>
5:14 pm - Sunday April 20, 4206

ህወሀት ግብዝ ነው ሊመጣ ያለውን ነገር ቀድሞ የመገንዘብ አቅሙ ደካማ ነው (ሚኪ አማረ)

ህወሃት የቀድሞ አቋሙን ለመመለስ በሁለት ቡድን ላይ ተመስርቶ ላይ ታች እያለ ነዉ፡፡ የኢህአዴግ ቁንጮወቹን የሲቪል ፖለቲከኛዉ ቡድን ሰብስቦ የተዛነፈ (በወያኔ ቋንቋ) አስተሳሰብ መታረም አለበት እስካልተራረምን ድረስ አንላቀቀም እያለ ይገኛል፡፡ ታችኛዉን ባለስልጣንና ህዝቡን ደግሞ የወታደሩ ክፍል በአስቸኳይ አዋጅ ስም በማሰርና በማፈን የተነሳበትን ተቃዉሞ ለማዳፈን እየሞከረ ነዉ፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ያሉ የታችኛዉ አመራርና የአዲሱ ኦህዴድ ስሪት የሆኑትን በማሰርና ከስልጣን በማባረር ተጠምዷል፡፡የዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን አሁን ኢትዮጵን ማዳን ከሚለዉ ወረድ ብሎ ኦህዴድን ማዳን አይነት ደረጃ ላይ ገብቷል፡፡ ዶ/ር አብይ ምናልባትም ጠቅላይ ሚኒስቴር ካልሆነ አዲሱ ኦህዴድ ወደ ቀድሞዉ ቁመናዉ ተመልሶ እነ አባዱላ እንደለመዱት የገበሬ መሬት ይቸበችቡበታል፡፡በነገራችን ላይ አባዱላ የዘረጋዉ ቡድን የገበሬዉን መሬት ያለርህራሄ እያፈናቀሉ ሲሸጡ የለማ ቡድን ቢቸግረዉ የከተሞችን ከንቲባወች በሙሉ ሴቶች አደረጓቸዉ፡፡
የህዝብ አመፅ ቢቀጥልም በአዲሱ ኦህዴድ የተዋቀረዉን የሰዉ ሃይል ከመታሰርና ከስልጣን ከመባረር የማስቀረት ሃይል አይኖዉም፡፡ እንዲያዉም ከዚህም ከፍ ሲል በገዱ አንዳርጋቸዉና በበረከት ሽምግልና የቀረዉ የዶ/ር አብይና ለማ መገርሳ ይታሰሩ ተብሎ የተፈረደበት የ17ቱ ቀን ግምገማ ላይ የቀረበዉ የፍርድ ቤት የእስር ትእዛዝ እንደገና ከመሳቢያ ወቶ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ህወሀት ግብዝ ነዉ ሊመጣ የሚችለዉን ነገር የመገንዘብ አቅሙ ደካማ ነዉ፡፡ አሁን ያለዉ ቀዉስ የመጣዉም በህወሃት ግብዝነትና እያንዳንዱ የሚያደርጋቸዉ ነገሮች ለዚህ ጉዳይ እንደሚዳርጉት መተንበይ ባለመቻሉ ነዉ፡፡ በዚህ ግብዝነቱ ተነስቶ ነዉ ባለፈዉም ካላሰርኳችሁ ሲል የነበር፡፡ በረከት የህወሃትን ግብዝነትና አላዋቂነት በደንብ ይገነዘባል፡፡ ባለፈዉም እነ ዶ/ር አብይ አይታሰሩም ብሎ የተከራከረዉ እነሱን ለማዳን ሳይሆን ሊመጣ የሚችለዉን ችግር በመረዳት ነዉ፡፡ ሌላዉ በሚቀጥለዉ ሳምንት የኢህአዴግ ምክር ቤት ይሰበሰባል መባሉም ህዋሀት ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሆናል ያለዉን ሰዉ መርጦና ወስኖ መጨረሱን ያሳያል፡፡
ሌላዉ አጋዚ ባሌ አካባቢ በመቶወች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ወታደራዊ ስልጠና እያሰለጠነ ነዉ የሚል መረጃ ወቷል፡፡ ወጣቶችን በማሰልጠን የተመረጡ አካባቢወችን እንዲያጠቁና ከዛም የኦነግ ወታደሮች ጭፈጨፋ አደረሱ እንዲሁም የክልሉን ጸጥታም ከክልሉ አቅም በላይ ሁኗል በማለት ወታደሩ ሙሉ ለሙሉ አካባቢዉን ለመቆጣጠር ያለመ ነዉ፡፡ በእነዚህ በሚያሰለጥናቸዉ ሰወች አማካኝነት ምናልባትም የሌላ አካባቢ ተወላጆች ላይ ጥቃት በመፈጸም በህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለዉን ጤናማ ግንኙነት ለማበላሸት ያቀደ ይመስላል፡፡
በአማራ ክልል  ወያኔ ባብዛኛዉ ጠመንጃ የማስፈታት ስራ ላይ የተሰማራ ሲሆን ይሄም ክልሉን እንደገና ወደ ከፍተኛ ዉጥረት መልሶታል፡፡ የሰዉ ህይወትም እንዲሁ በከንቱ እየጠፋ ነዉ፡፡ አማራ ክልል ላይ አሁን እንደ ትልቅ ማስፈራሪያ መንግስት የያዘዉ ገበሬዎቹን ስብስቦ ይሄን ባታደርጉ ጠመንጃችሁን እንቀማችዋለን በማለት ነዉ፡፡ በዚህም ምክንያት ገበሬዉ እንደፈለገ ወደ ከተማና ወደ ገቢያ አይሄድም፤ የግብርና ስራዉንም ተረጋግቶ እየሰራ አይደለም፡፡ አብዛኛዉ ገበሬ በተጠንቀቅ ተራራ አካባቢ ተሳባስቦ ነዉ ሲያወጋ የሚዉለዉ፡፡ ቤት አካባቢ እኳን አይቀመጡም፡፡ በነገራችን ላይ በመንግስት የተመዘገበዉ መሳሪያ ከ 10 በመቶ አይበልጥም፡፡ እወስዳለዉ ቢል እንኳን ህብረተሰቡ ዉስጥ ያለዉን የመሳሪያ መጠን በሚፈልገዉ መጠን አይቀንሰዉም፡፡ አጉል ከህዝብ ጋር እልክ የመጋባትና ጉዳት የማድረስ ነገር ካልሆነ በቀር፡፡
በአንዳንድ አካባቢ ህዝቡ ላይ ተጽእኖ አላቸዉ የሚባሉትን ሰወች ጠመንጃ አስገቡ እንኳን ብለዉ ሳይጠይቋቸዉ እንዲሁ ቤታቸዉ በመሄድ በአሰቃቂ ሁኔታ ይገሏቸዋል፡፡ ይሄም የአካባቢዉን ህዝብ ተስፋ ለማስቆረጥ ሆን ተብሎ ተጠንቶ የሚደረግ ስራ ነዉ፡፡ ነግር ግን ዲያስፖራዉና ሶሻል ሚዲያ ላይ ያለዉ ሰዉ እንደዚህ ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ግድያወችን እንደማዉገዝና መንግስት ላይ ጫና እንደማሳደር ጀግና ነዉ፤ ጥሎት ሞተ የሚል ሰለብሬሽን ለወያኔ ምከንያት ከመስጠት ዉጪ ተጠያቂነትን አያመጣም፡፡ ዛሬ ባይጠየቁ እንኳን የሚጠየቁበት ጊዜ ስላለ፡፡ ያለጥፋታቸዉ በወያኔ የዝግ ስብሰባ ተመርጠዉ የሚገደሉ ንጹሃንን እንደ ህግ ጣሽና ጥፋተኛ አድርጎ መሳል የወደፊት ተጠያቂነትን ችግር ላይ ይጥላል፡፡ አንዲት ቀበሌ ዉስጥ አንድ ታዋቂ ሰዉ ሲሞት በቀበሌዉ የሚኖሩ ሁለት ሺህና ሶስት ሺህ ሰወች ላይ ያለዉ ሰነልቦናዊ ጫና ከፍተኛ ነዉ፡፡ ለወያኔ 10 አይደለም 100 ወታደር  ቢሞት ግዱ አይደለም፡፡ ለእኛ ግን አንድ ተጽእኖ ፈጣሪ አጣን ማለት ሰፊ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ስለዚህም ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡እንዲህ አይነት extra judicial killing ሲያጋጥም መንግስትን ተጠያዊ ማድረግና ግለሰቦችን ያለአግባብ እንደሚገል ማሳየትና ማጋለጥ ሲገባ የሚገደሉ ንጹሀን ዜጎችን ጦረኛ በማስመሰል ይሄን ያህል ወታደሮች ገደለ በማለት ኢ-ሰባዊ በሆነ መንገድ መገደላቸዉ ሳያንስ መንግስት ግድያዉን ተገቢ ነበር በጸጥታ ሃይሎች ላይ ጉዳት ስላደረሱ ነዉ እንዲል እድል እየሰጠ ነዉ፡፡ ቢገል እንኳን እኛ ገደለ ብለን ሪፖርት የምናደርግበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡
መልካም ቀን
Filed in: Amharic