((ተከታዩ ፅፍሁ የዶ/ር አብይ የስልጣንን ዘመን ከአማራ ህዝብ አንፃር በስሱ ለመዳሰስ ተሞክሯል።ሀሳቡ የግሌ እንጅ የአማራ ድርጅት ወይም ማህበር ወይም የሌላ አለመሆኑ ይሰመርበት።አረፍ እያላችሁ ጨርሱት))
((ዶ/ር አብይን ወንበሩ ይጎርብጥህ የሚል ምርቃት መርቁልኝ።ምክንያቱም ያ ወንበር መሪዎች ከአዳራሹ ውጭ እንዳይመለከቱ እያደረጋቸው ነውና ከጎረበጠው ባይሆን ለመናፈስ ወጣ ሲል እኛን ያየን ይሆናል በሚል ነው።))
ለ27 ዓመት ሙሉ ካለንበት የፖለቲካ ስርዓት አንፃር እየተመለከትን እያንዳንዳችን የሚመስለንን ሀሳብ እየሰነዘርን ነው።እኔም እንደ አንድ ዜጋ የሚሰማኝ የተወሳሰብ ስሜት ቢኖርም ለጊዜው ስሜቴን ገታ አድርጌ ወደፊት ስለሚሆነው ወይም መሆን ስላለበት ነገር ሀሳቤን ልሰንዝር።
ዶ/ር አብይ ምን ማድረግ ያስብ ይሆን?ምን ምቹ ሁኔተዎችስ አሉ? በሚል አምስት ነገሮችን አቀርባለው።
አንደኛው ጉዳይ የአንድነት ጉዳይ ነው።ዶ/ር አብይ ምንም እንኳን ኦሮሞነትን እንደ ቅድመ ሁኔታ ተጠቅሞ የምርጫ ቅስቀሳ የተደረገለት/የተደረገበት ሰው ቢሆንም ለምርጫ የቀረበበት ወቅት ግን በብሄር ፖለቲካ ጡዘት ላይ ያለችው የኢትዮጵያ ጉዳይ ገዥዎቿ በተወሰነ መልኩ አደጋውን የተገነዘቡበትና ሀገራዊ እሴት ላይ ማተኮር አለብን የሚል አቅጣጫ የያዙበት ወቅት ላይ ነን። ይህም ዶ/ሩ ከኦሮሙማ ብቻ አስተሳሰብ ወጥቶ አቃፊ እና ደጋፊ ሚናን እንዲጫወት ያስገድደዋል ብየ አስባለው።ይህ ስርዓቱ አሁን የሚፈልገው ነገር ይመስለኛል።ስለዚህ ዶ/ር አብይ ምንም አይነት አዋጅ ማውጣት ወይም ህግ ማሻሻል ሳያስፈልገው እዚህ ላይ ከሰራ እርሱም ሀገሪቱም ትጠቀማለች ብየ አስባለው።ይህንን #የሀገር_አንድነት_አጀንዳ በደንብ ካጦዘው እኛም እንደ አማራ ተጎጅ እንሆናለን ብየ አልገምትም።ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን እንደ ትግል መነሻ ያደረጉ አማራዎች እግር በእግር የአብይን እንቅስቃሴ ቅርብ ክትትል ማደረግ አለባቸው ባይ ነኝ።በኢትዮጵያዊነት ሽፋን የአማራው ጥያቄ እንዳይዳፈን ወጥረን መያዝ አለብን።
ዶ/ር አብይ ስለኢትዮጵያዊነት (ህግም አዋጅም ማፅደቅ ሳያስፈልገው ሲሰራ) ህወሃት ቢቃወመው እንኳን ስለኢትዮጵያ ሲወራ ነፍሱ የሚከንፈው ሁሉ በጠላቴ ጠላት ወዳጀ ነው ስሜት ከጎኑ ይሰለፋልና እዚህ ላይ ዶ/ሩ እንደሚሳካለት አልጠራጠርም።ይህ ጥሩ ወይም ምቹ ሁኔታ ነው።ይህንን ያደረገለት ወቅት እንጅ ስርዓቱ አይደለም።እናም አብይ እውነትም ብቃት ካለው ብቃቱን ተጠቅሞ፤ ስርዓቱን ሳይቃወም የወቅቱን ጥያቄና ፍላጎት ማሳካት የሚችል ይመስለኛል።
ሁለተኛው ጉዳይ አብይ ሊሰራ ይገባል/ይችላል ብየ የምጠብቀው ነገር በአማራ አካባቢ ለዘመናት ሲነሱ የቆዩና ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ የፌደራል ተቋማትን በር እያንኳኩ ያሉ #የማንነት እና #የወሰን ጥያቄዎችን መመለስ ነው።እነዚህን ጉዳዮች ለመመለስም የማስፈፀም ብቃት እንጅ የስርዓት ለውጥ ማደረግ ወይም ህግ ማርቀቅ አይጠይቅም።አቅም ያለው ሰው ከተገኘ ስርዓቱ እያለ መመለስ የሚችሉ ቀላል ጥያቄዎች ናቸው።የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት፣ የራያና መተከል ጥያቄዎች ህገ መንግስት ማሻሻል ሳያስፈልግ መመለስ ይችላሉ።ዶ/ር አብይ ይህንን ማደርግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ አለው።ይኸውም እርሱ ያለበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ “ህዝባዊ ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ ማግኘት አለባቸው” ይህ ካልሆነ ሀገር ትፈርራሳለች ብሎ አቅጣጫ አስቀጦለታል።ከዚህ ውስጥ የማስተር ፕላን ጉዳይና የወልቃይት ጉዳይ በስም ተጠቅሰው ተቀምጠዋል (የቅማንት ጉዳይ ቀድሞ በመመለሱ ታልፏል)።
እናም የአዲስ አበባ ጉዳይ የተጀመረ ሲሆን የወልቃይትና ሌሎች የአማራ ህዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ አላውቅም።ዶ/ር አብይ ህወሃት/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሰው ህይወት የተገበረባቸውና አሁንም የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው ያሉ ተግባራትን ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ከፈለገ የተደላደለ ምቹጌ ያገኘ ይመስለኛል።እንዳልኩት ይህንን ለማደረግ የሚጠይቀው ቀናነትና ቆራጥነት ብቻ ነው።ያለውን ህግ ማስከበር ብቻ።ወደ አማራ ለመካተት የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዳለ እርሱ የሚመራው ክልል ኦሮሚያም ደቡብም ላይ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ መልስ ማግኘቱ ለዚህ በቂ ምክንያት ነው።ከዚህ የወሰንና ማንነት ጋር ተያይዞ መመለስ ያለበት ሌላኛው መሰረታዊና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ በአሁኑ አደረጃጀት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ በግምት ከ11 እስከ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ አማራዎች ጉዳይ ነው።ይህንን ገዳይ ማብራራት የሚያስፈልግ አይመስለኝም።በአማራ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞ ወገኖቻችን አያያዝ ኦህዴዶች ምክንያት ድርደራውን አቁመው በቀናነትና በእኔነት ስሜት ተመልክተው በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ሊተገበሩት ይገባል።
ሶስተኛው ዶ/ር አብይ መፈፀም ይችላል ብየ የማምነው #እስረኞችን መፍታት ነው።ይህንን ጉዳይ ህወሃትም ራሱ በተደጋጋሚ ቃል የገባውና ሀይለማሪያምም የጀመረው ጉዳይ ስለሆነ ለዶ/ር አብይ አቀበት አይሆንበትም።ይህንን ለመተግበር አዋጅ፣መመሪያ፣ ህግ ማርቀቅ ወይም መከለስ አልያም መሰረዝ አይጠበቅበትም።ምልክቱ ቀድሞ ታይቷል።እንደ እነመላኩ ፈንታ፣አንዳርጋቸው ፅጌ፣ መቶ አለቃ ማስረሻ፣ ዶ/ር ማሩ ፍቅሩ፣አግባው ሰጠኝ፣ አባ ገብረማሪያምና ሌሎችም ያሉ ሰዎችን በጠቅላላው ንፁሃንን ለመፍታት የህወሃትን ይሁንታ ማግኘት ብቻ በቂ ነው።ህወሃት ደግሞ ቀድሞ ቃል የገባ በመሆኑ ቃሉን እንዲያከብር መጠየቅ እንዲሁም ሌሎች ብሄራዊ ድርጅቶችን ተጠቅሞ ጫና ማሳደር ብቻ ነው የሚጠይቀው።በዚህ ህወሃት የሚይዘው የሚጨብጠው በጠፋበትና አንዱን ከአንዱ ለማጣላት ሌት ተቀን በሚሰራበት ወቅት ለህወሃት የወልቃይትን እና ራያን ጉዳይ እንዲፈታ በጊዜ ገደብ ማስቀመጥ እንዲሁም ሌሎችን የአማራ ጥያቄዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ማደረግ የአብይ ቀላሉ መፈተኛ ይሆናልም ባይ ነኝ።
አራተኛው ዶ/ሩ መጠነኛ የህግ ማውጣት ስራ ሊጠይቀው የሚችለው እና መጀመሩን የሰማውት የአዲስ አበባ #ማስተር_ፕላን ጉዳይ ነው።ዶ/ር አብይ እዚህ ላይ ቅርብ ክትትልና ድጋፍ የሚያስፈልገው ሲሆን የአዲስ አበባ ጉዳይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ እንዲፈታ ማድረግን መርህ ማደረግ ነውና።እዚህ ላይ የአብይ የራሱ ኦሮሙማ አስተሳሰብ፣ የኦሮሞው ህዝብ ፍላጎት እና የመስተዳደሩ ከንቲባ ከኦሮሞ መሆን ጋር ተዳምሮ ብቃቱን ሊፈትነው እንደሚችል ብገምትም የአዲስ አበባ መስተዳደርን ህዝብ ፍላጎት ግን ቅድሚያ የሚሰጥ መርህን ተከትሎ መፍታት እንዳለበት አምናለው።እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ የአዲስ አበባን ጉዳይ በአዲስ አበባ ነዋሪ ህዝብ መነፀር ብቻ ተመልክቶ መፍታት ካልተቻለ እና የሶስተኛ ወገንን (ለምሳሌ የኦሮሚያ ክልልን ጫፍ የወጣ እና በአዲስ አበባ ነዋሪዎችና መስራቾች ጉሮሮ ላይ የቆመ ፍላጎት) ፍላጎት መሰረት ያደረገ ውሳኔ ላይ የሚሄድ ከሆነ የዶ/ሩ ጉዳይ እዚህ ላይ የሚያበቃ ይመስለኛል። የፖለቲካ ብስለትህ ደካማ ነው የሚል ተንታኝ ካልመጣ በስተቀር ዶ/ር አብይ ከላይ ባስቀመጥኳቸው ጉዳዮች ተነሳስቶ የአዲስ አበባን ህዝብ ፍላጎት በትንሹም ቢሆን በተጋፋ መልኩ ከተጓዘ ከአዲስ አበባ ህዝብ፣ ከአማራ ህዝብ፣ ከብአዴን እና ከከፊል የአዲስ አበባ መስተዳድር አመራር ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ የሚገጥመው ይሆናል።የአብይ ፍፃሜም በአዲስ አበባ ጉዳይ የሚወሰን ይመስለኛል።ይህ ሳይሆን ቀርቶ የአዲስ አበባን ጉዳይ ከብአዴንና ከኦህዴድ ተፅዕኖ ወጥቶ ለነዋሪው ብቻ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚፈታው ከሆነ ደግሞ የፖለቲካ ብቃቱ ይታያል ማለት ነው።እናም አራተኛው ነጥብ ስጋትም ተስፋም ያለበት ስጋቱ ያጋደለ የአብይ ተግባር ይመስለኛል።
አምስተኛው ጉዳይ የአማራን ህዝብ #ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአማራ “ክልል” ብቻ ሊተገበሩ የሚችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ማስጀመር ነው።ለዚህም አብይ ሌላ ህግ ማርቀቅ ሳያስፈልገው የሀገሪቱ የዓመታት ሪፖርትን ብቻ በመመልከት የአማራ “ክልል” ባለፉት ዓመታት ከሌሎች ክልሎች አንፃር የሚገኝበትን ማየቱ በቂ ነው።ለዚህም ከወራት በፊት ብአዴን ገምግሞ የተስማማበት ነጥብ የአማራ ህዝብ ባለው ስርዓት ውስጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ማረጋገጡ ለአብይ ስራ ቀላል ይሆንለታል።በተለይም በኢንዱስትሪ እና ጤናው ዘርፍ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ዘርፍ (ከግብርና ውጭ) ክልሉ ከሌሎችም ክልሎች በባሰ ሁኔታ ኋላ ቀር መሆኑን መግባባት ላይ የደረሱ ይመስለኛል።ያንን ሪፖርት ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም እንዳቀረቡት እገምታለው።ስለሆነም ይህ ክልል ልዩ ድጋፍና ካሳ የሚያስፈልገው መሆኑ ለአብይ የሚጠፋው አይመስለኝም።ይህንን ለመፈፀምም የሚጠይቀው ካቢኔውን ማሳመንና መጠነኛ የህግ ማሻሻያ ማደረግ እንጅ ህገ መንግስት ማሻሻል አይደለም።
እንግዲህ ከላይ የጠቀስኳቸው አምስት ጉዳዮች በእኔ እይታ ዶ/ር አብይ አብዛኛው ተቃዋሚ የሚቃወመውን የህወሃትና ኦነግ ወለድ #የብሄር ፖለቲካ ማሻሻል ሳያስፈልገው፣ ብዙሃኑ (በተለይም አማራው) የማይቀበለውን ህገ መንግስት ሳይቀይር፣ የህወሃትን “ልማታዊ ዴሞክራሲ” እና የመንግስት ጣልቃ ገብነት (Interventionist) የሚፈቅድ ርዕዮት አለም ውድቅ ማድረግ ሳያስፈልገው በስርዓቱ ውስጥ ሁኖ ሊፈፅማቸው ይችላል ብየ አምናለው።ዶ/ር አብይ እነዚህን ጉዳዮች እንኳን መፈፀም ከቻለ የአንድ በስርዓቱ ውስጥ ያለ ጥሩ መሪ መለኪያው አድርገን በበጎው ማየት እንችላለን።ከላይ የጠቀስኳቸው አምስት ነጥቦች ካሉብን ግዙፍ ችግሮች ውስጥ በጣም ጥቂቶቹንና በአብይ “የመሪነት” ዘመን መፈፀም ይችላሉ ያልኳቸውን ብቻ ነው።ሌሎቻችን ከዚህም በተሻለ እንደምትገልጿቸው እገምታለው።እኔ ግን ለዛሬ ይህንን ካልኩ ይብቃኝ እላለው።በዶ/ር አብይ ፍቅር የወደቃችሁ አካላትም ከስሜት ወጥታችሁ ከላይ ያስቀመጥኳቸውን ነጥቦችና ሌላች ጉዳዮችን በራሳችሁ መንገድ በማንሰላሰል ላይ ብታተኩሩ እንደ ህዝብ የምንጠቀም ይመስለኛል።
ዶ/ር አብይ በጥቅሉ ግቡ መታ የምንለውስ መቸ ነው?
ይህ የብዙሃኑ ጥያቄ ይመስለኛል።ለእኔ ዶ/ር አብይ ግቡን መታ የምለው ባለፈው ኦህዴድ ያወጣውን መግለጫ (በድሮ ዘመንም ቢሆን የመደብ እንጅ የብሄር ጭቆና አልነበረም) ያለውን እውነታ በደንብ ገፍቶበትና ሌሎች ብሄራዊ ድርጅቶችም ተቀብለውት በሂደት በውሸት ከተፈጠረ የብዳይና ተበዳይ የብሄር ፖለቲካ የምንወጣበትን የዴሞክራሲ ስርዓት እና የመንግስት አወቃቀር መገንባት ሲችል ነው።ይህንን ለማደረግ ከራሱ ከኦሮሞው ወገኑ ሳይቀር ከህወሃት ያልተናነሰ ተቃውሞ እንደሚገጥመው መገመት እንችላለን።ነገር ግን አብይ በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ጽፌ ልለፍ ካለ Climax point ላይ የሚገኘውን በጥላቻ ላይ የተገነባ የብሄር ፖለቲካ በሂደት እንዲጠፋ ስራዎችን ከአሁን አቅዶ እየሰራ መቆየት ነው።ይህንን ለመፈፀም ብዙ ስልትና እቅድ መንደፍ እንደሚጠይቅ ማወቅ ያስፈልጋል።ይህንን ማደረግ ካልቻለ ወደፊት ስጋቱ ከአማራው ይልቅ ለሌሎቹ እንደሚሆን ዛሬ ላይ ሁኖ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።ስለሆነም የብሄር ፖለቲካን በረጀም ጊዜ የመቀየር ስልትን ከደጋፊ አቻወቹ ጋር ሊተገብር ይገባል ባይ ነኝ።
በማጠቃለያ ማንሳት የምፈልገው ነገር ደግሞ በዶ/ር አብይ ዘመን “ምንም አይነት ለውጥ አይመጣም” በሚል ሙሉ በሙሉ ራሳችን ጫፍ ላይ በማስቀመጥ ምን አገባን? ብለን እንጓዝ የሚለው ነው።ይህ ነገር ትክክለኝነቱ ቢያመዝንም እንደ ፖለቲካ ግን አዋጭነቱ አያስማማኝም።ፖለቲካን ማዘመንም ማድረቅም የምንችለው በቅርብ ስንከታተል እና ተለዋዋጭ ሁነን ነው፤ እንዲሁም ማሸነፍ የምንችለው የጠላትን ድልድይ በመስበር ብቻ ሳይሆን ለእነርሱ የገነቡትን ድልድይ ለእኛ በማደረግም ጭምር መሆኑን መዘንጋት የለብንም የሚለው መልዕክቴ ነው።እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለብን አንዱ ጉዳይ ወቅትን ነው።ዛሬም የትናንቶች በመኖራቸው እርግጠኞች ብንሆንም የትናንቱን ማደረግ እንደሚችሉ መሆኑን ግን በልበ ሙሉነት መናገር የምንችል አይመስለኝም።ለህወሃትም ቢሆን ዛሬ ትናንት አይደለም።እናም በጥንቃቄ ራሳችን ማየቱም አይጎዳም ለማለት ነው።
ቸር እንሰንብት!! መጭው ጊዜ ከህብዛዊ ትግል ጋር ብሩህ ነው!!!የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም።