>

"መንግስት" ያጠቃት ከተማ (ጌታቸው ሺፈራው)

የአጤ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት ሆን ተብሎ እንዲፈርስ እየተደረገ ነው!?!
ከሳምንት በፊት ነው። አንድ ጓደኛችን አንድ ቤት ሊያስጎበኝን ጎንደር ቀበሌ 18 አካባቢ ወሰደን።  ከባጃጅ ሳንወርድ “ይህ ነው” ብሎ አሳየን። በሩና የውጨኛው አጥር፣ የቤቱ ግድግዳ ላይ የተበሳሳ ምልክት በጉልህ ይታያል።  ሀምሌ 5/2008 ዓም ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ከትግራይ በመጡ የታጠቁ የሰራዊት አባላት የታፈነበት ቤት ነው።  ይህ ጎንደር ከተማ ላይ የተፈፀመ የአፈና ተግባር ነው፣ ጥቃት ነው።  ይህ ጥይት የበሳሳው ግቢ ቤት ጎንደር ከተማ እየደረሰባት ላለው ጥቃት ምልክት ነው።  ቤቱ ላይ ጥቃት የተፈፀመው አንድ ቀን ነው። ጥቃቱ ግን በአንድ ቤት ላይ የተደረገ አይደለም።  ይህ ቤት ጎንደር ከተማ እየደረሰ ለሚገኘው ጥቃት ትልቅ ምልክት ነው። ጎንደርን ተዘዋውሮ ለተመለከተ መንግስት የሚባለው አካል  አቅዶ ያጠቃት  ከተማ እንደሆነች ይታዘባል።
ለምሳሌ ያህል:-
ጎንደር ከምትታወቅባቸው ተቋማት አንዱ ሆስፒታሉ ነው። ይህ እድሜ ጠገብ ተቋም ሶስት መንግስታትን ተሻግሯል። ሆኖም ይህ ሆስፒታል ቁሳቁሶች ስለማይሟሉለት እናቶች በረንዳ ላይ ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ ነው።  ወደ ሆስፒታሉ ይወስድ የነበረው ዘመናዊ መንገድ ሆን ተብሎ የተቆፈረ ያህል ፈርሷል። ከአሁን ቀደም መንገዱን የሚያውቅ ሰው “መንገድ ተሳስቼ ነው” ይል ካልሆነ ወደ ሆስፒታሉ እየሄደ ላይመስለው ይችላል። ስለዚህ መንገድ ስናወራ አንዱ ጓደኛዬ “መኪና እና ባጃጅ ሲያነሳ ሲያፈርጣቸው እናቶች ሆስፒታል ሳይደርሱ እየወለዱ ነው” ተብሎ መራራ ቀልድ እንደሚቀለድ አጫውቶኛል።
ከጎንደር ሆስፒታል ወደ አዘዞ የሚወስደው መንገድ በሙሉ  ፈርሶ፣ ከአሁን ቀደም ዘመናዊ መንገድ የነበረው አይመስልም። ይህን መንገድ ተከትሎ ሎጅና ሆቴሎች ተሰርተዋል። ሆኖም ሁሉም የመንገዱ መብራቶች አይሰሩም። መንገዱ፣ ሆቴልና ሎጅዎቹን ድቅድቅ ጨለማ ውጧቸዋል።
የአጤ ፋሲለደስ ቤተ መንግስት ሆን ተብሎ እንዲፈርስ እየተደረገ ነው። ገዥዎቹ የሌሎችን ሕዝቦች ጭፈራ የራሳቸው አድርገው ለማስመዝገብ ዓለምን ሲያካልሉ ቀድሞ አለም ያወቀውን ቅርስ ግን ተረስቷል። የግንቡ ክፍሎች እየወላለቁ ነው። እናቶች ጠዋታ ጠዋት የፈራረሱትን ጎዳናዎች ሲያፀዱ ይታያሉ። የፋሲልን ቤተ መንግስት ግን የሚንከባከበው የለም። የወፍ ኩስና ላባ እንኳ የሚያነሳ የፅዳት ሰራተኛ እንዴት መቅጠር ያቅታል? አግዳሚ ወንበሮቹ ተሰባብረዋል፣ በሮች ተገነጣጥለዋል። ማንም እየገባ ግድግዳው ላይ ሲፅፍበት ይውላል። ይህ ሁሉ ሆን ተብሎ ካልሆነ በስተቀር በዩኒስኮ የተመዘገበ የዓለም ቅርስ እንዲህ ሊረሳ አይችልም።
የፋሲል  ቤተ መንግስት በአመት በርካታ ገንዘብ ያስገኛል።  ሆኖም ግቢውን ለማፅዳት የተወሰነ ገንዘብ እንኳ አልተመደበለትም፣ ተመድቦለት ከሆነም  ቅርሱን ለመጠበቅ እየዋለ አይደለም።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የአጤ ፋሲለደስን ቤተ መንግስትን በጎበኘበት ወቅት  “እኛ እየጎበኘን ያለነው በዘመኑ የተሰራውን ሳይሆን ከዛ ዘመን በኋላ ቅርሱን ለመጠበቅ ምንም እንዳልተሰራ ነው” ነበር ያለው።
 በእርግጥ በቅርሱ ላይ የተሰራ ነገር አለ።  የፌደራል መንግስት የሚጠቀምበት በርካታ ዶላር ለሚያስገኝ ቅርስ የፅዳት ሰራተኛ አለመመደብ ወይንም ቅርፁን በንፅህና አለመያዝ፣ በዩኒስኮ ለተመዘገበው ውድ ቅርስ የድብቅ ካሜራ እንኳን ለመግጠም አለመቻል ቅርሱን እንዲጠፋ ተሰርቷል ማለት ነው። በጉብኝት አብሮን የነበረ አንድ ወጣት ቅርሱ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ልዩነት በ6 ወር ውስጥ በግልፅ እንደሚያየው አጫውቶኛል። በየ 6 ወሩ ግልፅ የሆነ የመፍረስ አደጋ እንዲጋረጥበት ከማድረግ በላይ ምን ይሰሩበታል?
ጎንደር የቱሪዝም ከተማ ነች። ጎንደር በአብቃዩ አርማጭሆ፣ ደንቢያ፣ ቋራ… …ወልቃይት የተከበበች ከተማ ነች። ጎንደር ወደ ሱዳን መውጫ ከተማ ነች። ያም ሆነ ጎንደር ላይ የረባ ኢንቨስትመንት አይታይም።  የከተማዋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሚታሰበው በላይ የተፋዘዘ ነው።
በአንድ ከተማ የፌደራልና የግል ተቋማት የሚሰሩት ህንፃ በራሱ ኢንቨስትመንት ነው። የጎንደር አብዛኛዎቹ ህንፃዎች ይህ “መንግስት” ስልጣን ከመያዙ በፊት የተገነቡና በመንግስት የተያዙ ህንፃዎች ናቸው። እነዚህ ህንፃዎች በኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ የሚተዳደሩና ከአስር ብር ያነሰ “ኪራይ” የሚከፈልባቸው ናቸው።  አብዛኛዎቹ የፌደራል፣ የክልሉና የከተማው የ”የመንግስት” ተቋማት የራሳቸውን ህንፃ ከመገንባት ይልቅ በነፃ በሚባል ዋጋ በሕዝብ ህንፃ ህዝብ ላይ ትርፍ እየሰበሰቡ ቀጥለዋል።
የገዥዎቹ “ጥገት” የሚባሉት ቴሌ፣ መብት ኃይል፣ ፖስታ አገልግሎትና ሌሎችም የሕዝብን ህንፃ ይዘው ቀጥለዋል። ከመንግስት ተቋማት በተጨማሪ ካድሬዎቹ እስከ 10 ብር በሚደርስ ዋጋ የሕዝብ ህንፃዎችን  (አንድ ሙሉ ግቢ) ተከራይተው ይኖራሉ።
የጎንደር ማስተር    ፕላን በተሰራበት ወቅት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስተያየት በተጠየቀው መሰረት አየር እየሸጠ፣ ሲፈልግም ያውንም እያቆራረጠ በሕዝብ ላይ የሚነግደውም ቴሌን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልሉና የከተማው ተቋማት የየራሳቸውን ሕንፃ እንዲሰሩ አስተያየት ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ተቋማቱ አላደረጉትም። ምክንያቱም የሕዝብን ህንፃዎች በነፃ ተከራይተው ማትረፍ አለባቸው። አዲስ አበባን ጨምሮ ተቋማቱ የየራሳቸውን ህንፃ የሰሩባቸው ቦታዎች አሉ። ጎንደር ላይም መስራት ከብዷቸው አይመስለኝም። እነዚህ ሁሉ ተቋማት የየራሳቸውን ህንፃ ቢሰሩ ኢንቨስትመንት ነው። መንግስት ነኝ የሚለው አካል ሆን ብሎ ማጥቃት የሚፈልጋት ከተማ፣ እያጠቃት ለምትገኘው ጎንደር ደግሞ ኢንቨስትመንት አያስፈልግም ተብሏል። ይህን ለመረዳት ጎንደርን ዞር ዞር ብሎ ማየት ይጠይቃል።
ጎንደር መንግስት ነኝ ባይ አካል አስቦ እያጠቃት ያለች ከተማ ነች። ከአሁን ቀደም የውጭ ወራሪዎች አጥቅተዋታል።  ነገር ግን ድርቡሽ ቀድሞ የነበረውን መንገድ ያጠፋ አይመስለኝም፣ የአጤ ፋሲለ ደስ ቤተ መንግስትም የከፋ አደጋ ላይ የወደቀው ዛሬ ላይ ነው።
በዚህ የቴክኖሎጅ ዘመን ጎንደርን የመሰለች ከተማ እንዳትለማ የታቀደ እቀባ ማድረግ ከአሁን ቀደም የነበሩት ጠላቶች ካደረሱት ጥፋት የባሰ ያደርገዋል። ጎንደርን ተዘዋውሬ ስመለከት ኮ/ል ደመቀ ታፍኖበት የነበረው በጥይት የተቦዳደሰ ቤት ይታወሰኛል።  ትህነግ የላካቸው ወታደሮች ኮ/ል ደመቀን ለመግደል ያን ሁሉ ጥይት እንደተኮሱ፣ ያን ውብ ቤት በጥይት እንደቦዳደሱት ሁሉ፣ ይኸው “መንግስት ነኝ” ባይ ጎንደር ላይ ግልፅ የሆነ ጥቃት እንዳደረሰ ጠባሳዎቿ ከርቀት ይመሰክራሉ።
(የሚታየው ፎቶ በ1970ዎቹ የተነሳ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ይህ አካባቢ በፎቶው ላይ ከሚታየው የተራቆተ ገፅታን ይዞ ይታያል
Filed in: Amharic