>
5:21 pm - Saturday July 20, 6712

የኢትዮጵያን አንድነት ለምንፈልግ፣ ስሟ በክብር ሲጠራ ለሚያስደስተን፡ መስማት የምንፈልገውን ዛሬ ሰምተናል (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

የዶ/ሩ ንግግር ይቅርታ የተገለጸበት፡ ፍቅር የተንጸባረቀበት፡ ኢትዮጵያዊ አንድነት የተሰበከበት ነበር!!!!
ጥሩ ንግግር ነው። ኢትዮጵያዊነት የተወደሰበት፡ ያለፉት የኢትዮጵያ መሪዎች በነበራቸው መልካም ጎን ምስጋና ያገኙበት፡ የፈጣሪ ስም ተጠርቶ ኢትዮጵያን ይባርክ ዘንድ የተለመነበት፡ ድንቅ ንግግር። ህወሀት በተቆጣጠራት ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት እንዲህ ዓይነት ንግግር ጆሮአችን አለመደም። ዶ/ር አብይ በተለያዩ ቃለመጠይቆቹና የመድረክ ንግግሮቹ ይነግረን የነበረውን ኢትዮጵያዊ ህልም በእነአባይ ጸሀዬ ፊት፡ በአገዛዙ መድረክ ላይ የአገዛዙን ትልቁን ”ስልጣን” በጨበጠበት ዕለት ደግሞ ደጋግሞ ሲነግረን በእርግጥም ያልተለመደ በመሆኑ ያስደንቃል። የህወሀት መሪዎች መስማት የማይፈልጉትን ንግግር ፊት ለፊት ተደርድረው ሲጋቱት ማየትም አንድ ነገር ነው።
በ27ዓመታት የህወሀት አገዛዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማው ፊት የኢትዮጵያ ክብር ሲገለጽ በመስማታችን ልዩ ስሜትን ፈጥሯል። የፓርላማው አባላትም የመለስንና የሃይለማርያምን ደረቅ፡ ችክ ያለ፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ቃላት የተንዛዛ፡ ሰው ሰው የማይሸት ንግግር ስለለመዱ ነው መሰለኝ ለዛሬው የዶ/ር አብይ ንግግር የሚገባውን ጭብጨባ ነፍገውታል። እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የተዋጣለት ንግግር እዚህ አሜሪካን ኮንግረስ ቢሆን ኖሮ በየአራት ነጥቡ ጭብጨባ የሚያደምቀው፡ አስር ግዜ ከወንበር እየተነሱ አድናቆት የሚቸረው ንግግር በሆነ ነበር።
የኢትዮጵያን አንድነት ለምንፈልግ፡ ስሟ በክብር ሲጠራ ለሚያስደስተን፡ መስማት የምንፈልገውን ዛሬ ሰምተናል። የዶ/ሩ ንግግር ይቅርታ የተገለጸበት፡ ፍቅር የተንጸባረቀበት፡ ኢትዮጵያዊ አንድነት የተሰበከበት በአጭሩ አንድ የሀገር መሪ ለሀገሩና ለህዝቡ ማለት የሚገባው የተባለበት ንግግር ነው። ይህንንም ለመስማት የበቃነው በህዝብ ትግል ነው። ዶ/ር አብይ የዚያ ትግል ውጤት አንዱ መገለጫ ነው። መጨረሻው ግን አይደለም። ቃል ሰምተናል። መንፈሳዊ መጽሀፉም መጀመሪያ ቃል ነበር ይላል። ተግባሩ ነው ዋናው ጉዳይ።
አሁን ደግሞ መሬት ረግጠን እንናገር። አሁንም ስጋቱ ከፍተኛ ነው። በእርግጥ የመጀመሪያ ንግግር በመሆኑ ዝርዝር ነገሮችን ላንሰማ እንችላለን። ቢያንስ ግን ሀገሪቱን ማንቁርቷን አንቆ፡ መፈናፈኛ አሳጥቶ ስለያዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንድም ቦታ አለመጠቀሱ ጥያቄን ጭሮብኛል። አሁን ባለው ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በላይ ስልጣን ያለው ኮማንድ ፖስቱ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ተሰብስቦ በህወሀት ጄነራሎች እጅ ገብቷል። ዶ/ር አብይ መቼ ነው በህዝብ ፊት የተረከበውን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችለውን ስልጣን ከህወሀት ጄነራሎች እጅ የሚነጥቀው? የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያት ሰብሳቢ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑ እውነተኛ ስልጣኑን ይተገብራል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።
መሰረታዊው ጥያቄ የዶ/ር አብይ መምጣትና መልካም ንግግር ማድረግ ከምንናፍቀው፡ የስንቱ ህይወት መስዋዕት ከሆነለት ስርነቀል ለውጥ ጋር በምን ይገናኛል? ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያውያን የናፈቁትን እውነተኛ የስርዓት ለውጥ ለማጨናገፍ የተላኩ ስውር መልዕክተኛ ወይስ ወደዚያ ለውጥ ሊወስዱን ከልብ የቆረጡ መሪ? የዛሬው የስልጣን ርክክብ ከአንዱ የኢህአዴግ መሪ ወደሌላኛው የኢህአዴግ መሪ ከመሸጋገር ያለፈ ምን ትርጉም አለው? በዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ጨቋኙ የህወሀት አገዛዝ አተረፈ ወይስ ከሰረ? ኢትዮጵያውያን በእጃችን ምን የተጨበጠ ነገር ይዘን ነው የዛሬውን ትዕይንት በአወንታዊ ጎኑ የተቀበልነው? ጥያቄዎች መነሳታቸው ግድ ነው።
ጊዜ ወይም ፋታ ይሰጠው የሚሉ ወገኖች በዝተዋል። እርግጥ ነው- በአንዲት ጀምበር ሁሉ ነገር አይሆንም። በተለይ እንደህወሀት ዓይነት ተንኮለኛና መሰሪ ስርዓት እያለ ለውጥን በአጭር ጊዜ መጠበቁ አጉል ድፍረት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታና ከህወሀት ስርዓት ባህሪ አንጻር ጊዜ የማይሰጣቸው፡ ፋታ የማያስፈልጋቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ። አንዱም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ነው። በፊትም መደንገግ አልነበረበትም። ይህን ያህል ጊዜም መቆየት የለበትም። የዶ/ር አብይን ስልጣን የሚጋፋ በመሆኑም ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ መወገድ የሚገባው አዋጅ ነበር።
ትግሉ መቀጠል አለበት። ከምንም በላይ ዋስትናችን እሱ ነው። የዶ/ር አብይም ጉልበት የህዝቡ ትግል ነው። ህወሀቶች እሳት እንዳየ ላስቲክ ኩምሽሽ ብለው የማይፈልጓቸው ነገሮች እንዲሆኑ ያደረጋቸው የህዝቡ ትግል ነው። ዶ/ር አብይ በልቡ የፈቀደውን፡ ስለሀገሩ የሚመኘውን እንዲያደርግም የህዝብ ትግል ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉ ላይ ብዥታ ሊኖር አይገባም።
Filed in: Amharic