>

ህወሃት ሃይለማሪያም የተባለ ፈረሷን ሸኝታ ሽፈራዉ የተባለ አጋሰሷን ልትጭንብን አቆብቁባ ነበር!!! (ስንትአየሁ ባይኔ)

አስተማማኝ የመረጃ ምንጮች በዘገቡት መሰረት አቶ ደመቀ መኮነን በሞተ ሰዓት ለሊቀመንበርነት እንዳማይወዳደር በማሳወቅ ለዶ/ር አብይ አህመድ መንገዱን ጠርጎለታል፡፡ ይህ  ዉሳኔ የአቶ ደመቀ መኮነን የግል ዉሳኔ ይሆናል ብሎ ማሰብ መቼም ቢሆን አይቻልም፡፡ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ድርጅቱ ተወዳደር ብቻ ሳይሆን ሙት ካለዉ ሊሞት የግድ ነዉ፡፡
ያለ ምን ጥርጥር አቶ ደመቀ ለዉድድር ቀርቦ ቢሆን ኖሮ የድርጅት ስሜት ተጨምሮበት አብዛኛዉን የብአዴን አመራር ድምጽ ማግኘት በቻለ ነበር፡፡ ከህወሃት ደግ ነዉ በሚል ስሜት፣ ከደኢህዴንም በምከትልነት ብዙ ጊዜ የሰራ በሚል አዘኔታ የተወሰነ ድምጽ ማግኘት በቻለ ነበር፡፡ ኦህዴድ ከመጀመሪያዉም እኛ ካልሆንን ሞተን እንገኛለን ብለዉ ስለገቡ ከእነሱ ድምጽ ማግኘት የማይታሰብ ነዉ፡፡
በዚህ መሰረት ደመቀ ለዉድድር ቢቀርብ የብአዴን ድምጽ ለሁለት ይከፈላል ማለት ነዉ፡፡ አብዛኛዉ ለራሱ ለአቶ ደመቀ፣ የማይናቅ ቁጥር ያለዉ ደግሞ ለዶ/ር አብይ፡፡ የኦህዴድ ተሰብሳቢዎች ከዶ/ር አብይ በቀር ለማንም ድምጽ እንደማይሰጡት ሁሉ የብአዴን ተሰብሳቢዎችም ለዶ/ር  ደብረጽዮንና ለአቶ ሺፈራዉ ድምጽ ይሰጣሉ የሚል ግምት በጭራሽ የለኝም፡፡
ስለዚህ የአቶ ደመቀ በሞተ ስዓት ማፈግፈግ በተግባር የጠቀመዉ እንደ ግል ለዶ/ር አብይና ለራሱ ለአቶ ደመቀ ሲሆን እንደ ድርጅትም ለኦህዴድና ለብአዴን ነዉ፡፡ ይህም የተጀመረዉን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የፓርቲ ለፓርቲ ጭምር በማድረግ ተደገመ ማለት ነዉ፡፡ አቶ ደመቀ ቢወዳድርም ሁለተኛ ከመወጣት ሊዘል አይችልም ነበር፡፡ አራቱም ተወዳዳሪዎች የተወሰነ ድምጽ ሲወስዱ አንደኛ የሚሆነዉ ዶ/ር አብይ ለመመረጥ የሚያበቃዉን ድምጽ ያጣል፡፡
ይህም ለሌላ ዙር ድምጽ መስጠት ከመዳረግም አልፎ በብአዴንና በኦህዴድ መካከል የተጀመረዉን ግንኙነት ማሻከሩ የማይቀር ነዉ፡፡ በመሆኑም ሁለተኛ ወጥቶ ለዶ/ር አብይ ሊሰጥ ይችል የነበረን ድምጽ ከመሻማት ከነክብሩ አልፈልግም ማለት የፖለቲካ ጥበብ ነዉ፡፡
እንግዲህ የአቶ ደመቀ አለመኖር ነዉ አቶ ሺፈራዉን ሁለተኛ እንዲወጣ ያደረገዉ፡፡ ያለ ምንም ጥርጥር አቶ ሺፈራዉ ያገኘዉ ድምጽ ከራሱ ድርጅት የተወሰነ አብዛኛዉን ግን ከህወሃት ነዉ፡፡ ህወሃት አቶ ሃይለማሪያም የተባለ ፈረሷን ሸኝታ አቶ ሽፈራዉ የተባለ አጋሰሷን ልትጭንብን አቆብቁባ የነበረ ቢሆንም ዕድሜ ለኦህዴድና ለብአዴን ጥምረት እንዲሁም ለተወሰኑት የደኢህዴን አመራሮች ከሽፎባታል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን ያገኘዉ ሁለት ድምጽ የሚናገረዉ ነገር የህወሃት ሞት በኢህአዴግ ምክርት ቤት ደረጃም መፈጸሙን ነዉ፡፡ በእዉነት ይህ ትልቅ የፖለቲካ ሞት ነዉ፡፡ መቸም ህወሃት ቤት ይሉኝታ ስለሌለ እንጅ ሁኔታዉን ገምቶ ይቅርብኝ ማለት ይሻለዉ ነበር፡፡ የአገራችን ህዝብ ህወሃትን ላለፉት 27 አመታት የተሸከመዉ ትከሻየ ተላልጦ እየተዘጠዘ አላስቀምጥ አላስተኛ አለኝ በሚልበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ከመወዳደር በላይ ድንቁርና የለም፡፡
ለማንኛዉም እዉነቱ ይህ ቢሆንም ብአዴን ዶ/ር አብይን የሚገዳደር መሪ መፍጠር ባለመቻሉ ሃፍረት ሊሰማዉ ይገባል፡፡ አዳዲስና ወጣት ሙህራንን ወደ ድርጅቱ በስፋት በማስገባት ከአስርና ከአስራ አምስት አመታት በሗላ (አንተ ወያኔ ስለሚቀጥሉት አስርና አስራ አምስት አመታት ታስባለህ እንዴ ተብሎ ብዙ ዉርጅብኝ እንደሚወርድብኝ ይገባኛል) ከራሱ የወጣ  ጠቅላይ ሚኒስትር ለማየት አሁኑኑ ስራ መጀመር አለበት፡፡
ዕድል በማጣት ይሁን እድላቸዉን መጠቀም ባለመቻላቸዉ ባይታወቅም በከፍተኛ ትምህርት መዝለቅ የተሳናቸዉ፣ ከተማ የሚያስገባኝ ባገኘሁ እንጅ የማንም ባሪያ ሆኜ ባገለግልኩ ነበር የሚል ስሜት ያሸነፋቸዉ፣ ኑሮ የቸገራቸዉ የገጠር መምህራንን ብቻ ወደ ድርጅቱ እያስገባ ራሱን በአመራር ድርቀት ማስመታት የለበትም፡፡
እርግጠኛ ነኝ  አሁን ላይ አቶ አባዱላ ገመዳ ወጣት ሙህራንን በስፋት በማስገባት አስገብቶም የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ አሁን ላይ ፍሬዉን ሲመለከት ከፍተኛ ኩራት ሊሰማዉ የሚችል ሲሆን ብአዴኖች ግን ሃፍረት እንደሚሳማቸዉ፡፡
እንግዲህ የሆነዉ ሆኗልና ዶ/ር አብይ ህገመንግስታዊ ስልጣናቸዉን በትክክል እንዳይወጡ ሰቅዘዉ የሚይዟቸዉን ተቋማት ለይተዉ መልክ ማስያዝ ይገባቸዋል፡፡ ካልሆነ ግን ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎም አቅመዳ መሆኑ የማይቀር ነዉ፡፡ ሌሎች ተራማጅ ዉሳኔዎችን ተግባራዊ በማድረግም ልዩነት ፈጣሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸዉን በተግባር ማሳየት አለባቸዉ፡፡ በአስቸኳይ መፍትሄ የሚሹትን በቀናት፣ በሳምንታትና በወራት ዉስጥ መፍታት፣ በሂደት የሚፈቱትን ደግሞ ግልጽ  የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጠዉ ወደፊት መራመድና ማራመድ  ይገባቸዋል፡፡
እንግዲህ ወደድሽም ጠላሽም ጠቅላይ ሚኒስትርሽ በአባቱ ኦሮሞ፣ በእናቱ አማራ ነዉ የሚባለዉ ዶ/ር  አብይ አህመድ ነዉ፡፡ አብይ የክርስቲያን ስም አህመድ ደግሞ የእሳላም ነዉ፡፡ በቋንቋም ሆነ በሃይማኖት ብዝሃነትን የያዘ ሰዉ መቸም ቢሆን ሚዛናዊ ለመሆን የቀረበ ይመስለኛል፡፡
Filed in: Amharic