>
5:13 pm - Tuesday April 19, 0140

ይድረስ ለአዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር (ጠ/ሚ?) አብይ አህመድ! [በላይ ማናዬ (ጋዜጠኛ)]

በመጀመሪያ የድርጅትዎ ሊቀመንበር ሆነው በመመረጥዎ እንኳን ደስ አለዎት! በተጨማሪም በድርጅትዎ አሰራር መሰረት የሀገሪቱ መሪ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። ለዚህም በድጋሜ እንኳን ደስ አለዎት!
ክቡር አቶ አብይ፣ በአዲሱ ኃላፊነትዎ ብዙ ፈተና ውስጥ ያለችን ሀገር መረከብዎን የሚያጡት ሀቅ አይደለም። እሳት ላይ እንደተጣዱ ነው የምቆጥረው። ይህን ደብዳቤ የምፅፍልዎት ከበርካታ ውሳኔ የሚፈልጉ አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል የእርስዎን አጣዳፊ ውሳኔ ከሚሹት አንዱን በአስቸኳይ እልባት ይሰጡት ዘንድ ለመጠየቅ ነው።
ያለፈው መጋቢት 15 እና 16/2010 እሁድና ቅዳሜ በአዲስ አበባ እና ባህር ዳር ከተሞች በቅርቡ ከአመታት እስር በኋላ የተፈቱትን ጨምሮ በርካቶች ለእስር ተዳርገዋል። ከእነዚህም መካከል 11 ሰዎች በአዲስ አበባ፣ 19 ሰዎች ደግሞ በባህር ዳር በአንድ ቀን ልዩነት ታፍሰው በግፍ እስር ቤት ተወርውረዋል። ሌሎች ብዙዎችም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በአፋኙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ታጉረዋል።
ክቡር አቶ አብይ፣ አሁን የምናገርላቸው እና በቅርብ የታሰሩት ሰዎች በተለያዬ ሙያ ላይ ሀገሪቱን የሚያገለግሉና ለተሻለ ለውጥ የሚተጉ ሰላማዊ ዜጎች ስለመሆናቸው ብዙዎችን በቅርበት ስለማውቃቸው ምስክርነቴን ልሰጥላቸው እችላለሁ። ስለማን እየተናገርሁ እንደሆነ ለመረዳት ቀጥሎ ያለውን ዝርዝራቸውን በጥሞና እንዲመለከቱልኝ እጠይቃለሁ፣

አዲስ አበባ የታሰሩት

1) ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
2)ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
3) አቶ አንዱዓለም አራጌ (ፖለቲከኛ)
4) አቶ አዲሱ ጌታነህ (የህግ ባለሙያ)
5) ጦማሪ ዘላለም ወርቅ አገኘሁ
6) ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን
7) ጦማሪና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ኃይሉ
8) ወ/ት ወይንሸት ሞላ (የፖለቲካ ፓርቲ አባል)
9) አቶ ይድነቃቸው አዲስ (የፖለቲካ ፓርቲ አባል)
10) አቶ ስንታየሁ ቸኮል
11) አቶ ተፈራ ተስፋዬ

ባህር ዳር ላይ የታሰሩ፣

12) ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ (ባ/ዳር ዩንቨርሲቲ መምህርና የጣና ደህንነትና የአካባቢ ጥበቃ ማህበር ፕሬዚደንት እና ተመራማሪ፣ ረዳት ፕሮፌሰር)
13) ጋሻው መርሻ (የአንጸባቂው ኮከብ መጽኃፍ ከታቢ፤ አዲስ አበባ በማስተማር ሙያ ላይ ይገኛል))
14) የሱፍ ኢብራሂም (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረና በአሁንኑ ወቅት ጠበቃ)
15) ተመስገን ተሰማ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር፤የወሎ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መስራች፣ ረዳት ፕሮፊሰር እና አማራ ነን የሚለው መዝሙርም ገጣሚ)
16) በለጠ ሞላ ( ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር)
17) ጋዜጠኛ ንጋቱ አስረስ (የአማራ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ(አርታኢ)፤ከ1997 እስከ 1999 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዜዳት)
18) ጋዜጠኛ በለጠ ካሳ (የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ)
19) አቶ ሲሳይ አልታሰብ( ከአአዩ ሲቪል ኢንጅነር ምሩቅ)
20) አቶ ዳንኤል አበባው (ጣናን ከእቦጭ አረም ለመታደግ እየተጋ ያለ ወጣት)
21) አቶ መንግስቴ ተገኔ
22) አቶ ቦጋለ አራጌ
23) አቶ ካሱ ኃይሉ (የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪ)
24) አቶ ተሰማ ካሳሁን
25) አቶ ድርሳን ብርሃኔ
26) አቶ በሪሁን አሰፋ
27) አቶ ፍቅሩ ካሳው
28) አዲሱ መለሰ (ደ/ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር)
29) አቶ ተመስገን ብርሃኑ

ክቡር አቶ አብይ፣ ከላይ የዘረዘርኋቸው ለማሳያነት እንዲሆንዎ ጠቀስሁ እንጂ በተለያዩ እስር ቤቶች በስመ ሽብር ክስ የታጎሩትን ዘንግቼ አይደለም። እርስዎም የዋልድባ መነኮሳትን እና ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ በርካታ ንፁሃን ማሩን በእስር ላይ እንደሚገኙ የሚያውቁት ነው። የብዙዎች የእስር መነሻ መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ በመጠየቃቸው ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ ለማህበራዊ ጉዳይ በጋራ መገኘታቸው ነው። መቼስ ይሄ አሳፋሪ ድርጊት እየተፈፀ ስለመሆኑ አላውቅም እንደማይሉ ተስፋ አለኝ።
ክቡር አቶ አብይ፣ ይህን ደብዳቤ የምፅፍልዎ በዋናነት በአፋጣኝ እነዚህን አሳፋሪ ጉዳዮች አይተው መፍትሄ እንዲሰጡት ለመጠየቅ ነው። አሁን እርስዎ የኦህዴድ ሊቀመንበር ብቻ አይደሉም፣ የኢህአዴግም ሊቀመንበር ሆነዋል። ከመጪው ቅዳሜ ጀምሮ ደግሞ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ይሆናሉ። ይህ ማለት ብዙ ኃላፊነት፣ ትልቅ ግዴታ አለበዎት ማለት ነው።
ክቡር አቶ አብይ፣ አንድ ነገር ግልፅ ለማድረግ እፈልጋለሁ። ይኸውም እርስዎ ብዙ ሰዎች የሀገራችንን ምስቅልቅል ሁኔታ ተገንዝበው ማሻሻያ እንደሚያደርጉ ተስፋ አላቸው። በዚህም የኢህአዴግ ሊቀመንበር፣ አልፎም ጠ/ሚ ሆነው መመረጥዎ ያስደሰታቸው አሉ። ይህ ማለት ግን እርስዎ በህዝብ የተመረጡ ነዎት ማለት አይደለም። እርስዎ ድርጂትዎ እንጂ ህዝብ በነፃ ፍቃዱ አልመረጥዎትም። ምናልባት የምርጫ ስርዓቱን አመቻችተው ወደ ምርጫ መድረኩ ከመጡ ህዝብ ይመርጥዎት እንደሆን የምናየው ይሆናል።
ክቡር አቶ አብይ፣ በመጀመሪያ አዲሱ ኃላፊነትዎ አፋኙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሰርዙልን፣ የታሰሩትን የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ውሳኔ እንዲሰጡ በማክበር እጠይቃለሁ። ይህን ውሳኔ ሳይውሉ ሳያድሩ ቢወስኑ በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገቡ የማሻሻዬ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያለዎትን ፍቃደኝነትና ዝግጁነት ሊያመለክት ስለሚችል ውሳኔዎን በቶሎ እንዲያሳዩን ያስፈልጋል።
እኔም ሆንን በርካቶች ከኢህአዴግ ውስጥ ለለውጥ ፍላጎት ያለዎት ነዎት ብለን የድርጅትዎ መሪ በመሆንዎ ድጋፍ ባንሰጥ እንኳ በውስጣችን “እስኪ እንያቸው” በሚል መመረጥዎን በተስፋ ተቀብለናል። ከዚህ ቀን በኋላ እርስዎ የሀገር ኃላፊነት ተረክበዋል። ይህ ማለት ከዚህ በኋላ በግሌ የእርስዎ ተቺ፣ ጎደለ የምለውን እንዲሞሉ አሳሳቢ፣ ሲያጠፉ ወቃሽ ነኝ። ወንጀል ሲፈፀም ተጠያቂ እንዲሆኑ ወትዋችም ነኝ። ቅን ከሆኑ እንዲህ ያሉ ድምፆችን ሰምተው በጎ እርምጃ ይወስዳሉ። አልያ ግን እንደቀደሙት የድርጂትዎ መሪዎች በመፃፌ፣ በመተቸቴ እስር ቤት ያግዙኝ ይሆናል። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ ዛሬ የታሰሩትን እንዲፈቱ ማሳሰቤ ከንቱ ነው ማለት ነው። እንዲያ ከሆነ ተስፋችንን አደበዘዙት ማለት ነው። በተቃራኒው ደግሞ፣ እንዲህ ካደረጉ መውደቂያ ጊዜዎን አፋጠኑ ማለት ነው።
ክቡር አቶ አብይ፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ እንደቀደመው እንደማይቀጥል እርግጠኛ መሆን ይቻላል። እንደስከዛሬው ህዝብ ረግጦ መግዛት እንደማይቻል እንዳይረሱ ለማስታወስ እፈልጋለሁ። ህዝብ አሁን የለውጥ ፍላጎቱ ንሯል። ለዚያ ነው እሳት ላይ ነው የተጣዱት ያልሁዎት! አሁን የፖለቲካ እስረኞቹን ካልፈቱ ህዝብ ራሱ ያስፈታቸዋል፣ አዎ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ህዝብ ያስፈታቸዋል። ያኔ እርስዎም በስልጣን አይኖሩም! ስለዚህም ፈጥነው እስረኞችን ይፈቱ ዘንድ፣ ለለውጥ ዝግጁ መሆንዎን ምልክት ያሳዩ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።

ከማክበር ጋር

በላይ ማናዬ (ጋዜጠኛ)

Filed in: Amharic