>

30 ደቂቃ በማዕከላዊ (ወሰንአየሁ መርሻ)

ትናንትና አመሻሽ አካባቢ ወዳጄ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ሰለሞን ስዩም ስልክ ደወለልኝ እንዲህ አለኝ፡-
“ነገ ምን ፕሮግራም አለህ? ፕሮግራም ከሌለህ ስዩም ማዕከላዊ ሄደን ተሾመን እና ታዬ ደንደአን ብንጠይቅስ?”
“አይገርምህም እኔም ይህንኑ አስቤ ዛሬ ቀበሌ ሄጄ የነዋሪነት መታወቂያዬ አሳድሻለሁ” አልኩት፡፡ እናም የዛሬ ፕሮግራማችንን በዚሁ አፅንተን ተሰነባብተን፡፡
.
ዛሬ ዕለተ ረቡዕ (መጋቢት 13) ከቀኑ 7 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ወደ ማዕከላዊ አመራን፡፡ ማዕከላዊ በኋላ በር በኩል ያለ የጥበቃ ክፍል ውስጥ መሳሪያ የታጠቀ ፖሊስ ተቀምጧል፡፡ ከጥበቃው ቤት ውጪ ሌላ ያልታጠቀ ፖሊስ ቆሟል፡፡ እናም ጠጋ ብለን “እስረኛ ለመጠየቅ ፈለገን ነበር” አልነው፡፡
“ይቻላል፤ ማንን ነው የምትጠይቁት?”
ነገርነው፡፡
“አንድ ሰው ብቻ ነው መጠየቅ የምትችሉት”
“እሱ ታዬ ደንደአን፤ እኔ ስዩም ተሾመን ነው የምንጠይቀው”
“ትችላላችሁ”
“እሺ፤…. እዛጋ የሆነ ነገር ገዝተን እንምጣ”
“መግዛት የምትፈልጉት ውስጥ አለ” አለ ፖሊሱ ወደ ግቢው እየመራንና ወደ አንድ ክፍል እየጠቆመን፡፡ “መጀመሪያ እዚህ ተመዝገቡ”
እንደተባልነው ተመዘገብን፡፡
“የያዛችሁትን እቃ ሁሉ እዚህ አስቀምጡ” አለ ሌላ ፖሊስ ለፍተሻ እየተዘጋጀ፡፡ “ወረቀት፣ እስኪሪፕቶ፤ ሞባይል ….ወ.ዘ.ተ”
በየኪሳችን ያለውን ሁሉ አስረከብን፡፡ ፖሊሱ ፈተሸንና ግቢው ውስጥ ያለውን ሱቅ ጠቆመን፡፡ የታሸገ ውሃና ቆሎ፣ የልብስና የገላ ሳሙና፣ ሶፍት … ወ.ዘተ አለ፡፡
.
ከሱቁ ፈንጠር ብሎ እስረኛች እና ጠያቂዎች ተደርድረው ይታያሉ፡፡ ከጀርባ ፖሊሶች ቆመዋል፡፡ ወደዚያው ጠጋ ብለን ለአንዱ ፖሊስ የምንፈልጋቸውን እስረኞች ስም ነገርነው፡፡ ስማቸውን የያዘው ብጣሽ ወረቀት ፅፎ “እዚያ ጋ ተቀምጣችሁ ጠብቁ” አለን አግዳሚ ወንበር ያለበትን ዳስ በጣቱ እየጠቆመን፡፡
.
ከአፍታ በኋላ ታዬ ደንደአ ከውስጥ ብቅ አለ፡፡ ሰለሞን ስዩም ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደ እሱ ሄደ፡፡ እኔም ባለሁበት ሆኜ እጄን አውለበለብኩለት፡፡ ታዬም እንደዚያው እጁን እያውለበለበ መልስ ሰጠኝ፡፡ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት … ደቂቃ ካለፈ በኋላ ስዩም ተሾመ ብቅ አለና በዐይኑ ጠያቂውን ሰው አማተረ፡፡ እጄን አንስቼ ምልክት አሳየሁትን ታዬ ደንደአ ወደቆመበት ቦታ ጠቆምኩት፡፡ መጠየቅ የሚቻለው አንድ ሰው ነው ስለተባለ በዚያው ታዬን ለማዋራት እንዲመቸኝ ነበር ቦታ የጠቆምኩት፡፡
“አይቻልም፤ በዚህ በኩል ና” አለው ከውስጥ አጅቦት የመጣው ፖሊስ፡፡ “ምንም ማድረግ አይቻልም” አልኩ ለራሴ፡፡ እናም …. ጨበጥኩት፡፡
“እንዴት ነህ ስዩሜ?”
“ደህና ነኝ፤ እግዚአብሔር ይመስገን”
“ጤንነት ….ምናምን?” አልኩ፤ መጠየቅ የፈለግኩት ሌላ ነገር ነበር፡፡ የፖሊሶችን ስሜት በወጉ ስላላጤንኩ አልደፈርኩም፡፡
“ደህና ነኝ፤ በጣም ደህና ነኝ፡፡ ይቅርታ አርግልኝ…. አላወቅኩህም” አለኝ ስዩም፡፡
“አዎ በአካል አንተዋወቅም፤ በአየር ላይ (በፌስቡክ ነው) የምንተዋወቀው” አልኩና ስሜን ነገርኩት፡፡
“ኦ…. አንተ ነህ እንዴ?” አለና ሳቀ፤ እየተሳሳቅን ጥቂት አወራን፡፡
ወዲያው “ይቅርታ ብዙ ላነጋግርህ አልችልም፤ ፍርድ ቤት ልቀርብ እየተዘጋጀሁ ነው የመጣኸው፤ ልሰናበትህ ነው”
“ፍርድ ቤት እንደምትቀርብ አውቃለሁ፤ ቻው”
ስዩም ወደ እስር ክፍሉ ሲመለስ አጅቦት ወደ መጣው አጠገባችን ወደቆመው ጠና ያለ ፖሊስ ዞር ብዬ “ታዬን እንድጠይቀው ብትፈቅድልኝስ?” አልኩት፡፡
“ትችላለህ” አለኝ፡፡
.
በዚች ደቂቃ ሌሎች እስረኞችና ጠያቂዎች አልነበሩም፡፡ ታዬና ሰለሞን ብቻ ናቸው ያሉት፡፡
ሰለሞን “ጓደኛዬ ነው፤ እና ደግሞ ጨንቋሪ ነው” አለና ስሜን ነግሮት አስተዋወቀን፡፡ “ስለመጣህ አመሰግናለሁ” አለ ታዬ ደንደአ፡፡ ጥቂት የሰላምታ ቃላት ከተለዋወጥን በኋላ “እና …እንዳልኩህ ነው” አለና ከሰለሞን ጋር የጀመረውን ወሬ ቀጠለ፡፡
“እና እንዳልኩህ…. ሰዎች የፖለቲካ አመለካከታቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ ያልሆነ ስም እየለጠፉ የማሸማቀቅ ስልት ያለፈበት ነው …  በዚህ ዘመን የአማራ ገዢ መደብ ምናምን እያሉ ማሸማቀቅ አይሰራም፡፡ በዚህ ዘመን የአማራ ገዢ መደብ የሚባል ነገር የለም፤ ይኑር ቢባል እንኳ ሊኖር አይችልም፡፡….”
.
እኔ የታዬን አባባል እያመነዠኩ ከጀርባው የቆሙትን ፖሊሶች ስሜት እያጤንኩ ነው፡፡ ፖሊሶቹ የምናወራውን የሚሰሙ አይመስሉም፡፡ ታዬ ስለ አገሪቱ ያለፈ ታሪክ እያወራ ነው፡፡
“… አዎ ባለፉት ዘመናት ስህተት ተፈፅሟል፤ ስህተቱ ባይፈፀም ጥሩ ነበር፡፡ ግን ተፈፅሟል፤ ስህተቱን የፈፀሙት ጨቋኞችም ተጨቋችም አልፈዋል፤ እነዚያ ወገኖች በህይወት ካለፉ 50 እና 100 ዓመት ከዚያም በላይ አልፏቸዋል፡፡ እኛ ግን ያንን የታሪክ ስህተት እየቆሰቆስን መኖር የለብንም፡፡ ምንም አይጠቅመንም፤ የራሳችንን አዲስና ካለፈው የተሻለ ታሪክ ነው መስራት ያለብን፡፡ ….”
.
ይገርማል፤ የታዬ ደንደአ የንግግር ብስለት ይገርማል፤ ወረቀት ላይ የተፃፈ ንግግር የሚያነብ ነው የሚመስለው፡፡
.
“…. ዶ/ር አቢይ በአንድ ወቅት እንደተናገረው ይህቺ አገር ያላት ሃብት ለ100 ሚሊዮን አይደለም፤ ለ300 የሚበቃ ነው፡፡ እኛ ያቃተን የዚህችን ለም ሀገር ሃብት እንዴት መጠቀም እንዳለብን አለማወቃችን ነው፤ አለማወቅ ሳይሆን ተነጋግረን፣ ተወያይተን መግባባት አለመቻላችን ነው፤ አለመደማመጣችን ነው፡፡  ከሃገሪቱ ዳቦ ትልቁን ድርሻ ‹ለእኔ ብቻ- ለእኔ ብቻ› እያልን መስገብገባችን ነው፤ እንጂ ሃገራችን ለ300 ሚሊዮን ሕዝብ የሚበቃ ሃብት አላት”
.
በውይይታችን መሃል የታዬን የቀደመ ታሪክ ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ እርግጥ ነው ታዬን እስከዚች ደቂቃ ድረስ በአካል አላውቀውም፡፡ ስለ ታዬ ታሪክ ያወቅኩት በቅርቡ #BBC_አማርኛ “ታዬ የህግ ድግሪውን አጠናቆ ለመመረቅ አስራስድስት ዓመታት ፈጅቶበታል” በሚል ርዕስ ያቀረበውን አጭር ዘገባ አንብቤ ነው፡፡ ታዬ ዲግሪ ለመያዝ ይኼን ያህል ጊዜ የፈጀበት በእስር ምክንያት መሆኑን ዘገባው ያትታል፡፡ እዚህ ላይ የ#BBC_አማርኛን ዘገባ በጥቂቱ ቃል በቃል ልጥቀስ፡-
.
“….ሆነም ቀረም ታዬ ለአስር ዓመታት እስር ወደ ማረማያ ቤት ተላከ። መጀመሪያም በቁጥጥር ስር ሲውል አስር ዓመት እንደሚያስፈርድበት የያዘው የፖሊስ መኮንን ዝቶበት ነበር። ይግባኝ ቢጠይቅም ተሰሚነት አላገኘም። ‘ፀፀት የሚባል የለም’
‹ማረሚያ ቤት ማለት በቀን ለ24 ሰዓታት የፈለከውን ነገር ማድረግ የምትችልበት ቦታ ማለት ነው። እኔም መናደዴን ትቼ ሦስት ነገሮችን ለማሳካት ወስኜ ተነሳሁ” ይላል ታዬ። እነዚህም አንድ ከመፃህፍት እንዲሁም በእውቀት እና በዕድሜ ከሚበልጡት መማር፤ ሁለት መፃህፍትን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ መተርጎም እንዲሁም ሦስተኛው የማረሚያ ቤት ጓደኞቹን የኦሮምኛ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማር ነበሩ።
በማረሚያ ቤት ቆይታው ወቅት ‘ገላ ደሎታ’ ወይም ‘ስንቅ ለመጪው ትውልድ’ በሚል ርዕስ ተረት እና ምሳሌ አዘል መፅሃፍ አዘጋጀ። “በማረሚያ ቤት ባሳለፍኩት ጊዜ ፀፀት የሚባል ነገር አይሰማኝም” ባይ ነው ታዬ።
.
ይኼንን ዘገባ እያሰብኩ የታዬን ንግግር አቋረጥኩና ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡
“ታዬ ይቅርታ ስላቋረጥኩህ፤ የአሁኑ የእስር ቤት አያያዝህ እንዴት ነው? ድብደባ ምናምን …?”
“ድበደባ የለም፤…ምርመራ ብቻ ነው” አለኝ ታዬ፡፡
ጆሮዬን አላመንኩትም፡፡
“ስትያዝም ሆነ፤ ከተያዝክ በኋላ ድብደባ የለም”
“የለም”
“ጥፊ እንኳን አልተሰነዘረብህም?”
“በፍፁም.፤ ማንም እጁን አላነሳብኝም፤ አሁን እኮ እንደዱሮው አይደለም፤ ከ2ወር ወዲህ ካለፈው ስብሰባ በኋላ (የኢህአዴግ የ17 ቀን ስብሰባ ማለቱ መሰለኝ) ነገሮች ተቀይረዋል፤ በምርመራው ወቅት በጥያቄ ብቻ ሊጫኑህ ይሞክራሉ እንጂ ድብደባ የለም፡፡ ….” አለኝ፡፡
.
ከዚህ በኋላ ወደ ቀደመው ወሬአችን ተመለስን፡፡ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ድንገት ግን ታዬ እጁን ብድግ አድርጎ ምልክት ሲሰጥ አየሁ፡፡ ለሌላ ጠያቂ ምልክት እየሰጠ ነው፡፡
“በል ፤ ሌሎች ጠያቂህን አነጋግር፤ እኛ ቦታ እንልቀቅ አለ – ሰለሞን ለስንብት እጁን እየዘረጋ፡፡ እኔም ልሰናበተው እጄን ዘረጋሁ፡፡
“ጋዜጠኛ ነህ አይደል?” እጄን ይዞ፡፡
“ነን ብለናል”
“አሁንም እየፃፋችሁ ነው?”
“አዎ፤ እየሞከርን ነው፤ ራሳችንን ኤዲት እያደረግ ለመፃፍ እየሞከርን ነው”
“በርቱ፤ በዚህ አገር ተስፋ አትቁረጡ”
.
ይቺኑ አባባሉን እያላመጥኩ ተሰናብቼው ወጣሁ፡፡ ወጣን፡፡
“በርቱ፤ በዚች አገር ተስፋ አትቁረጡ……ህም!”
.
ያን ሁሉ የመከራ (የእስር ዘመን) አሳልፎ፤ አሁንም የመከራ ጭቃ ውስጥ ተወርውሮ “በዚህች አገር ተስፋ አትቁረጡ” የሚል፣ የማያቄም (ያላቄመ) ብርቱ ሰው ማየት፣ በተስፋ የታሸ እምነቱን ሲያርከፈክፍብኝ ደስ አለኝ!
Filed in: Amharic