>

ፀረ-ሰላም ኃይል ዘርማ ወይንም የጉራጌ ማህበረሰብ ሳይሆን የህወሃት መራሹ ስርዓት ነው!!! (ስዩም አርጋው)

የዘርማና የጉራጌ ማህበረሰብ እየጠየቀ ያለውን ትክክለኛ ጥያቄ ለመቀልበስ እንዲሁም ለማሰር፣ ለመደብደብና ለመግደል እንዲመቻቸው ለማስቻል ነፍሰ ገዳይ ካድሬዎችን ለመሾም የፐ/ሰርቫንት አባላት ስብሰባ ሊቀመጡ ነው። ለዚህም የተዘጋጀ መነሻ ሰነድ ከዚህ ፅሁፍ ጋር ለአባሪነት አያይዤዋለሁ።
ከሰነዱ በመነሳት የሚከተለውን ለሚመለከተው ሁሉ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፦
1. የዘርማና የጉራጌ ማህበረሰብ ጥያቄ መሰረታዊና የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ይህን ትግል ለመቀልበስ ከገዳዩ የወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ጋር ያበራችሁና እያበራችሁ ያላችሁ ከማህበረሰቡ ጉያ የወጣችሁ ካድሬዎች ልታስቡበት ይገባል። በስልጣን ላይ ያለው የወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ስርዓት ላለፉት 27 ዓመታት በማህበረሰባችን ብሎም በመላው ኢትዮጵያ አገራችንና ህዝባችን ያደረሰው አልበቃ ብሎት ወንበሩን አደላድሎ በስልጣኑ በቀጠል ተጨማሪ በደልና ግፍ እንዲፈፅም ተባባሪ መሆን ትልቅ ወንጀል ነው። እምነውኝ ለናንተም በኋላ ዋጋ ያስከፍላችኋል።
2. የዘርማና የጉራጌ ማህበረሰብ ጥያቄ ትክክለኛ ወቅታዊ በመሆናችው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከዘርማና ማህበረሰቡ ጋር ከመተባበር ይልቅ በሌላ ሃይል ተገፍተው እንደወጡ ማፈረጅ ለዘርማና ለማህበረሰቡ ያላችሁ ንቀት የሚገልፅ በመሆኑ ልታፍሩበት ይገባችኋል። ይህ የሚያመላክተው ለማህበረሰቡ ካላችሁ ንቀትና ጥላቻ በላይ እራሳችሁን ለማስተካከል ያልተዘጋጃችሁ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ የስርዓቱ ባህሪ ነው። እናንተ ደግሞ ስርዓቱ የወለዳችሁ ልጆች ናችሁ። ለዚህም ነው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የሚታገለው።
3. ፀረ-ሰላም ኃይል ዘርማ ወይንም የጉራጌ ማህበረሰብ ሳይሆን የወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ ስርዓት ነው።
4. የጉራጌ ማህበረሰብና ዘርማ በሰላማዊ መንገድ ህዝባዊ ተቃውሞ ባቀረቡበት ወቅት በስርዓቱ ጀሌዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው። እነዚህን ለህግ በማቅረብ፤ ስርዓቱ ለሟች ቤተሰቦች፣ አካል ጉዳት ለደረሰባቸውና ንብረታቸው ላጡት ካሳ መክፈል ይኖርበታል።
5. በአሁን ወቅት የዘርማ ትግል ላይቀለበስ ተቀጣጥሏል። ይህ ደግሞ በቀጣይ ትላልቅ ድሎች ይቀዳጃል፤ ለዛም ከቄሮ፣ ፋኖ፣ ነብሮ ብሎም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ተባብሮ ይሰራል። ስለዚህ ሁሉም ሰው የዘርማን ትግል ሊደግፍ ይገባል።
6. የጉራጌ ዞን ካድሬዎች እጃችሁ በደም ከማጨማለቃችሁ በፊት ልታስቡበት ይገባል። የጉራጌ ማህበረሰብና የዘርማ ጥያቄ ከሆስፒታል የዘለለ ሰፊ ጥያቄ ነው። ይህ ስርዓት ደግሞ ለመመለስ ፍቃደኛ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከባህሪውና ስርዓቱ ከተገነባበት አንፃር ሊመልሳቸው አይችልም። ስለዚህ እጃችሁ ከማህበረሰባችን አንሱ። የገዳይ ስርዓት ተባባሪ አትሁኑ።
በመጨረሻም፦ አሸባሪና ፀረ-ሰላም ሃይል ወያኔ/ህወሃት-ኢህአዴግ እንጂ ዘርማ ወይም የጉራጌ ማህበረሰብ አይደለም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
የዘርማ ትግል ይቀጥላል!
የኢትዮጵያ ትግል ይቀጥላል!
እናቸንፋለን!
Filed in: Amharic