እንኳን ደስ አለን፡፡ ቢያንስ በሁለት ምክንያት ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ዶ.ር አብይ በመመረጣቸውና በተመረጡበት መንገድ ደስ ሊለን ይገባል፡፡

ዶ.ር አብይ ከመመረጣቸው በላይ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ ተስፋ የተመረጡበት መንገድ ነው፡፡ እሳቸው ለ180 የኢህአዴግ አባላት በስልክና በሻይ ቡና በተላለፈ ማሳሰቢያ፤ ያለልዩነት በሙሉ ድምጽ አልተመረጡም፡፡ እሳቸው የተመረጡት ለህዝቦች መብትና ጥያቄ መመለስ የቀረበውን፣ የክልላቸውን ህዝብ ጥያቄ ጥያቄያቸው አድርገው፣ ከሁለት አመት በላይ ነግሶ ያለውን የህዝብ አመጽ ተከትለው ኢህአዴግን ፈትነው፣ አኦሄዲድና ብአዲን ጋር አሸንፈው በመውጣት ነው፡፡ ከእንግዲህ በኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ተመልሶ ፌዝና ለበጣ ለመሆን ተአምር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በጠመንጃ ስልጣን መያዝና ማስተዳደርን ዋና አማራጭ አድርጎ የሚያየው ‹‹ያ ትውልድ›› እንደነለማና አብይ ያሉ በህሊናቸው ከጠመንጃና እስርቤት ይልቅ እውቀትና መነጋገርን የያዙ ወጣት መሪዎች በየድርጅቱና የፖለቲካ ፓርቲው ስለሚተኩ (ይህ የግድ ነው) ዲሞክራሲው እየዳበረ የመሄድ ተስፋው ትልቅ ነውና ስለተስፋው መደሰት አይበዛም፡፡
ከሁሉም በላይ ለተገኘው የዲሞክራሲ ጭላንጭል በዋናነት መመስገን ያለባቸው እንደ ድርጅት ኦሄዲድና ብአዲን፣ እንደ ህዝብ ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ናቸው፡፡ የህዝብን ጥያቄ ይዞ የተነሳው አመጽ፣ በተለይ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ምክክር፣ ኢትዮጵያዊነትን ከተቀበረበት አዋራውን እፍፍ ብሎ ያስነሳና ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም መንገድ የቀደደ ነው፡፡
ጅምሩ ለፍሬ በቅቶ፣ . . . እየተገላመጡ የማይናገሩባት፣ በተናገሩት ለእስር የማይዳረጉባት ፣ በዲሞክራሲ የበለጸገች ሀገር ለልጆቻችን ለማውረስ እንደምንበቃ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡