ይሀው ነው የአፓርታይድ ስርአት ነገር!
(ሄኖክ አበረ)
ከጨዋታቸዉ እንደተረዳሁት ሁለቱም በዘመነ ኢህአዲግ ወታደር የነበሩ ከኤርትራ ጋር በነበረዉ ጦርነት የተሳተፉ ናቸዉ። V8 መኪና ይዞ የገባዉ የትግራይ ሰዉ ሲሆን ጥበቃዉ ደግሞ የወሎ አማራ ነዉ። “እንዴት ነህ? እንዴት ነህ? ምን እየሰራህ ነዉ?” ሲባባሉ የትግራዩ ሰዉ “ምን ባክህ ትንሽ ጥይት ታፋዬ አካባቢ ጫር አርጋኝ ነበር፤ አዛዦቹ የኛ ሰወች ናቸዉ። ወዲያዉ ጡረታ እንድወጣ አደረጉኝ። አሁን ሰዎች ገቢዎችና ጉምሩክ አስቀጥረዉኝ ጥሩ ኑሮ እኖራለሁ። ደሞዙም አበሉም ጥሩ ነዉ። የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችም አሉት። ጡረታዬም አድጋልኛለች። አንተስ አንዴት ወጣህ? ” ሲለዉ አማራዉ “ምን ባክህ የፈንጅ ፍንጣሪ እግሬን መቶኝ ጦር ሀይሎች ሆስፒታል አንድ አመት ተኝቼ ተሰቃይቼ እግሬ ዉስጥ ብረት ገብቶልኝ ከመቆረጥ ተርፌ ጡረታ አስከብሩልኝ ብል ‘ባትዋጋ መጋዘን መጠበቅ ትችላለህ፤ ጤነኛ ነህ’ ሲሉኝ ተበሳጭቼ ከመከላከያ ወጣሁ፤ አሁን በጥበቃ ነዉ የምተዳደረዉ፤ ቅዝቃሴ ሲኖር ሌሊት ሌሊት ይጠዘጥዘኛል፤ ያዉ መኖር ከተባለ አለሁ“ አለ
እንባ ተናነቀኝ ፤ከዚህ በላይ መስማት ስላልፈለኩ ተነስቼ ሄድኩ፤ ጉዳዬን ጨርሼ ስወጣ ሀምሳ ብር ለጥበቃዉ ሰጥቼዉ ወጣሁ።