>
5:18 pm - Friday June 15, 0446

«አቶ ስዩም ተሾመና  አቶ ታየ ደንደአ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ»  [አምነስቲ ኢንተርናሽናል]

DW-አሻም ሚዲያ 
በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ መንግስትን በመተቸታቸዉ በኮማንድ ፖስቱ የተያዙትና በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ያለም ቅድመ ሁኔታ  እንዲለቀቁ  የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸዉን በመጠቀም በመናገራቸዉና በመጻፋቸዉ  በሃገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ ከታወጀ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ይነገራል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል «መንግሥትን በመተቸት» ታስረዉ የሚገኙ ሁለት ኢትዮጵያዉያንን በአስቸኳይ እንዲለቀቁ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል። አምነስቲ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ የሃሳብ ነፃነት መብታቸዉን በመጠቀም መንግሥትን በመተቸታቸዉ የታሰሩ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህርየኢንተርኔት አምደኛና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ስዩም ተሾመ እና በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፍትህ ቢሮ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ  አቶ ታየ ደንደአ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቋል።  ሁለቱ ሰዎች የት እንደታሰሩ በርግጠኝነት መናገር አንችልም ያሉት በኬንያ ናይሮቢ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪቃ ቢሮ ምክትል ተጠሪ ሳይፍ ማጋንጎ አምነስቲ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ይጠይቃል ብለዋል።
«ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከታሰሩበት እንዲለቀቁ ጥርያችንን እናስተላልፋለን። ይህን ጥሪ ያቀረብነዉ ሁለቱ ግለሰቦች ሃሳብን በነፃነት የመናገር መብትን ተጠቅመዉ የሚያምኑትን ነገር በመናገራቸዉ ነዉ። ሁለቱም የመናገር መብት አላቸዉ።በዚህም ምክንያት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ እንጠይቃለን።»
በኢትዮጵያ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ከታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኋላ ብዙ ሰዎች እንደታሰሩ ከተለያዩ ምንጮች መረጃዎች ቢደርሱንም ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ እና የት እንዳሉም በርግጠኝነት መናገር አልቻልንም ብለዋል ማጋንጎ። እንድያም ሆኖ ባለፈዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በሽዎች የሚቆጠሩ ያለፍርድ ታስረው እንደነበረ አስታዉሰዋል።
«ባለፈዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በተደረገበት ወቅት በሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለምንም ፍርድና ፍትህ ታስረዉ ነበር። አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ ባለፈዉ እንደሆነዉ ሁሉ አሁንም ይደገማል  የሚል ስጋት አለን። ከዚህ በተጨማሪ የአስቸኳይ አዋጁን ተከትሎ አሁንም ብዙ ሰዎች እየታሰሩ ነዉ የሚሉ ዘገቦች እናያለን። ግን አሁንም ስንት ሰዎች እንደታሰሩ እና የት እንደታሰሩ በርግጠኝነት መናገር አንችልም።
አሁን ጥሪ የምናስተላልፈዉ መንግስት ፣ሰዎች የመናገር መብታቸዉን ተጠቅመዉ ያሰቡትን የሚያምኑትን ነገር በመናገራቸዉ ያሰራቸዉንን እንዲፈታ ነዉ። ሌሎች ያለምንም ፍርድና ፍትህ ታስረዉ የሚገኙ ደግሞ ፍርድ ቤት ቀርበዉ ፍትህ እንዲያገኙ ነዉ። ያለምንም ፍርድ በእስር ይዞ እንዳያስቀምጥ ነዉ።»
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል መምህርና የኢንተርኔት አምደኛዉ አቶ ስዩም ተሾመ እና በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፍትህ ቢሮ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ  አቶ ታየ ደንደአ ጠበቃ የመያዝ መብት እንዲከበርላቸው እና ቤተሰቦቻቸዉ እንዲጠይቋቸዉ እንዲደረግ ጠይቋል። ሳይፍ ማጋንጎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንዲያከብር አምነስቲ ከመጽደቁ በፊት መጠየቁን አስታውሰዋል።
« ከጥቂት ሳምንታት በፊት የድርጅታችን ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያለምንም ማሻሻያ እንዳያፀድቅ ሲሉ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ተነጋግረዉ ነበር። እንዲያም ሆኖ አዋጁ ፀድቋል። የተደነገገዉ አዋጅ እና ሕግ ለኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ ሥልጣን የሚሰጥ ለትርጉም ሰፊና አሻሚ በመሆኑ ምናልባትም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ያስከትላል። የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ሕግ ተመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕግ የበላይነትን የኢትዮጵያን ሕግ መንግሥትን እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የገባቻቸዉን የሰብዓዊ መብት ግዴታዎች ባከበረ መልኩ ሊመለከተዉ ይገባል።»
ከዚህ ቀደም በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሦስት ወራት ታስረው የተፈቱት የአምቦ ዩኒቨርስቲ ወሊሶ ካምፓስ መምሕር፣ የኢንተርኔት አምደኛና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ስዩም ተሾመ የካቲት 29፤ 2010 ዓ.ም ዳግም በኮማንድ ፖስቱ ማዕከላዊ መታሰራቸዉን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሀን ተጽፏል። አንድ ጊዜ ለሦስት ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሰባት ዓመታት በአጠቃላይ ለአስር ዓመታትን በእስር የቆዩት በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፍትህ ቢሮ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታየ ደንደአም አሁን ደግሞ በኮማንድ ፖስቱ ወደ ማዕከላዊ መወሰዳቸዉ ተሰምቷል።
#DW_Amharic #Asham_Media #አሻም_ሚዲያ
Filed in: Amharic