>

የአማራ ጉዳይ መፍቻ ያጣ እንቆቅልሽ እየሆነ ነው!!! (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)

አማራ ነን እያሉ በስሜት የሚናጡት ሰዎች የሚጽፉትን ያነበበና አልፎ አልፎም አዳማጭ ሲያገኙ የሚናገሩትን የሰማ ከፕሮፌሰር ዓሥራት ጀምሮ የጎሣ ፖሊቲካ ፓርቲ ለማቋቋም የተደረገውን ሙከራ ሁሉ መክሸፉን አልሰሙም፤ አያውቁም፤ መለስ ዜናዊ ከጓደኞቹ ጋር የፈጠረውን ጭራቅ የኩራትና የዳቦ አባታቸው (ዓሥራት ሆዳም ያላቸውን) አድርገው ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ፤ ሆኖም ፈልገው ፈልገው እስካሁን አላገኙትም፤ ሆዳሞች ሞልተዋልና የወያኔን ጭራቅ መፈለጉ አላቆመም፤ በወልቃይት ጸገዴ፣ በአርማጭሆ፣ በጎንደር፣ በደብረ ታቦር፣ በየጁ፣ በአምባሰል፣ በወሎ፣ በይፋት፣ በአንኮበር፣ በመንዝ፣ በመርሀቤቴ፣ በጅሩ፣ በምንጃር፣ … በጎጃም፣ በዳሞት፣ በባሕር ዳር፣ … እየፈለጉት ቢሆንም ገና አላገኙትም፤ የሚያስከብርና የሚያወፍር እንጀራ መብያ ያላገኙ ሁሉ የጎሣ ድርጅት ማቋቋሙ እንጀራና ክብር የሚያስገኝ እየመሰላቸው የሚደክሙ አሉ፤ ከደሀነትም አልፈው የመንፈስ ደሀዎች ናቸው፡፡
እስቲ ከሰሙና ከገባቸው ለመጨረሻ ጊዜ አማራ ምን ማለት አንደሆነ ከመምህራኑ ያገኘሁትን ላቀብላቸው፤
1. አማራ ማለት

1.2. ከሣቴ ብርሃን ተሰማ
‹‹የተመረጠ፣ ነጻነት ያለው ተውልድ፣ … ዐም ሕዝብ፣ ሓራ ሔር የወጣ ጨዋ፣ ነጻነት ያለው ወገን ወይም አሸናፊ፣ ድል ነሺ ዋና አለቃ ማለት ነው፤
1.3. አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ዐም ሕዝብ፣ ሐራ ነጻ በተገናኝ ነጻ ሕዝብ ገዢነት እንጂ ተገዢነት የማይስማርው ማለት ነው፤ ዐማራነት ዐማራ መሆን ተገርዞ፣ ተጠምቆ፣ ማተብ አስሮ የሚኖር ነው፤
1.4. አለቃ ዓጽሜ አማራ ከወዴትም አልመጣም ጥሩ የላስቶች ወታደር፣ከየዓይነቱ የተጠራቀመ፣ ኃይለኛ፣ ግፈኛ፣ አድመኛ እውቀት ያለው ያልተማረ ጨካኝ ጭፍራ ነው፤
1.5. የአባ ዮሐንስ ትግርኛ/አምሐርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ አምሐራ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ነው፤›. የሚል ነው፤
1.6. ንቡረ እድ ኤርምያስ ዐማራ ማለት ‹‹በነጻነት የመኖርን ጸጋ ከእግዚአብሔር በቃል ኪዳን ላገኘው ከየነገዱና ከየጎሣው በጋብቻ፣ በልደትና በኅብረተሰባዊነት ተዋህዶ አንድ ፍጹም ሙሉ ዘር ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰጠ የኅብረ ነገድ ወይም የኅብረ ብሔር አጠቃላይ የባሕርይ መታወቂያ ስያሜ እንጂ የአንድ ጎሣ ስም አይደለም፡፡

ሰለጎሣ ማወቅና መረዳት የፈለጉ በጎሣነት የታወቁ ማኅበረሰቦች እያንዳንዳቸው አባሎቹን ሁሉ የሚያያይዛቸው የጋራ መሪ እንዳላቸው መገንዘብ፣ በዘፈናቸው፣ በስክስታቸው፣ በምግባቸውና በመጠጣቸው፣ በልብሳቸው … መመሳሰል እንዳሉባቸው ማወቅ ይጠቅማል፡፡ መረጃንና ማስረጃን ለመቀበል ለሚችል አእምሮ በተዘረዘሩት ላይ ጠለቅ እያሉ በማሰብ የአስተሳሰብ ጉድፍን ለማጥራት ይቻላል፡፡
አንድ ሌላ አማራ ነን ባዮቹ የሚያመልጣቸው ግንዛቤ አለ፤ ጎሠኛነት በወያኔና በሌሎች ላይ ሲታይ በጣም ያንገሸግሻቸዋል፤ እነሱ ግን ጎሠኛነትን በሌላቸው ጉልበትና በስድብ ለማስፋፋት ሲሞክሩ ምንም የአስተሳሰብ ቅራኔ አይታያቸውም፤ በአንድ በኩል ወያኔ ጎሠኛነትን አምጥቶ አንድነታችንን አደጋ ላይ ጣለው እያሉ እየጮሁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጎሣን ለመፍጠርና የጎሣ ጦርነትን ለማፋፋም እሳት እያቀጣጠሉ ጨርቅ ሳይጥሉ ማበድ ይመስላል፡፡
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሦስት ሊቃውንት እንደሚያስረዱት አማራ የአንድ ጎሣ ስም አይደለም አማርኛ ቋንቋ የአማራ የሚባል ጎሣ ነው በሌላ ጊዜ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን፡፡

Filed in: Amharic