>

ኢትዮጵያ ሆይ! መዳንሽም ቀርቧል?! አምላክ ሊጎበኝሽ ከበራፍሽ ቆሟል?! [አቤል ዋቤላ]

ዛሬ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሚዘከርበት ዕለት ነው። ክርስትያኖች የክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ለሰው ልጅ ድኅነት ነው ብለን እናምናለን።

ኢትዮጵያውያንም አምላክ ሳይሆን እንደኛ የሆነ ሰው ወደ አራት ኪሎ መግባቱን እየተጠባበቁ ነው። አሁን አድን! አሁን አድን! የሚለው ድምፅ ከመቼው ጊዜ በበለጠ ጎልቶ ይሰማል። ህፃን ኣዋቂው፣ ሴት ወንዱ፣ ሙስሊም ክርስቲያኑ፣ ከሀገር ውስጥም ከባህር ማዶም፣ ጥቁርም ነጭም “አሁን አድን የኢትዮጵያ ልጅ!!!” እያሉ ነው።

እርግጥ ነው አንዳንዶቹ የኦሮሞ ልጅ አሁን አድን ማለታቸውም ይሰማል። የኦሮሞ ልጅ ወደ ስልጣን መምጣቱ በራሱ ብቻውን ድኅነት የሚያመጣ ይመስል የመጀመሪያው ኦሮሞ ወደ ስልጣን መጣ ብለው ከበሮ ይደልቃሉ። ከዐፄ ምኒልክ ዘመነ ጀምሮ ኦሮሞዎች በስልጣን ማማ መኖራቸውን ይክዳሉ። ዘረመል ብቻውን ዴሞክራሲን የሚፈጠር ግብዐት ባለመሆኑ ጩኸቱ አድን ሳይሆን ሌላ ነው የሚሉ በርክተዋል። መንበሩ መላው ኢትዮጵያውያንን ማገልገያ በመሆኑ ኦሮሞነት ወደ ስልጣን መውጫም ከስልጣን መከልከያም ሊሆን አይገባውም።

በሌላ መልኩ አዲሱ ተመራጭ በህዝብ ያልተመረጠ፣ ከወንበዴዎቹ አንዱ፣ የአውራው ወንበዴ አሽከር፣ የገንጣይ አስገንጣይ ቀኝ እጅ ነው ብለው የሚከራከሩም አልጠፉም። ከሀገሪቱ ታሪክ እና ደኅንነቱ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ከመፈትፈቱ አንፃር ጥርጣሪያቸው ተገቢነት አለው። ነገር ግን ምርጫውን የቀደሙ ክሰተቶች ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ጨምሮ ከተመለከተን ጥርጣሬው ብዙ ውሃ የሚቋጥር አይሆንም ። ተመራጩ ዶር አብይ አህመድ ውስን በሆነው የሚዲያ ተጋላጭነታቸው የገነቡት ተክለ ሰውነት ብዙዎች በሰውየው ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ያስወገደ ነው። ወጣት መሆናቸው፣ በቂ ሊባል የሚችል አካዳሚያዊ ጉዟቸው፣ በዲያስፖራው በመጀመሪያ የተከፈተባቸው የማጥላላት ዘመቻ፣ የህዝብ ልጅ በመሆን እና ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን የሚታወቁት የአቶ ለማ መገርሳ የቅርብ አጋር እና ጓድ መሆናቸው በአወንታዊ መልኩ እንዲታዪ አስተዋፅኦ አድርጓል።

እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ስናስገባ ስመጥሩ ኢኮኖሚስት ዶር እሸቱ ጮሌ በ1984 ዓ.ም. አከባቢ የሽግግር መንግስት ሊቋቋም ሽር ጉድ በሚባልበት ሰሞን የተናገሩ ተብሎ ተፅፎ ያነበብነውን ያስታውሰናል። እሸቱ ጮሌ እንዲህ አሉ “ለአንድ ትውልድ ከአንድ በላይ ዕድል አይሰጠውም ‘ይህ ትውልድ’ ግን እድለኛ በመሆኑ ሁለተኛ ዕድል አግኝቷል። ይህንን ሁለተኛ ዕድል ማባከን በታሪክ ይቅር የማይባል ስህተት ነው።” እንዲህ ልብ የሚነካ ምከር ተግባራዊ ሳይሆን ህዝባዊ መንግስት ሳይቋቋም፣ ሀገር በቁልቁልት ስትጓዝ ሦስት አስርት አመታት ሊቆጠሩ ጥቂት አመታት ብቻ ይቀራቸዋል።

በያ ትውልድ ንጉሱ እና የፊውዳል ስርዓትን አስወግዶ ወታደራዊ መንግስት በተከለው፣ ቀጥሎም ወታደራዊ ስርዓቱን አስወግዶ ዘውጋዊ ስርዓት በዘረጋው በዚያ ትውልድ የመጨረሻ ወራት አዲስ እድል ለአዲስ ትውልድ በር እያንኳኳ ይመስላል። ያ ትውልድም የሀገሪቱን ሦስተኛ ዕድል ለሦስተኛ ጊዜ ለማጨናገፍ አድብቷል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንደ ከዚህ ቀደሙ ጭፍን ድጋፍም ሆነ ጭፍን ተቃውሞ ለሀገር የሚበጅ ሳይሆን አጥፊውን የሚረዳ ነው። እንደ እነ ልደቱ ያለው “ሦስተኛው መንገድ” እና የእነ ኃይሌ ፊዳ “ሒሳዊ ድጋፍ” ምሳሌ ይሁን አይሁን አላውቅም።

ነገር ግን መፍትሄውንም ከላይ ካነሳናቸው ምሁር የቆየ ምክር ብንጀመረው ደስ ይለኛል። ዶሩ ለተማሪዎቻቸው የመከሩት ምክር ተደራጁ!ተደራጁ! ተደራጁ! የሚል ነበር። አሁንም ለህዝብ ፊቱን ያዞረ የሚመስለው ዕድል እንዳይባክን የሚፈልግ ሰው ያለው አማራጭ መጠነ ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ ብቻ ነው። መደራጀት ለመጠነ ሰፊ ተሳትፎ በር ይከፍታል። በዘውግ የተደራጁ ቡድኖች ያደረጉትን አይተናል፤ በርዕዮተ ዓለም የተቧደኑትንም አይተናል፤ ብሶት ወልዶ የሰበሰባቸው የሚያሰለፈልፋቸውንም ተመልክተናል። ሁሉም ባለበት መርገጥ ነው።

አሁን መደራጀት ያለብን ለከበረ ሐሳብ ነው። መደራጀት ለፍትህ ነው። መደራጀት ለእውነት ነው። መደራጀት ለነፃነት ነው። መደራጀት ለእኩልነት ነው። መደራጀት ለወንድማማችነት ነው።

ዶር አብይን አንደሊትመስ ፔፐር የሚፈትናቸው የተደራጀ እና የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ ትውልድ እርብርብ ነው። የህዝብ ልጅ ከሆኑ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርግ እና የተደራጀ ትውልድ ክንድ ይሆናቸዋል። ወንበዴ ወይም የወንበዴ አሽከር ከሆኑ ደግሞ የተደራጀ እና ሀገሩን የሚጠብቅ ትውልድ ከነአለቃዎቻቸው አንቅሮ ይተፋቸዋል።

መሲህ የለም። ከየትም ሊመጣ አይችልም። ድኅነት በእጅ ያለ ነው። በተግባር እውን የሚሆን።

Organize! Organize! Organize!

ከታዕካ ነገስት በዐታ ለማርያም፣ አራት ኪ

Filed in: Amharic