>

ቄሮዎች ስለ ዶ/ር አብይ አህመድ ምርጫ ይናገራሉ (ተስፋለም ወልደየስ እና ነጋሽ መሐመድ

ቄሮ የሚለው የኦሮምኛ ቃል መሠረቱ “ያላገባ ወጣት” የሚለውን የሚወክል ቢሆንም ባሁኑ ወቅት ግን ብዙዎች ስያሜውን ከተቃውሞ ንቅናቄ ጋር ያይዙታል፡፡ በእርግጥም በኦሮሚያ ክልል ለሶስት ዓመታት በተካሄደው ተቃውሞ ይህን ስያሜ የሚጠቀሙ ወጣቶች ሁነኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል፡፡ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግበው በተደጋጋሚ አደባባይ ከመውጣት እስከ እስር እና ሞት ድረስ ተጋፍጠዋል፡፡ የቄሮዎች ያልተቋረጠ ተቃውሞ እና ግፊት የክልሉን ገዢ ፓርቲ የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ከዚህ ቀደም ያልታዩ ለውጦችን እንዲያመጣ እንዳስገደዱት የሚናገሩ አሉ፡፡
ኦህዴድ በገዢው ግንባር ኢህአዴግም ሆነ በፌደራል ደረጃ ያለው ተሰሚነት እና ድርሻ እንዲሰፋ ከመጋረጃ ጀርባም፣ በግልጽም ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ ጥረቱ በቅርቡ የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ስልጣንን የተረከቡትን ዶ/ር አብይ አህመድን ለግንባሩ መሪነት ከፍ ሲልም ለሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እስከማስመረጥ የዘለቀ ነዉ፡፡ ዶይቼ ቬለ ያነገጋራቸው በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ቄሮዎችም ይህን እምነት ያስተጋባሉ፡፡
በኦሮሚያ ምስራቅ ሸዋ ዞን ያለ ማንነቱ እንዳይገለጽ የጠየቀ አንድ ቄሮ “አብይም ሆነ የክልሉ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ የቄሮ ትግል ውጤት ናቸው” ይላል፡፡ የቡራዩ ከተማ ቄሮም የቀዳሚ ባልደረባዉን ሐሳብ ይጋራል። ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው ለትግሉ “አንድ እርምጃ ነው” ሲል ያስረዳል፡፡በዶ/ር አብይ ምርጫ በጣም መደሰቱን የሚናገረው የሰበታው ወጣት የእርሳቸው ምርጫ በቄሮዎች እና ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች ኢትዮጵውያን ዘንድም ተቀባይነት ያለው ነው ይላል፡፡ የምስራቅ ሸዋው ቄሮም በዶ/ር አብይ እና ለማ መገርሳ ሲቀነቀን የቆየው የኢትዮጵያውያን አንድነት እና እኩልነት ጉዳይ የቄሮዎችም ፍላጎት እንደሆነ ያስረዳል፡፡
እርሱም ሆነ ሌሎች ቄሮዎች በዶ/ር አብይ መመረጥ መዘናጋት እንደሌለባቸው የሚመክረው ይህ ወጣት በርካታ መሰራት ያለባቸው ነገሮች እንደሚቀሩ ይገልጻል፡፡ በአዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር አማካኝነት ቄሮዎች በአጭር እና በረጅም ጊዜ እንዲተገብሩላቸው የሚፈልጓቸውን ጉዳዮችም ይዘረዝራል፡፡ የቡራዩው ቄሮ በበኩሉ በህዝብ ዘንድ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሚነሳ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳሉ ይናገራል፡፡ እርሱም እንደ ምስራቅ ሸዋው ቄሮ የአጭር የረጅም ጊዜ ሲል ከፋፍሏቸዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ቄሮዎች በትላንቱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ዶ/ር አብይ ባይመረጥ ኖሮ በኦሮሚያ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይቀሬ ነበር ይላሉ፡፡ የቡራዩው ቄሮ ዶ/ር አብይ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በህዝብ ዘንድ ያላቸውን ድጋፍ ይጠቅሳል፡፡ ሰውየው በቀጣይ ሳምንታት የሚሰጧቸውን መግለጫዎች እና የሚወስዷቸው እርምጃዎች ወሳኞች እንደሆኑ ያሰምርበታል፡፡ የምስራቅ ሸዋው ቄሮ ዶ/ር አብይም ቢሆኑ ቃላቸውን ካልጠበቁ ከተቃውሞ እንደማያመልጡ ያስጠንቅቃል፡፡
ተስፋለም ወልደየስ
ነጋሽ መሐመድ
Filed in: Amharic