>

ይታየኛል....!!!! [ሉሉ ከበደ]

ዶክተር አቢይ ይህን የሰው በላውን ስርአት መከላከያ ፖሊስና ደህንነት ፍርስርሱን  አውጥተው፤ ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ ጦርሰራዊት፤ ፖሊስ ፤ ደህንነት አዋቅረው፤ በበጎ ፍቃድና ሙሉ ፍላጎት ላይ ተመስርተው የመላው ሀገሪቱ ወጣቶች ሰልጥነው የገነቡት ጦር ሰራዊት ፤ ክቡር ሰንደቅ አላማችንን እያውለበለበ ፤ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሊያስከብር በአራቱም አቅጣጫ ወደ ዳር አገር ሲተም። ፖሊስ፤ የህብረተሰቡን ደህንነት ሊያረጋግጥ ሲተጋ ፤ ወንጀልን ለመከላከል የህግን የበላይነት ሊያስከብር ፤ ሊያረጋግጥ ሲተጋ ፤ ደህንነት የኢትዮጵያና የህዝቧን ብሄራዊ ጥቅምና ሰላም የሚፈታተኑ የውጭ ሃይሎችን፤ ጠላቶቻችንን እያነፈነፈ በስውር እጁ ሲያከስማቸው። ይታየኛል ። በኢትዮጵያ እርቀሰላም ወርዶ ፤ የተበደለ ተክሶ ፤ የበደለ እዳውን ከፍሎ፤ ተንበርክኮ አልቅሶ፤ ይቅርታ ብሎ የወሰደውን መልሶ ሲታረቅ። ይታየኛል። እጁ በደም የተነከረም አድሎ በሌለበት ፍርድ ቆሞ ባፈሰሰው ደም ልክ ቅጣቱን አሜን ብሎ ሲቀበል። አሜን ብሎ ሲዳኝ ። ይቅር የተባለም ይቅር ተብሎ፤ የሰላም የፍቅር ህይወት ሲቀጥል። ታየኛል። ማንም ኢትዮጵያዊ የፈለገበት ጥግ ሄዶ ጎጆ ቀልሶ ፤ሰርቶ ፤ትዳር መስርቶ በደረሰበት ህይወቱ በሰላም ስትለመልም። ማነህ ?ምንድነህ? ከየት ነህ ? ሳይባል ኢትዮጵያዊ በሄደበት ጥግ ሁሉ “ግባ በሞቴ ፤ ቤት ለንግዳ ፤ ቤትህ ነው ቤቴ” እየተባለ ዝንተአለም የሀገሬ ሰው በሰላም ሲኖር ። ይታየኛል።ህልም እንዳይመስላችሁ ከነአብይ ከነለማ ጋር ሆነን የምናመጣት ኢትዮጵያ ይህች ነች።

Filed in: Amharic