለየብቻቸው እንዲጠይቋቸውና መልሶቻቸውን ከነምክንያቱ እንዲያቀርቡ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ የሁሉም ልጆቹ መልሶች በጥቅሉ በሦስት የሚመደቡ ቢሆንም የተለያዩ ምክንያቶች በመጥቀስ ምላሽ ሰጡ፡፡

ጥያቄውን ስናየው ለብዙዎቻችን ቀላል ይመስላል፡፡ ለጥቂቶቻችን ደግሞ ከባድ ነው፡፡ ለልዑላኑ የቀረበላቸው ጥያቄ የሚከተለው ነበረ፦

“አባትህ ንጉሡ፣ እናትህ እቴጌዪቱ፣ አንተና የልጆችህ እናት ሚስትህ አራታቹህ ባላቹህበት ጀልባ እንደሆናቹህ ሁላቹህንም ሊያጠፋ የሚችል ከባድና አደገኛ ማዕበል ተነሣ፡፡ አንተ ግን ግሩምና አስደናቂ የሆነ የዋና ችሎታ ስላለህ ከሦስቱ አንዳቸውን ማዳን ትችላለህ፡፡ በዚህ መሠረት ከሦስቱ ማንን ታድናለህ?” የሚል ነበር የመፈተኛ ጥያቄው፡፡

ሁሉም የየራሳቸውን ምላሽ ከነምክንያቶቻቸው አቀረቡ፡፡ ስድስቶቹ ለእናታቸው ባላቸው ተፈጥሯዊ ፍቅር የተነሣ “እናት መተኪያ የላትማ!” ከሚል ምክንያትና ከዚሁ ጋራ የሚቀራረብ ምክንያቶች በመጥቀስ መልስ ሰጡ፡፡ ንጉሡ እናቱን ወዳጅ በመሆኑና እናታቸውን እንዲወዱ አድርጎ ስላሳደጋቸው በምርጫቸው ንጉሡ ይቀየመናል ብለው አልሠጉም፡፡

አምስቶቹና ብልጦቹ ከግሞ ማለትም “ንጉሡን አድናለሁ!” በማለታቸው ንጉሡ ለንግሥና እንደሚያበቃቸው ያመኑት “አባቴ ንጉሥ ስለሆነና ዛሬ ቢያረጅም ለሀገር ብዙ የሠራ፣ በርካታ ስኬት ያስመዘገበ በመሆኑ በዚህ መልኩ በሞት መወሰድ ስለሌለበት!” የሚልና ከዚሁ ጋር የሚቀራረብ የተለያየ ምክንያት በመጥቀስ ምላሽ ሰጡና ንጉሡን ወይም አባታቸውን የእደሚያድኑ ተናገሩ፡፡

አንዱና የመጨረሻው ልጅ ብቻ ሚስቱን እንደሚያድን ተናገረ፡፡ “ለምን?” ተብሎ ለተጠየቀው ጥያቄም መልስ ሰጠ፡፡ ይሄ ልጅ የሰጠውን መልስና ምክንያት ሊቃውንቱ አልጠበቁትም ነበር፡፡ ሊቃውንቱ የሁሉንም ልጆች መልሶችና ምክንያቶች በአግባቡና በጥንቃቄ መዝግበው ለንጉሡ አቀረቡ፡፡

ንጉሡም የልጆቹን መልሶችና ምክንያቶች በጥንቃቄ ከተመለከተ በኋላ የሚፈልገውን አገኘ መሰል ደስታው ፊቱን አፈካው፡፡ ፈጣሪውን አመሰገነ፡፡ የጦር መሪዎቹን፣ ሊቃውንቱንና ሕዝቡንም ጉባኤ ጠራ፡፡ በጉባኤው ላይም እሱን የሚተካ፣ የሀገሪቱን እድገት የሚያስቀጥል፣ ሰላሟን የሚያረጋግጥ ንጉሥ ከልጆቹ መሀል ማግኘቱን አበሰረ፡፡ የጦር መሪዎቹ፣ ሊቃውንቱና ሕዝቡ በደመቀ ጭብጨባና እልልታ ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ንጉሡ ይሄንን ለመለየት ለልጆቹ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ለሕዝቡ ከገለጸ በኋላ እያንዳንዳቸው የሰጡትን ምላሽ ከነምክንያቱ እራሳቸው በየተራ መድረክ ላይ እየቆሙ ለሕዝቡ እንዲገልጹ አደረገ፡፡

ቀጠለና ልጆቸ የቀረበላቸውን ጥያቄና የሰጡትን ምላሽ አነምክንያቶቻቸው አድምጣቹሀል፡፡ ማንኛውን የመረጥኩ ይመስላቹህል? ሲል ሕዝቡን ጠየቀ፡፡ የሕዝቡ ምላሽ የተለያየ ነበረ፡፡ ብዙዎቹ እንዲያውም ልጆቹ የሰጡትን መልስና ምክንያት ግምት ውስጥ አላስገቡም፡፡ በመልኩ ከወንድሞቹ የላቀውን የመረጡ አሉ፣ በቁመናው ከወንድሞቹ ያማረውን የመረጡ አሉ፣ በወንዳወንድነቱ የወደዱትን የመረጡ አሉ፣ “ምስኪን ለሰው አዛኝ ነው!” በመባል የሚያውቁትን የመረጡ አሉ፣ በጦረኛነቱ ልቆ የሚታወቀውን የመረጡ አሉ፡፡

በሊቃውንቱ መሀከል ግን ምንም ልዩነት አልነበረም፡፡ ምርጫቸው ከአንዱ ልጅ ላይ አርፏል፡፡ ሁሉም ያለጥርጥር በአንዱ ልጅ ላይ ተስማምተዋል፡፡ የጦር መሪዎቹ ደግሞ የንጉሡ ምርጫ ከሁለቱ ልጆቹ አንዱ እንደሚሆን እርግጠኞች ነበሩ፡፡ የትኛው ሊሆን እንደሚችል ግን እርግጠኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ንጉሡ ዕድሜው 64 ዓመት ነው፡፡ በመጀመሪያ ልጁና በመጨረሻ ልጁ መሀከል የ22 ዓመት የዕድሜ ልዩነት አለ፡፡ የመጀመሪያ ልጁ 44 ዓመቱ ሲሆን የመጨረሻ ልጁ ደግሞ 22 ዓመቱ ነው፡፡

ንጉሡ ማንን እንደመረጠ ይፋ ለማድረግ ተነሣ፡፡ ማናቸውንም ቢመርጥ ልጆቹን እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ እንዲከባበሩ፣ ከሥልጣን ይልቅ ወንድማማችነቱ እንደሚበልጥ፣ ሀገር እንደምትበልጥ አሳምኖ አስተምሮ ስላሳደጋቸው የተቀሩት ቅር እንደማይሰኙና ሁሉም ተባብረው ተስማምተው ተደጋግፈው ውድ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነትና በቆራጥነት እንደሚያገለግሉ እርግጠኛ መሆኑን ገለጠ፡፡ ሕዝቡም በጭብጨባ በእልልታ ደስታውን ገለጠ፡፡

የመረጠው ማንኛውን ልጁን እንደሆነ የሚገልጥበት ሰዓት ደረሰ፡፡ እቴጌዪቱን ጨምሮ ሁሉም ማን መሆኑን ለማወቅ እጅግ ከመጓጓቱ የተነሣ በጥፍሩ ቆሟል፡፡ ንጉሡ ድምፁን ከፍ አድርጎ “መሪው ተገኝቷል!” ሲል አሰማ፡፡ ሕዝቡ ” ኋ………!” የሚል ጩኸት በማሰማት ሆታውን አቀለጠው፡፡ ንጉሡ አሁንም ደገመና “ንጉሡ ተገኝቷል!” አለ፡፡ አሁንም እንደገና ሆታው ቀለጠ፡፡ ንጉሡ ከልጆቹ መሀል የአንዱን ማለትም ሚስቱን እንደሚያድን የተናገረውን የመጨረሻ ልጁን ስም ተጣራ፡፡ ሊቃውንቱና የጦር መሪዎቹ ጭብጨባቸውን እያቀለጡት ከመቀመጫቸው ተነሡ፡፡ ሕዝቡም ሆታውን አቀለጠው፡፡ ንጉሡ ዘውዱን አወለቀና ለዚሁ ልጁ ጫነለት በትረ መንግሥቱን አስጨበጠው፣ በዙፋኑም ላይ አስቀመጠው፡፡ ከዚያች ቅጽበት በኋላ ንጉሡ ይሄ ልጅ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

ይሄ ልጅ ሚስቱን እንደሚያድን የሰጠውና አባቱን አስደስቶት ለንጉሥነት እንዲመርጠው ያደረገው ምክንያት የሚከተለው ነበረ፦

“የማድነው ሚስቴን ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይሄንን የማደርገው ግን ከወላጆቸ ይልቅ ሚስቴን ስለምወድ አይደለም፡፡ ይሄንን በሚገባ ታውቃላቹህ፡፡ ሚስቴን የምጠላት ብሆንም እንኳ የምወስደው እርምጃ ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ ይሄንን የማደርግበት ምክንያት እናቴም አባቴም ለቤተሰባቸው፣ ለሀገርና ለሕዝብ የድርሻቸውን ተወጥተው ጨርሰዋልና፣ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በሚገባ ተወጥተው ጨርሰዋልና ተራው የኔና የባለቤቴ በመሆኑ ነው፡፡ ወላጆቸ ከዚህ በኋላ የሚቀራቸው ነገር ቢኖር ወደማይቀርበት ዓለም መሔድ ነው፡፡ ይሄ ተፈጥሯዊ ጥሪ በየትኛውም ሰዓትና በየትኛውም ቦታ መከሰቱ አይቀሬ በመሆኑ ይሄ ጥሪ በዚህ አሳዛኝ አጋጣሚና ሁኔታ ጀልባ ላይ እያለን ሦስቱንም ላድን በማልችልበት ሁኔታ በመምጣቱ አዝኘ ይሄንን በእናትና አባቴ ላይ የመጣውን ተፈጥሯዊ የማይቀር የሞት ጥሪ ጨክኘ በመቀበል እናትና አባቴን ሸኝቸ ሚስቴን ከማዳን ውጭ ሌላ እርምጃ መውሰድ አይኖርብኝም፡፡ አባቴን ወይም እናቴን በማዳንና ሚስቴን ለሞት በመስጠት ሕይዎት እንድትቆም ማድረግ አይኖርብኝም፡፡ ሕይዎት መቀጠል አለባት! እናትና አባቴ የድርሻቸውን እንደተወጡ ሁሉ እኔና ባለቤቴም ወደፊት የሚጠብቀንን ኃላፊነትና ድርሻ በሚገባ መወጣት ይኖርብናልና ነው ከሚስቴ ይልቅ እናትና አባቴን የምወድና የማከብር ብሆንም እንኳ ሚስቴን የማድንበት ምክንያት!” በማለት ነበረ እጅግ እያዘነ ነገር ግን ቆፍጠን ብሎ የተናገረው፡፡

ብልሁ ንጉሥ ለተቀሩት ልጆቹ እንደሰጡት ምላሽና ምክንያት ይችሉታል ይወጡታል ያለውን ሥልጣንና ኃላፊነት መድቦ አስያዛቸው፡፡ ብልጥ ለመሆን ብለው ንጉሡን እናድናለን ያሉትን በንግድ ዋና ሹምነት (ሚንስትርነት) እና መሰል ዘርፍ ላይ አሰማራቸው፡፡ ለእናታቸው ባላቸው ላቅ ያለ ፍቅር ምክንያት እናታቸውን ለመረጡት በማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዋና ሹምነት (ሚንስትርነት) እና መሰል ዘርፎች ላይ ሾማቸው፡፡ ንጉሡ እንዲህ በማድረጉም ምክንያት በተመኘው ደረጃ የሀገሪቱና የሕዝቧ ሰላም ብልጽግናና አንድነት ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል ቻለ ይባላል፡፡

እርግጠኛ ነኝ አንዳንዶቻቹህ ይሄንን ወግ ስታነቡ ወያኔ ጉልቻ እየለዋወጠ ሕዝብን ደልሎ ዕድሜውን ለማራዘም በመሞከር ከሚያደርገው ሰሞንኛ ጥረቱ ጋር በማያያዝ ከወያኔ/ኢሕአዴግ ስብስብ ውስጥ ነፍስ ያለውና ከጠባብ ዘውገኝነት ወጥቶ ኢትዮጵያን በማስቀደም የማሥተዳደር ብቃት፣ ችሎታ፣ አቅም፣ አቅል፣ ትከሻ፣ ጥንካሬ፣ ጽናት… ያለው ሰው ይገኝ ይመስል “ማን ይሆን የተገኘው መሪያችን?” ሳትሉ አትቀሩም፡፡ ተስፋ ቁረጡ ከወያኔ/ኢሕአዴግ መንጋ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያስቀድም ሰው ማግኘት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ርዕዮተዓለማቸው ጎሳ ጎሳቸውን እንዲያስቀድሙ እንጅ ኢትዮጵያን እንዲያስቀድሙ አይፈቅድላቸውምና ከወያኔ/ኢሕአዴግ እንዲህ ዓይነት ሰው እናገኛለን ብላቹህ ተስፋ አታድርጉ፡፡

አንዳንዶቻቹህ ደግሞ ከፍ ብሎ የተረኩትን ወግ ካነበባቹህ በኋላ “አሁን እስኪ እራሱን ለጠላቶቻችን ቀጥሮ አንድነታችንን ባፈራረሰ፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅሞች ክፉ ለሚመኙልን ጎረቤት ሀገራትና ባዕዳን አሳልፎ በመስጠት የሀገር ክህደት በፈጸመ፣ አኩሪ ታሪካችንንና ሌሎች እሴቶቻችንን እያጠፋ ባለ ቅጥረኛና ባንዳ አገዛዝ ተጠፍንገን ተይዘን በእጅጉ ሆድበባሰን ሰዓት እንዲህ ዓይነት ወግ ማቅረብ ምን ማለት ነው?” ሳትሉ አትቀሩም፡፡ አዎ የኔም ፍላጎት ይሄንን እንድትሉ ነው፡፡

“ከዛስ?” ካላቹህ ከዚያማ ተሸጠህ ሳታልቅ፣ በገዛ ሀገርህ የባዕዳንና የቅጥረኛ ባሪያ ሆነህ እስከወዲያኛው በማይፈታ የባርነት እግር ብረት እግር ከወርች ከመታሰርህ በፊት ቶሎ መላ እንበል ነዋ! ፣ ጅማሬህን አጥብቀህ ያዝና ለፍጻሜ አብቃ ጊዜ በሰጠነው ቁጥር ለመንቀል ወደማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነውና ጊዜ አንስጥ ነዋ! ፣ ፈጽሞ በምንም ነገር አትደለል አትሸንገል ነዋ! ፣ ያለ ስርነቀል ለውጥ ሕመምህን የሚያክም ስብራትህን የሚጠግን መድኃኒትና መፍትሔ እንደሌለ አውቀህ ቁረጥ ጨክን ነዋ!!!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

Filed in: Amharic