>

የባህርዳሩ ማዕከላዊ (አባይ ዘውዱ)

ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ለምን ወፍ ይሏታል?ያው እንደለመደባቸው ዶሮ ወይም ዥግራ ብለው መብላት ነው እንጅ!
የባህርዳር 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ማለት በበርካታ ወጣት የዛሬ ሀገር ተረካቢዎች ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፀምበት አስቀያሚ ማጎሪያ ነው ።
በ2007 ዓ•ም ከ9ኛ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ የአደራ እስረኞች ተብለን በፀረ ሽብር ግብረ ሀይሉ በፌደራል ፖሊስ እየተጠበቅን ምርመራ በሚል ስም የበቀል እርምጃ የተወሰደብን “ሳንገድል እናሰቃያቹሃለን ተነቅቶባቹሃል”እየተባልን ያለ ስማችን ስም ያለ ድርጊት ድርጊት እየተሰጠን ዋጋ የከፈልነበት ቦታ ነው ።
የተወለድንበት የአማራ ብሄር ሳይቀር እየተጠቀሰልን ተደብድበናል ።ማተቤን የበጠሱበት ፣እግሬን ግድግዳ ላይ ተደግፈው ከሲሚንቶ ላይ የረገጡበት ፣በአጠቃላይ በአካልም ሆነ በሰነ ልቦናና በሞራል የበላይነት እንዳላቸው ለማሳየት የተሞከረበት ማጎሪያ ቦታ ነው ።
በተጨማሪም ከጎጃም ፍኖተ-ሰላም አካባቢ ታፍነው የመጡት እነ ዘሪሁን በሬ እና አወቀ ሞኝ ሆዴ ከባድ ዋጋ የከፈሉበት በብልት ላይ የሞላ ሀይላንድ ውሃ በማሰር እየጎተቱ የተሳለቁበት የእኛ ቤተ ሙከራ የእኛ ቤተ መከራ ።ባልተጣራ መረጃ አሉባልታን አጋልጡ በማለት ደም በደም በማድረግ ራሳችን ስተን በጨለማ እየተጎተትን የምንመለስበት ግፍ የማይሰለቻቸው ሰዎች በስቃይ/በጣረሞት ድምፅ የሚደሰቱና የሚዝናኑ የስርዓት አሽከሮች የህዝብ ባለደሞች የነበሩበት ቦታ ነው ።
ጠዋት እና ማታ 12 ስዓት ብቻ ለሽንት መውጣት የሚፈቀድበት የአንድ ወንድማችን ቆዳው በድብደባ ተገፎ ነጭ ሆኖ ያየንበት በውጭ ሳይሆን በውስጥ ደም ያነባንበት ቦታ ነው ።
ጣናና አባይ እፊታችን ላይ እያየነው ለ42 ቀናት ያክል ሻወር የተከለከልነበት አዲስ አበባ ማዕከላዊ ስንመጣ የቆሸሸ ሰውነታችንና ልብሳችን ያየ ወገን ሀገራችን ወደየት አቅጣጫ ለመውሰድ የፈለጉ አካላት ናቸው ይህን አይነት አረመኔያዊ ተግባር የሚፈፅሙ በማለት አስተዛዝነውናል _መቀየሪያ ልብስ ሰጥተውናል ።
ማስታወስ አልፈልግም ነበር ግን ከሰሞኑ ህጋዊ አማራን የሚወክል ፓርቲ ለመመስረት ወደ ባ/ዳር ያቀኑ 19 የአማራ ወጣት ሙህራን በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባ/ዳር 9ኛ ፖሊስ ጣቢያ መግባታቸውን በመስማቴ ነው የተዘጋውን ፋይል በትንሹም ቢሆን ገርበብ ለማድረግ የፈለኩት ።
አሁን አሁን ችግር እየበዛ ነው ይብዛ ግድ የለም መፍትሄው መወለዱ አይቀርም ።
ችግር የመፍትሄ እናት መሆኗን ለማረጋገጥ ይረዳናል!!!
Filed in: Amharic