>

"የሚታወቅ መረጃ ነው እየነገርኩት ያለሁት፤ አትናገርም የምትሉኝን አልቀበልም፤ የፈለጋችሁትን ልታደርጉ ትችላላችሁ!" እስክንድር ነጋ

በ እዩኤል ፍስሃ

ብርቱው እስክንድር ነጋን በንፋስ ስልክ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አግኝቼው ነበር። አብረዋቸው ታስረው ስለሚገኙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰለባዎች ጥያቄ አንስቼለት ነበር።

አብዛኞቹ ከሰበታ አካባቢ ተይዘው እንደመጡና ከታሰሩ 1 ወር እንዳለፋቸው ገልፆልኛል።

“እኛ የተፈታን ጊዜ ነው የታሰሩት፤ በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት” ሲል ገልፆልኛል።

እስክንድር ይህን እያለኝ ሳለ ወሬያችንን ለማዳመጥ የተሰየመው ፖሊስ በወሬያችን ጣልቃ ገብቶ “እስክንድር ተው!” ሲል እስክንድር ከመናገር እንዲቆጠብ ለማሳሰብ ሞከረ። እስክንድርም በእርጋታ ተሞልቶ “የሚታወቅ መረጃ ነው እየነገርኩት ያለሁት፤ አትናገርም የምትሉኝን አልቀበልም፤ የፈለጋችሁትን ልታደርጉ ትችላላችሁ!” አለው። ፖሊሱም ይህን ጊዜ በመለሳለስ “እስክንድር አንተ ወንድማችን ነህ፤ ምንም አናደርግህም!” አለው። ወደእኔ በመዞርም “እንዲህ ያለ መረጃ ካስፈለገህም ከዚህ ሳይሆን ከሚመለከተው አካል መጠየቅ ትችላለህ” አለኝ። እስክንድር ይህም ስላልጣመው በእኔና በፖሊሱ ምልልስ ጣልቃ በመግባት “የምነግርህ ተጨማሪ መረጃ ስለሌለ እንጂ ማንም የመናገር መብቴን አይነጥቀኝም! የምነግርህን ነገር ተናግሬ ስለጨረስኩ ግን የምነግርህ ነገር የለም” አለኝ።

ወደ ፖሊሱ ተመለከትኩ። ፖሊሱ ላይ ምነው ሲናገር ባላስቆምኩት ኖሮ የሚል ቁጭት ፊቱ ላይ አነበብኩ። ሌሎቹን እንዲጠራልኝ እስክንድር ነግሬው ተለያየን። ከእስክንድር ሁሌም የሚያስደምመኝ ባሕርዩ በምንም ሁኔታ ውስጥ መብቱን እንዲጣስ ፈፅሞ የማይፈቅድና መብቱ ሲጣስም መብቱን የሚጥሱ ሰዎችን ስራቸው አግባብ አለመሆኑን በፍፁም ትህትና የማስረዳት ችሎታው ነው።

እስኬው በእስር ብዛት የሚቀየይረው አንዳች አቋም የለውም። በእስክንድር መታሰር የሚጎዳው እስክንድር አይደለም። ሀገር ነው የምትጎዳው፤ ሕዝብ ነው የሚጎዳው! እናም እስክንድርንም ሆነ አብረውት ወደ ወሕኒ የተወረወሩት የመብት ተሟጋቾችን በአስቸኳይ ብትለቁ መልካም ነው!

Filed in: Amharic