
ለእውቀትና ለእውነት ደንታ የሌላቸው ሰዎች መሆናቸውን፣ ሌላው ቀርቶ የተጻፈውን እንኳን በትክክል ሳያነቡና ሳይገባቸው እንደየበር ላይ ውሻ የሚጮሁ መሆናቸውን ለማሳየት ሁለት ማስረጃዎችን አቀርባለሁ፤ አንደኛ አማራ የለም አላልሁም የትም ቦታ አላልሁም፤ ያልሁት አማራ የሚባል ጎሣ የለም ነው፤ በዚህ ትርጉሙ ድርጅቶች ተቋቁመው ሲፈልጉት ሁለት ዓመታቸው ነው፤ ገና አላገኙትም፤ አማራ የሚለውን ቃልም ሆነ ጎሣ የሚለውን ቃል በትክክል የማያውቁት ፊደላውያን ጩኸታቸው የብዙ ሰዎችን ጆሮ ስለጎዳ ለማብራራት ወሰንሁ፤ የኔ የግል አስተያየት እንዳልሆነም ለማሳየት ታላላቅ ሊቃውንትን በአስረጂነት ደርድሬ ነበር፤ ስሕተቴ ሊቃውንቱን ከድንጋይ ራሶች ጋር ለማስተዋወቅ መሞከሬ ነው፤ አይለምደኝም፤ የለመዳችኋቸው እንደለመዳችሁት ያስተምሯችኋል፡፡
ሁለተኛ፣ አማራ ለሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ለመስጠት አልሞከርሁም፤ ግን ሊቃውንቱ ከጻፉት ውስጥ ይነበብ ነበር፤ ከድንጋይ ራሶቹ አንድም የተጠቀሱትን አንብቦ የተረዳ የለም፤ ያሳዝናል፤ የአማራን ትክክለኛ ትርጉም ለመቀስቀስ የዞረባቸው የወያኔ ከድሬዎች ሥራ የጀመሩ ይመስላል፤ እስላም ጠቀላይ ሚኒስትር ሊሆን ነው እየተባለ ይወራል፤ ይኸ ወሬ አማራን ሊቀሰቅስ የሚችለው እስላም አማራ ሳይባል፣ አማራ ጎሣ ሳይባል ነበር!