ቻይና በኢትዮጵያ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖና የቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶች ትስስርን በማስፈጸም በኩል አቶ መለስ ዜናዊና ድርጅታቸው ያደረጉት ነገር ቢኖር ሁለት ሰዎችን ለዚህ የተለየ ኃላፊነት መመደብ ነበር። አንደኛው ከውጭ ጉዳይ ምኒስትርነታቸው ተነስተው በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በውጭ የተመደቡት አቶ ስዩም መስፍን ሲሆኑ ሌላኛው በኢትዮጵያ የቻይና አምባሰደር “መስለው” እንዲሰሩ የተመደቡት አቶ አርከበ ዕቁባይ ናቸው። አርከበ በተለይም የኢንደስትሪ ፓርኮችንና ከተሞችን ለማስፋፋት በሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው እየሠሩ ሲሆን ሱፍያን እነዚህን ሁለት ሰዎች በማገዝ እሚገባውንና እሚወጣውን ገንዘብ መልክ ሲያስይዙ ቆይተዋል። ይህን ያስተዋለው የእነለማ መገርሣው ኦህዴድ፣ ለዓመታት ሳይነኩ የቆዩትን አቶ ሱፍያንን በመንቀል ድርጅታዊ ሽፋን ነሳቸው። እንዲያውም ከአንዳንድ የሆቴል ባለቤቶች ጋር ሆነው ፈጽመዋል የተባለውን ሙስና በማጋለጥ ለክስ አቀረባቸው። ይህን ያዩ የህወሃት ሰዎች ይብላኝ ለናንተ እንጂ እኛስ ጥለን አንጥላቸውም ያሉ መሰሉ። የኢፌዴሪ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፍያን አህመድ ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በእጩነት እንዲቀርቡ ተደረገ። በኦህዴድ ሰዎች ከኢትዮጵያ ካዝና የተነቀሉት ሰው የአፍሪካን ባንክ እየመዘበሩ እንዲያበድሩ ታጩ። ባንኩ ግን አልተቀበላቸውም። ስለዚህ ኦህዴዶቹ ህወሃቶችን አፋጠጧቸው ሲባል እንደሚወራባቸው ለሥልጣን ፍለጋ ያደረጉት ይሆን ወይስ የምዝበራው መጠን ከልክ እያለፈ መምጣቱን ለማመልካት ይሆን? ሱፍያን አህመድስ እንደወጡ ይቀሩ ይሆን ወይስ እንደተመለደው ከደሙ ንጹህ ነኝ ብለው የካዝናውን ሚስጥር ያጫውቱን ይሆን?
እንደወጡ የመቅረቱ ነገር ግን የኦህዴዶች እጣ ብቻ መሆኑ ይገርማል። አገር ውስጥ ያፈነገጡት ይሞታሉ የወጡትም እንደወጡ ይቀራሉ። ስመጥሩ ጸሐፊ ስዩም ተሾመ እንደጻፈው የኦሮምያ ፕሬዚዳንቶች አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ (ሞተዋል)፣ አቶ ሀሰን ዓሊ እና አቶ ጁነዲን ሳዶ አገር ጥለው ወጥተዋል። የቀድሞዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የነበሩት ወ/ሮ አልማዝ መኮ’ን ጨምሮ እንደ ዮናታን ዲቢሣና ድርባ ሀርቆ ያሉ የቀድሞ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችም ሀገር ጥለው ኮብልለዋል። ስዩም እንደሚለው ፣ ዶ/ር አብይና ለማ ችግር የበረታባቸው እንደሌሎቹ ሸሽተን አንወጣም ብለው እዚያው በመጋፈጣቸው ይሆን? ለነገሩ እንኳን ኦህዴዶቹ ይህን መሰል ሀሳብ እያነሳ እዚያው አገር ውስጥ የተጋፈጠው ጸሐፊው ስዩም ራሱ የት ደርሷል?
በነገራችን ላይ የሙስና ነገር ከተነሳ፣ ብአዴኖቹ አሁን በእስር ላይ እሚገኙት ፣ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ መላኩ ፈንታ እንዲፈቱላቸው መጠየቃቸው ተሰምቷል። ህወሃቶችም የተስማሙ ሲሆን አቶ መላኩ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈቱ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው። ኦህዴዶቹም ቢሆን ለቄሮዎች ምስጋና ይግባቸውና ሌሎችን ማሳሰር ጀመሩ እንጂ በርካቶችን አስፈትተዋል። የጀመሩትን ገፍተውበት ኢትዮጵያን ከታሰረችበት ቢያስፈቱ ደግሞ የበለጠ በሆነ ነበር።