>

ተስፋና ስጋት በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሹመት (ሳዲቅ አህመድ)

“ከቃለ-መሓላ በሗላ ተራምደው ወደ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት የሚገቡበት ቀይ ምንጣፍ በመላው አገሪቱ የፈሰሰው የሰማእታት ደም መሆኑ መዘንጋት የለበትም!”
ልክ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ሲሞቱ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ የነበረው ተስፋ አሁን ናኝቷል። ጠቅላዩ ቢሞቱም ተጠቅላዩ ሐይለማሪያም መጡና ሐይል-አልባ መሆናቸውን አሳዩ። የመለስ ሞት በዙፋኑ ላይ ያፈናጠጣቸው ሐይለማሪያም ደሳለኝ ፈልገውትም ይሁን በህወሃት አለቆቻቸው ታዘው እነደሆነ ዉሉ ባለየ መልኩ «ስራዬን በገዛ ፈቃዴ ለቅቅያለሁ» አሉ። ሁናቴው በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የተከሰተ ተብሎ ቢወደስም፤ በዙፋኑ ላይ ለመፈናጠጥም ይሁን ለመንጠልጠል ይደረግ የነበረው ሙከራ ቀላል አልነበረም።
ዶክተር አቢይ አህመድን አስወንጭፎ አራት ኪሎ ለማስገባት የተቀናጀ የበይነመረብ ዘመቻ ሲጀመር ለማስተዋል ችዬ ነበር። ጉዳዩን መሬት ላይ ያሉ ምንጮች እንዴት እየተከታተሉት እንደሆነ ስጠይቅ «ዶክተሩ አራት ኪሎ እንደሚገቡ ከሶስት ወራት በፊት (አሁን አራት ወር ሞልቶታል) ጥረት እንዳለ እናዉቅ ነበር» የሚል ምላሽ አገኘሁ። ዶከተር አቢይ አህመድ በግለሰብ ደረጃ ያላቸው ብቃት ሚዛን የሚደፋ ቢሆንም፤ ከበስተጀርባቸው የሚኖረውን ሐይል ተቋቁመው እንደምን የተሳካላት ጠቅላይ ሚኒስቴር ይሆናሉ? የሚለው ሐሳብ ጉዳዩን በጥንቃቄ እንድመለከተው የሚያደርግ ነው።
አገራዊ ተግዳሮት
ዶክተር አቢይ አሀመድ በህወሃት መዳፍ ስር ያለውን የመከላከያ ሰራዊት፣የደህንነት መዋቅር፣የመዋእለንዋይ ፍሰትና አቅም፣ የመገናኛ ብዙሗን በህወሃት ቁጥጥር ስር መሆን፣የተንሰራፋዉን የአንድ ብሔር የበላይነት አሸንፈው ብሔራዊ መግባባትን ይፈጥራሉን? ለቀጣዩ ምርጫ የሚደርስ የተዋጣለት የሽግግር መንግስትን ማዋቀር ይችላሉን? መሰል ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ ተፈትሸዋልን? ደረጃ በደረጃ ሒደቱ ደረጃ በደረጃ ሳይቃኝ፤ የስርዓት ለዉጥ ሳይሆን የግለሰብ ለዉጥ በመምጣቱ፤ ከመጠን ያለፈ ፈንጠዚያና ተስፋ (expectation) መኖሩን በጥንቃቄ ልንመለከተው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ረጃጅም የውጭ እጆች
ዶክተር አቢይን ለማስወንጨፍ የውጭ ሐይል አሰፍስፏል። ምሁሩ ፖለቲከኛ ጥምር የዘርና የእምነት ማንነት ያላቸው በመሆናቸው እርሳቸውን «ኢትዮጵያዊ ኦባማ» አስመስሎ ለማስረጽ የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። አፍሪካን በቅኝ በመግዛት፣በተለያዩ የአለም ክፍሎች እምነት አዘል በሆነ ተልእኮ በስልጣን ማማ ላይ በወጡ አገዛዞችና አመራሮችን በመጠቀም፣በአለማችን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ለዉጦች ላይ በመጠቅለል ጥቅምን ለማስረጽ ከሚጥረው የዉጭ ሐይል የአገርን ሉዓላዊነት እንደምን መጠበቅ ይቻላል? በዚህ ረገድ የመቶ ሚሊዮን ህዝብ መሪ መሆን ከባድ መሆኑ አሌ-አይባልምና የዶክተር አቢይ ፈተና ከባድ ነው።
መለስ የጀመሩት የዉጭ ሐይልን የማስገባት ሴራ የቀድሞው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ዶክተር ሺፈራው ተክለማርያም ለማስፈጸም መጣራቸውን ልብ ይሏል።ከቴክሳስ እስከ ኮሎራዶ ከዚያም እስከ አዉሮፓ ትላልቅ ከተሞች ያሉ ልዩ ጥቅም አስከባሪ ሐይላት (special interest groups) ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘልቀው ለመግባትና ጥቅማቸውን ለማስከበር እምነትን መሰረት ያደረጉ ረጃጅም እጆቻቸውን መዘርጋታቸው አይቀርም።የዉጭ እጆች ጥቅምን ለማስከበር ሲዘረጉ የዜጎች ህልዉናና ሰላም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ መከላከሉ ተገቢ ነዉና የዶክተር አቢይ ታሪካዊ ሚና በአይነ-ቁራኛ የሚጠበቅ ነው።
ሹመቱ በህዝብ ትግል የመጣ ነው
ዶከተር አቢይ ዛሬ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት እንዲገቡ ላለፉት ስድስት አመታት አያሌ መስዋእትነት ተከፍሏል።ህዝቡ የከፈለው መስዋእትነት በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ቡድን እንዲፈጠር አድርጓል።ከለማ ቡድን መካከል ዶክተር አቢይ የህዝብን አደራ የመሽከም ሐላፊነት ተጥሎባቸው ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ያለ ኢትዮጵያዉያን ሙስሊሞች «የድምጻችን ይሰማ» ትግል ዶክተር አቢይ ያሉበት ደረጃ ላይ አልደረሱም።ያለ ሰማያዊና አንድነት ፓርቲ የዉስጥና የጎዳና ላይ ሰላማዊ ትግል ዛሬ ዶክተር አቢይን ባላወቅን ነበር። በጎንደርና በጎጃም ያሉ ኢትዮጵያዉያን ለመሰዋእትነት ተዘጋጅተው አደባባይ ባይወጡና በስርዓቱ ላይ ባያምጹ ኖሮ ዶክተር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን ባልቻሉ ነበር።አገር አንቀጥቅጥና ህወሃትን የሚነቀንቅ የቄሮ ትግል ባይኖር ኖሮ ዶክተር አቢይ ወደ አራት ኪሎ ባላቀኑ ነበር። ህወሃት መራሹን መንግስት በጦር እንጥላለን ብለው ጫካ የገቡ ኢትዮጵያዉያን መኖራቸው ለዶከተር አብይ መከሰት ምክንያት አልሆነም ማለት አይቻልም።
ባህር ማዶ ያለው ኢትዮጵያዊና ትዉልደ-ኢትዮጵያዊ ግዜውንና ገንዘቡን ሰጥቷል።ሚዲያዎች እየታፈኑና ከሳተላይት እንዲወርዱ እየተደረገ ለዉጥን ለማምጣት ሰርተዋል።ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና ለዉጥ ፈላጊዎች በአሜሪካና በአዉሮፓ ጎዳኖች ላይ በጸሃይ-በሐሩር-በበረዶ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ብዙ ጥረዋል።አያሌ ስብሰባዎች፣የግብንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች፣የማግባባት (lobbying) እና በህወሃት መራሹ ቡድን ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና የማሳደር ጥረቶች ተደርገዋል።
ተስፋ የተጣለበትን ድህረ-የስርዓት ለዉጥ ለማየት በዝጉም ይሁን በክፍቱ የህወሃት እስርቤቶች ብዙዎች ታስረዋል፣ተገርፈዋል፣ሴቶችም-ወንዶችም በጾታዊ ጥቃት ቶርቸር ተደርገዋል፣ነፍስን ለማዳን አገርን ጥለው የጠፉ በርካታ ናቸው።ከሁሉም በላይ መተኪያ የሌለውን ህይወት በመስጠት መስዋእት የሆኑ ብዙ አገር ወዳድ ዜጎች የሚዘነጉ አይሆኑም።አጋዚ በሚባለው የህወሃት ቅልብ ጦር ልጅ ተገድሎባቸው ለምድራዊ ስቃይ የተጋለጡ እናቶች፣አባቶች፣እህቶች፣ወንድሞች፣ቤተሰቦች፣ወዳጅ-ዘመዶችና ጎረቤቶች ብዙ ናቸው። ዶክተር አቢይ ወደ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ሲያመሩ በክብር ቀይ ምንጣፍ ሳይሆን ህወሃት ለ40 አመታት ሲያፈሰው በነበረው የሰማእታት ደም ላይ መሆኑ አትኩሮት ያሻዋል።
የክብር ቀይ ምንጣፉ የሰማእታት ደም ነው
ከሚሰማው የደስታ ድምጽ ባሽገር ስጋት አለ።ስጋቱ በብዙዎች ዘንድ እየተዥጎደጎደ ባለው የምስራች ላይ ሟርትን ለመቸለስ አይደለም።የዶከተር አቢይ መመረጥን ወደ ሌላ እርከን አሳድጎ ለዉጡ የሰው ለዉጥ ሳይሆን የስርዓት ለዉጥ እንዲሆን መትጋት አለብን የሚል ምልከታ (reservation) ዉስጥን በእጅጉ ይሞግታል ።ስለዚህ ያለውን ነባራዊ ሁናቴ በሚገባ አጢነን ህዝባችን የሚሻውን ወሳኝ ለውጥ ከግብ እናድርስ የሚል ጥሪ ሳቀርብ ዶክተር አቢይ ከቃለ-መሓላ በሗላ ተራምደው ወደ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት የሚገቡበት ቀይ ምንጣፍ በመላው አገሪቱ የፈሰሰው የሰማእታት ደም መሆኑ መዘንጋት የለበትምና ልብ ያለው ልብ ይበል።
Filed in: Amharic