>

ወደ ባንኮች ተመልክቱ!!! (ደረጀ ደስታ)

አሜሪካ ውስጥ ነጮቹ ጥቁሮቹን ጨቁነዋል ሲባል የጭቆናው መልኩ ብዙ ነው። አንዱ ጥቁሮቹን ማደህየት ብቻ ሳይሆን ያላቸውንም ጥሪት መዝረፍ ነበር። በዚያ በከፋው ዘመን ነጮቹ ከጥቁሮቹ መንደር ከጉራንጉሩ ሳይቀር ይገቡና ባንኮችን ይከፍቱላቸዋል። ጥቁሮቹ ገንዘቦቻቸውን ለመቆጠብ ያስቀምጣሉ። ካስቀመጡት ገንዘብ ግን ለንግድ፣ለቤት መስሪያም ሆነ መኪና መግዣ ብድሩን የሚያገኙት ሌላ አካባቢ እሚኖሩ ነጮች ነበሩ። ቅርንጫፍ ባንኮቹ ከተከፈቱበት መንደር እምትቀር ገንዘብ የለችም። በዚያ ላይ የትም ያሉ ባንኮች ብናበድራቸውም መልሰው መክፈል እማይችሉ በሚል (redlining ) ውስጥ ከከተቷቸው ውስጥ ጥቁሮች ይገኙበታል። ከዓመታት በኋላ ይህን የተረዱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በመታገላቸው ኮንግረስ ህግ አወጣ። 1977 የወጣው The Community Reinvestment Act (CRA)፣ (ኮሚዪኒቲ ሪ ኢንቨስመትን አክት  ) ህግ ባንኮች ቅርንጫፍ በከፈቱባቸው አካባቢዎች ያሉትን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለባቸው ግዴታን የጣለ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ባንክ ቅርንጫፍ ሲከፍት የተወሰነ ፐርሰንቱን ለአካባቢው ነዋሪዎች ማበደር ይኖርበታል። በርካታ አዋጆችን ከውጭ አገር እሚቀዱ የአገራችን ፖሊሲ አውጭዎች ይህን እንደሚያውቁት እንገምታለን። ችግሩ እንደ ጥቁሮቹ ሳይሆን እንደነጮቹ ሆነው ካወቁት ነው።
የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የንግድ ባንክ ነው።ከወራት በፊት በወጣው ዘገባ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ 347 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ደርሷል። ቅርንጫፎችን በየወረዳ የገጠር ከተሞች ሳይቀር እያስፋፋ ዛሬ 1 ሺህ 186 አድርሶታል። ዓላማው ገንዘብ ለማሰባሰብ (ዲፖዚት ሞብላያዜሽን) እና ትርፍ ለማጋበስ ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አተረፈ እሚል ዜና በየጊዜው እሚለፈፍ ስኬት ነው። ከደሃ ገበሬዎች ሳይቀር እሚሰበሰበውን ገንዘብ ግን እሚበደሩት ሌሎች ናቸው። ዜጎች ገንዘቦቻቸውን እሚያስቀምጡት በንግድ ባንክ ብቻ አይደለም። በኢትዮጵያ ዛሬ ወደ 18 እሚጠጉ የተለያዩ የግልና የመንግሥት ባንኮች አሉ። 2016 በወጣ አንድ ዘገባ 435 ቢሊዮን አላቸው ተብሏል። ወደ 21.5. ቢሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል። እስካለፈው ጁን ድረስ የቅርንጫፎቹ ቁጥር 3,153 ደርሶ ነበር፡፡
ስለዚህ ገንዘብና ትርፍ እየተሰበሰበ ነው።
ትርፉን ምን ያደርጉታል? ኤፈርት፣ ሜቴክ፣ ሚድሮክ …ከመሳሰሉ ድርጅቶች አንስቶ እስከ ግለሰቦች በብድር ረጭተው ጨርሰውታል እሚለውን ተነጋግረን ጨርሰነዋል። በዚያ ላይ ባንኮቹ ራሳቸው እሚያደርጉትን አሳጥቷቸዋል። በአሜሪካ እንደምናየው አንዳንድ የኢትዮጵያ ባንኮች የፕሬዚዳንቶቻቸውን ወርኃዊ የደመወዝ መጠን ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ማድረስ መጀመራቸውን አንብበናል። ሰማይ ጠቀስ ፎቆችና ትላላቅ ቢሮዎችን ለመስራት እየተሽቀዳደሙ መሆኑንም አይተናል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ እየገነባ መሆኑ ይታወቃል። የህወሓት ነው እሚባለው ውጋጋን ባንክም ከ805 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በቅርቡ አስመርቋል።ስቴዲዮም ጋር የተሠራው የወጋገን ህንጻ 29 ፎቆች ያሉት ሲሆን በአገሪቱ ረጅሙ ፎቅ ተብሏል። ህንጻውን እስከሰራበት ድረስ ባንኩ ለቢሮው በዓመት 20 ሚሊዮን ብር ኪራይ እየከፈለ ሲሰራ መኖሩም አንብበናል። የባንኩ አጠቃላይ ሀብትም ከ16.1 ቢሊዮን ብር ወደ 20.9 ቢሊዮን ብር ገደማ ማደጉን  ኃላፊዎቹን ከጠቀሰ የሪፖርተር ዘገባ መረዳት ይቻላል። እና ወጋገንም እንዲሁ በመላው አገሪቱ  የከፈታቸው ቅርንጫፍ ባንኮች 245 መድረሳቸው ተነግሮናል። በእነዚህ ቅርንጫፎች የሰበሰባቸውን ብሮች እሚያበድረው ለማን ነው?
ለማንስ ቢሆን ማን ይጠይቃል?  ባንኩ ግን ባለ ራዕይ ነው። በህንጻው ምረቃት ወቅት እንዲህ ተብሏል “ወጋገን ባንክ እ.ኤ.አ በ2025፣ በአፍሪካ ከሚገኙ አስር ስመ-ጥር ተፎካካሪ ባንኮች አንዱ ለመሆን ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት አዲሱ ህንጻ  ዋነኛ አጋዥ ይሆናል”
የኛ የሰፊው ህዝቦቹ ራዕይ ግን ምን ይሆን? እርግጥ ነው ይህ እማይመለከታቸውና ባንክ ተቀማጭ እሚሆን ገንዘብ የሌላቸው ወገኖቻችን ይበዛሉ። በኢትዮጵያም በመንግስት ድጋፍ ተደርጎላቸው ለፖለቲካው ድምቀት የተቋቋሙ 30 አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት አሉ። በአገሪቱ ካሉት 3ሺ የባንክ ቅርጫፎች አንጻርና ካለው የድህነት መጠንና የድሆች ቁጥር አንጻር እነዚህ ምንም አይደሉም። ከእነሱም ቢሆን ብዙዎቹ አቅም እያነሳቸው፣ በእዳ እየተዘጉና ሙስና እያዳለጣቸው ነው። ፍሬ ነገሩ ግን ገንዘባቸው ባንክ እሚያስቀምጡ ሰዎች ከባንኩ አነስተኛ ወለድ ሌላ እሚያገኙትም ሆነ እሚያስገኙት ጥቅም አለመኖሩን መረዳቱ ላይ ነው። ድሆች ወገኖቻቸውን ሳይሆን የበለጸጉና በሙስና የጨቀዩ ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎችን እየጠቀሙ መሆኑን ከማወቁ ላይ ነው። የዚህ መንግስት ህልውና ከባንኮች እና ከታክስ በሚገኝ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ማስተዋሉ ደግሞ የበለጠ ጠቃሚ ነገር ነው። እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ባንክ ለተከፈተበት አካባቢ ምን አድርጓል የሚል ጥያቄ ማንሳት ሁሉም አካባቢውን ቢያለማ አገርም እኩል በለማች ነበር እንደማለትም ይሆናል።
Filed in: Amharic