>

ነገረ ምረጫ፥ ግምት እና እውነታው በሊቀመንበር ምርጫ!!(ከታዛቢ)

ሰሞኑን የኢህአዴግ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ መጨረሻ ላይ የድርጅቱን ሊቀመንበሩን መመረጡ ትኩስ ወሬ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ምርጫውም ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን እንዲሁም አቶ ደመቀ መኮንን ራሳቸውን አግልለው ሳይሆን ሦስት እጩ ብቻ እንደሚጠቆም ሕገደንቡ ላይ ስለተቀመጠ በዚያው መልክ እንደተፈጸፈ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ገልፀዋል፡፡ በሌላ መልኩ አቶ ሽፈራው የገለጹት ነገር ምን ያህል እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ ወሬ  ለመቀራረም ሞክሬ ነበር፡፡ በዕለቱ ጋዜጠኞች በአስር ሰዓት ተጠርተን ነበር ስላሉኝ አንዱን ጓደኛዬን እየደወልኩ ብጨቀጭቀውም ብዙም ጠብ ያለ ነገር አልነበረም፡፡
ይህ የሆነው ግን እስከ ጧት ብቻ ነበር፡፡ ጧት ላይ ይህ ጓደኛዬ  የውስጥ አዋቂ ምንጮቼ ከሚላቸው  ከአንዱ የምክር ቤት አባል ያጋራውን ወሬ ከነገረኝና እኔም በግሌ ከማውቀው ከሌላ የምክር ቤት አባል ያረጋገጥኩትን ጥቂቱን ላጋራችሁ ወደድኩ፡፡ አሁን ላይ ይሄን ጉዳይ እንድጽፍ ያስገደደኝ የሽፈራው ሽጉጤና የደብረ ጽዮን በዐደባባይ መዋሸት ነው፡፡ የምርጫው ሒደትም እንዲህ ነበር፡፡
ከሁለቱም ሰዎች እንዳረጋገጥኩት ምርጫው ሊጀመር ሲል ሀይለማርያም ለምን  እንደለቀቀ ገልፆ ከመድረኩ ወረደ፡፡ እና ደመቀ መኮንን መድረኩን ብቻውን እንደመራው ፣ ሀይለማርያም ለመልቀቅ የተገደደበትን እና ደመቀም ለጠቅላይ ሚንስትርነት አልወዳደርም ማለቱን ከብዙ አጃቢዎች ወጎችና  እና ትረካዎች ጋር ሁለቱም ዘረዘሩልኝ፡፡  ደመቀ አልውዳደርም ሲል ከፍተኛ ቁጣ ያነሱ የህወሀት ሰዎች እንደነበሩ ነግረውኛል፡፡ የቁጣቸውን ምክንያት ግን ለሁለታቸውም ለእኔም አለገባኝም፡፡ ለማንኛውም ልክ እንደ አለምነህ ዋሴ እኔም ደመቀን  “አዲስ ፊት ወደ ላይ ይምጣ” ብሎ ወስኖ አልወዳደርም በማለቱ አድንቄዋለሁ፤አክብሬዋለሁ፡፡
ጓደኛዬ እንደነገረኝ የመጀመሪያውን እጩ አንድ የህወሀት የምክር ቤት አባል ሽፈራውን ሲጠቁም ምንም ተቃውሞ አልነበረም፡፡ በመቀጠልም አቶ ለማ መገርሳ ዶክተር አብይን ሲጠቁም ከፍተኛ ቁጣ እና ትችት በተለይም ከህወሀት አመራሮች እንደተነሳ እና ለሰዓታት ክርክር እንደነበረ አረጋግጠውልኛል፡፡ ኦህዲዶችም በበቂ ሁኔታ ስለ ዶክተር አብይ ሞግተዋል አሉ፡፡
እኔን የገረመኝ አንዱ የብአዴን አመራር እድል ወስዶ ዶክተር ደብረፂዮንን መጠቆሙ እና ህወሀቶች /ራሳቸው ደብረፂዮንንም ጨምሮ/ መቃወማቸውን እንዲሁም በሪኮንሲደሬሽን እንደገና መታየቱ ፤መልሶም ብአዴን ዶ/ር ደብረጽዮንን “የለም ተልዕኮ ስለሆነ መቀበል አለብህ ” በማለቱ እጩነቱ ፀደቀ::
መጨረሻም ሽፈራው ሽጉጤ  በህወሀት ተጠቁሞ ያለምንም ተቃውሞ  ፤ ዶክተር አብይ አህመድ በኦህዴድ ተጠቁሞ በከፍተኛ ክርክር እና ተቃውሞ /በተለይም ከህወሀት እና ከሌሎች ሶስት አመራሮች/ እንዲሁም ዶክተር ደብረ ጽዮን በብአዴን ተጠቆሞ ከህወሀት በተነሳ ተቃውሞ ተነስቶ በብአዴን እና በህወሀት መካከል ከነበረው ክርክር በኋላ በምርጫ ህግና ደምብ መሰረት ምርጫው ሲጠናቀቅ ዶክተር አብይ 108፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ 59፣ ዶክተር ደብረፂዮን 2 ድምጽ አግኝተው አንዱ ደግሞ አልመርጥም ብለው ድምፅ ሰጥተው ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ሲጠናቀቅ ለአስር ሰዓት የተጠሩት ጋዜጠኞች ሲንቃቁ ቆይተው መመለሳቸውን  ጋዜጠኛው ጓደኛዬ አጫውቶኛል፡፡ሌላኛውም መረጃ ሰጭዬ አረጋግጦልኛል፡፡
እንግዲህ ሽፈራው ሽጉጤ ስለምን እውነታውን መደበቅ ፈለጉ? ለመሆኑ ደመቀ መኮንን ለምን አልወዳደርም አሉ ? የህወሀት አመራሮች ለምን ዶክተር አብይን ተቃወሙ? ብአዴን ለምን ከብአዴን ሳይሆን ከህወሀት ዶክተር ደብረፂዮንን ጠቆሞ እንዳይቀሩም ተከራከረ? ህወሀትስ ለምን የአቶ ደመቀን አልወዳድርም ማለት ተቃወመ? ሕወሀት አሁንም አቶ ሽፈራውን ጠቁሞ ዶክተር አብይን እና ዶክተር ደብረፂዮንን ለምን ተቃወመ ? መረጃ ያላችሁ ወይም ግምት ያለችሁ ጥቂት በሉን ፡
Filed in: Amharic