>

የተሰጥዎት የአገልጋይ ፣ የሃላፊነት እና የአደራ ወንበር እንጂ ዙፋን አይደለም ! በጭራሽ ! (ዮናስ አበራ)

ኢትዮጵያን ከዚህ መከራ ለማውጣት ሚሊዮኖች እርሶ ላይ ተስፋ ጥለዋል ። የ100 ሚሊዮን ዜጎች አይኖች እና ጆሮዎች ሁሉ እርሶ ላይ አርፈዋል ።
ሃገር አደጋ ላይ ነች ። ማጥ ውስጥ ገብታ በመዳከር ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ያድኑ ዘንድ ታሪክ ፣ እጣፈንታ እና ፈጣሪ ይህችን ቀን ዛሬ ለእርሶ አበርክቷል ። ታላቅ እድል ብቻ አይደለም ፥ ታላቅ አደራ ጭምር እንጂ ። የተሰጥዎት የአገልጋይ ፣ የሃላፊነት እና የአደራ ወንበር እንጂ ዙፋን አይደለም ! በጭራሽ !
እሱ ወንበር ላይ ጓደኞችዎ ከዚህ ቀደም ተቀምጠውበታል ፤ ሟቹ በእብሪት ተወጥሮበታል ፣ ደንፍቶበታል ፣ አሲሮበታል ፤ ዜጎች ላይ አላግጦበታል ፣ ለዜጎች ደረጃ አውጥቶ የኢትዮጵያን ህዝብ እርስበርሱ የሚያባላበትን የርኩሰት ማኑዋል ተቀምጦ ፅፎበታል ፣ በስራ ፋንታ ሴራ ፥ በፍቅር ፋንታ ጥላቻ ዶልቶበታል !! ቅጥፈትንና ውሸትን ብሔራዊ ባህል አድርጎ መንደር ድረስ አስፋፍቶበታል !! ቀይ ስርቆትን “ሙስና” ብሎ ዳልቻ ቀብቶ ሃገር ዘርፎ አስዘርፎበታል !! አይን ያወጣ ዘረፋን “ኪራይ ሰብሳቢነት” በሚል ዘይት አለስልሶ ስርቆትን የፌዴራሊዝሙ ባህል አድርጎ ወረዳ ድረስ አስፋፍቶበታል !! በድካም እና በስራ ሳይሆን በሌብነት በአንድ ጀምበር መበልፀግን ስኬት አድርጎ እንዲያስብ አዲሱን ትውልድ አንጋዶበታል !! ኢትዮጵያዊነትን ያቀነቀኑ ዜጎች ያለእፍረት በጅምላ አሳስሮበታል ፣ አስደብድቦበታል ፣ አስገድሎበታል ፣ የዘር ፍሬአቸውን አኮላሽቶበታል !! ከግብርአበር ጓደኞቹ ጋር ሆኖ በተለይ አማራን እንደ ሸለመጥማጥ አሳዶበታል ፤ ውዱን የኦሮሞ ህዝብ በኦነግ ስም አስገርፎበታል ፣ አስጨፍጭፎበታል !! ወንበሩን አርክሶ እሱም ረክሶ ንስሃ ሳይገባ ፥ አምላኪዎቹ ንስሃ ያገኝ ዘንድ ፀሎት እንኳን እንዳያደርጉለት ህመሙና ሞቱ ሁሉ ተደብቆ በረዶ ቤት የከረመ ቋንጣው መጥቶ ከማይቀርበት አፈር ገብቶ አፈር ለብሷል !! ኢትዮጵያ ደግ ነችና ከእነርኩሰቱ መጥቶ ሲቀበርባት አፈሯን ፥ ሆዷን አልነፈገችውም ። መርዙ ግን እናት ሃገሬ ኢትዮጵያዬ ላይ እስካሁን ተተክሏል ……
ቀጣዩ ገልቱ ደግሞ ወንበሩ መጀመሪያዉኑ ያለ ልኩ ነበረና ጭራሽ ለሌሎች አከራየውና አረፈ ! አቶ ሃይለማሪያም እንዲሁ አንዱም ነገር ሳይገባው በለሆሳስ እንደባተተ ከረመ ፤ እራሱ ረክሶ የሃገር መሪነትን ወግ ማዕረግ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ታች አወረደው ፤ የርኩስ “ሌጋሲ” ሳይበረዝ አስቀጥላለሁ ሲል ባሪያነቱን በምቾት ኖረበት ፤ ፈጣሪውን ትቶ በሙት መንፈስ ነፍስ አልባ ስጋ ሆኖ ውሎ አደረ !!
 የሟቹ ጋሻጃግሬዎች በእብሪተኝነት የሟቹን የተወለካከፈ ቅዠት “የታላቁ መሪያችን ራዕይ” በሚል ዜጎች ላይ ከእነ ክርፋቱ ካልተገደገደ አሉ ! ፈጣሪና እጣፈንታ ሳይታሰብ ያመጣውን የለውጥ እድል አርቀው ቀብረው በከንቱነት ተመላለሱ ። ዜጎችና ኢትዮጵያዬም አብራ ይበልጥ ረከሰች !! አቶ ሃይለማሪያም ሃገር ከፊት ሆኖ ሊመራ ቀርቶ ንግግር እንኳን በቅጡ የማይችል ሆነና ሁለት ሳቅ (አንዱ እያረርን) ሲያስቀን ከረመ ። እሱ ለሚናገረው ዜጎች ተሸማቀቅን ፤ ጤፍ አከልን ። የውጭ ዲፕሎማቶች ግራ ገብቷቸው  “Who is leading the nation ?!” እስኪሉ ድረስ ተዋረደ ! ተዋረድን ! ወደ በኋላማ የጠቅላይ ሚኒስቴር ወንበር አስከመኖሩም ተረሳና ሁሉም እኩል ቤት ሆነ !  እነ አባይ ፀሐዬም “ልክ እናስገባችኋለን !” እያሉ አንገታቸው ድረስ የጠጡትን ብላክ ሌብል አናታችን ላይ ያለከልካይ ያቀረሹብን ጀመር ። እነ በረከት እየተቀባበሉ ተሳለቁብን ፤ ሌቦች “ልማታዊ ባለሃብቶች” እየተባሉ ተወደሱ ፥ ሜዳሊያ ተጠለቀላቸው !! አባቶቻችን ባቀኑት ሃገር ላይ ተላላኪና አፍራሽ ሃይሎች ተብለን ተገፍተን ቀላዋጮች ተባልን ፤ ጨዋነታችን እና ትህትናችን በጥፊ ተመታ !! እህህህህህህ ብለን ወደ ፈጣሪ አነባን !!
 ሃገሪቱ ሁሉም እየተነሳ ያሻውን እየተንተባተበ የሚደነፋባት ርካሽ የመንደር መሸታ ቤት መሰለች ! በዚህ ውስጥ ሆነን ነው እንግዲህ እርሶን እና ጓደኞችዎን ያየነው ፤ ጎጥ ወደ ጎን ተብሎ “ኢትዮጵያ” የሚል ጣፋጭ ቃል የሰማነው ።  ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እንደ ፊኒክስ ከአመድ ውስጥ ሁሉ እንደገና ተነስቶ ዳግም ነፍስ ዘርቶ ከአፅናፍ አፅናፍ እንደሚናኝ አጥብቀን እናምናለን ፤ አምነንም ወደ ፈጣሪ እንፀልያለን …. ይሰማንማል !!
ክቡር ጠ/ሚ ዛሬ ሳር ቅጠሉ ሁሉ “ቪቫ አብይ” ሲል እርሶ ላለፉት 26 አመታት ስርዓቱን ሲያገለግሉ እንደነበር አጥተነው እንዳይመስልዎ ፤ ምናልባት ለመልካም አገራዊ ፋይዳ ብለው እርስዎ የመሠረቱት ኢንሳ (INSA) (የኢንፎርሜሽንና መረጃ ደህንነት ኤጀንሲ) ስርዓቱ መስሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ ዜጎችን መሰለያ ተቋም ሆኗል ሲባልም ሳንሰማ ቀርተን አይደለም ። የትናንቱ ትናንት አልፏል ። ዛሬ አዲስ ቀን አዲስ ንጋት ነው ። የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ባይ ነው ። ይቅርታውም ከልብ ነው ። ዜጎች እርሶ ላይ ከታላቅ አደራ ጋር ተስፋ ጥለናል !! ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምድር ሲኦል ሆናለች ፤ ሰማይዋ ታላቅ መከራ አርግዟል ፤ ፍቅር ጠፍቶ በቀልና ጥላቻ አንዣቧል ። በበኩሌ ይሄን ሁሉ ምስቅልቅል በአንድ ጀምበር ያበኑታል ብዬ የማስብ ገራገር አይደለሁም ።
አንደ መውጫ
መምከር ከተፈቀደልኝ የአቅሜን ልበል ?
ክቡርነትዎ
 በእርኩሰት ረክሶ ከርሟልና በመጀመሪያ ፅህፈት ቤትዎን በፀሎት ያንፁት ። ቅድም ያደረጉት ንግግር ላይ “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ” እንዳሉ ሁሉ “ፈጣሪ ሆይ ቀኝ ቀኙን ምራኝ” ብለው በጥልቅ ከልብዎ ይፀልዩ ።
ከህዝብ አይራቁ ፤ ህዝብ አይናቁ ፤ ከህዝብ ጋር ሁሌ ይምከሩ ፤ ዙሪያዎትን ያፅዱ ፤ የውሳኔ ሰው ይሁኑ ፤ እርምጃ ለሚያስፈልገው ነገር ቆራጥ እርምጃ ይውሰዱ ፤ ሃገር በደቦ አይመራምና የአቶ ሃይለማሪምን ስህተት እንዳይደግሙ (The buck always stops with you !) እንዲል ፈረንጅ ፣ እርምጃዎት የማያወላዳ ፥ ፈጣንና ግልፅም ይሁን ፥ እርምጃውንም ለህዝብ ወዲያዉኑ ያሳውቁን ፤ ከሁሉ ከሁሉ በላይ ግን ……… ፈፅሞ ፈፅሞ …..ስለሚያመልኩት ፈጣሪ ብለው ምንም ነገር አይዋሹን !! ውሸት ታክቶናል !!!!!
ዮሐንስ ወንጌል 8፥32 “… እውነት ነፃ ታወጣሃለች” ይላልና ምንም ነገር ቢሆን ፈፅሞ አይዋሹን !
  “….. and the truth shall set you free.”
በተረፈ ከጎንዎት ነን ። የምስራች አብሳሪ እንጂ መርዶ ነጋሪ አያድርጉን ፤ በበኩሌ መርዶ መንገር ደክሞኛል !!!  አበቃሁ ።
ፈጣሪ እርሶንና ኢትዮጵያን ይባርክ ።  
መልካም የስራ ዘመን
Filed in: Amharic