( በአማን ነጸረ)

#ሰባኪው፡- … ውድ በሕግ ጥላና ዣንጥላ መካከል ያላችሁ ምዕመናን ወምዕመናንት፣ እዚህ ያሰባሰበን አምላክ የተመሰገነ ይሁን! (ሰዎቹ ምላሽ አልሰጡም!) መልስ ስጡ እንጂ?! ያሰባሰበን እሱ እኮ ነው! አይደለም እንዴ? … ማነው የሰበሰበን?
#የተያዙት፡- ፌደራል!
#ሰባኪው፡- እሱም ምድራዊ ነው! የሰማዩን አልኩ እንጂ?!
#የተያዙት፡- ነው እንዴ? እሱማ ዘነጋነው እንጂ አየር ወለድም አለበት!
#ሰባኪው፡- ‹‹አንትሙ፡ ተሀውሩ፡ ግድመ፡ ግድመ፡ ወአነኒ፡ አሀውር፡ ግድመ፡ ግድመ፡›› አለ መጽሐፍ! ተው እንጂ ምዕመናን ቀና ቀናውን ተናገሩ! አማኝ ልብና አንደበቱ አንድ ሲሆን ነው መልካም! ልብና አንደበቱ አንድ ሆኖ በተሰባሰበ ሕዝብ መካከል ፈጣሪም ይገኛል! አይደለም? … መልሱልኝ እንጂ? ‹‹ … 2ትም፣ 3ትም ሆናችሁ ብትሰባሰቡ በመካከላችሁ እገኛለሁ›› ሲል ያወጀልን ማን ነው? … መልሱልኛ?!
#የተያዙት፡- ኮማንድ ፖስት!
#ሰባኪው፡- ኧረ ተዉ ምዕመናን! የተገናኝንበትን አንርሳ! እደግመዋለሁ! አማኝ ልብና አንደበቱ አንድ ሲሆን ነው መልካም! ልብና አንደበቱ የማይገጥም፣ ተናግሮ የሚኖር፣ ግን ደግሞ የተናገረውን የማይኖርማ አማኝ ሳይሆን … እህሳ? … ምን ይባላል?
#የተያዙት፡- ህም! …ድሮ ካድሬ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን ሰባኪም፣ የሃይማኖት ‹‹አባትም›› ያው እየሆነ ነው!
#ሰባኪው፡- እናንተስ ተጣልቱዋችኋል!
#የተያዙት፡- ማን?
#ሰባኪው፡- ‹‹መንግሥት ነዋ!›› እንድል ትሻላችሁ … እኔ ለራሴ ዓለም በቃኝ ብዬ ቆብ የጫንኩ ሰው ነኝ! አ…ይ! እንግዲህ ….ምዕ…መናን…! ከፖለቲካ አታነካኩኝ! አሉና ዲኤክሳቸውን አስነስተው ነጎዱ – ሳያሳርጉ!
ድኅረ ታሪክ፡- “ከምሽቱ 2 ሰዓት ሆኗል፤ ከዜናዎቹ ጋር … ነኝ! በቅድሚያም አርእስቱን: ‹የሃይማኖት አባቶች በሕብረተሰቡ ያላቸውን ተቀባይነት መሠረት በማድረግ በአስቸኳይ ጊዜ የተያዙ ተጠርጣሪዎችን በአካል እየተገኙ ማጽናናታቸው ለአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ስኬት የማይተካ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡›” ETV-ZENA
ሀገሬ እንዲህም ያደርጋታል!