>

ዞምቢዎቹ...! (መስፍን ነጋሽ)

ይህ “ዞምቢዎቹ” የተባለ ጽሑፍ ከዘጠኝ ዓመት በፊት (2001 ዓም) አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይ የጻፍኩት ነበር። አሁን መልሼ ሳየው ይህን ያህል የሚረባ ባይሆንም ብዙዎች ከሚያስታውሱት ጽሑፎች አንዱ ነው ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ወዳጄ ኢዮብ ብርሃነ ጽሑፉን መልሶ ተይቦ፣ ከማስታወሻ ጋራ በገጹ ስላጋራኝ አመሰግነዋለሁ። እኔም እዚህ ለጥፌዋለሁ። እነሆ።

ዞምቢዎቹ…!

መስፍን ነጋሽ
ነፍሱን ይማረውና (ይህን ማለትም ወግ ነውና!) ማይክል ጃክሰን ስሙ ሲነሳ የሚታወሰኝ ሌላ ጉዳይ ነው፣ ዞምቢዎች። “ትሪለር” በተባለው እጅግ ዝነኛ ዘፈን ውስጥ ሲሞቱ በነበሩበት ሁኔታ ከመቃብራቸው የሚመጡ ¨ሰዎች¨ እንመለከታለን፤ ዞምቢዎች።
አፈታሪኩም ሆነ ታሪኩ እንደሚለው ዞምቢዎች የሙታንን መንፈስ በሚጠሩ ¨የሃይማኖት¨ ሰዎች ከመቃብራቸው ይጠራሉ። ዞምቢዎች ነፍስ የላቸውም፣ የሚንቀሳቀስ አካል እንጂ። እናም እግራቸውን እየጎተቱ የተቦደሰ አካላቸውን እንደያዙ ጤነኞቹን ህያዋን ያሳድዳሉ። `ትሪለርን´ አይተው ሲጨርሱ አካባቢያቸው በዞምቢዎች ተወሮ እንደሆነ ለማጣራት ዙሪያቸውን የሚቃኙ አንባቢዎች እንደሚኖሩኝ አልጠራጠርም። ነገር ግን ዞምቢዎች የሌሉ ከመሰለን እጅግ እንደተጭበረበርን ይሰማኛል።
ዛሬ ዛሬ በምንሄድበት ሁሉ ዞምቢዎች በዝተው የሚታዩኝ እኔ ብቻ እሆን? አይመስለኝም። የእኛን ዞምቢዎች ከአፈታሪኮቹ ዞምቢዎች የሚለያቸው ነገር ቢኖር እነዚያኞቹ መሬት ውስጥ ተቀብረው ሲነሱ፣ እነዚህኞቹ በየቀኑ ልባችን ውስጥ መቀበራቸውና ድጋሚ መነሳታቸው ነው።
መበስበስ የጀመረ ወይም የበሰበሰ ሥጋ እና ህሊና ተሸክመው የሚንገላወዱት ዞምቢዎቻችን ዓላማቸው ወደ ¨ሕይወት¨ መመለስ አይደለም። ¨ነፍስ¨ያላቸውን ሰዎች እያሳደዱ ወደ ዞምቢነት መቀየር ብቻ ነው።
 በየቀኑ የሚበሰብሱት ዞምቢዎች፣ በየቀኑ በተግባር የሚለመልሙ ሰዎችን ለማየት አይፈቅዱም፣ ስለዚህም ያሳድዷቸዋል። እናመልከዋለን፣ እናገለግለዋለን ጭራሹንም ¨እንሞትለታለን¨ ከሚሉት አምላክ በግብራቸው እየራቁ፣ በአስተሳሰብና በድርጊታቸው በየዕለቱ የሚበሰብሱ ዞምቢ ሃይማኖተኞች አይታዩዋችሁ? ስለ ¨እውነት¨ እያወሩ ሐሰትን፣ ስለ ¨ፅድቅ¨ እየሰበኩ ሐጢአትን የሚኖሩ ዞምቢ ቄሶች፣ ዞምቢ ሼኮች፣ ዞምቢ ፓስተሮች፣ ዞምቢ መዘምራን …ዞምቢዎች።
በስብዕናቸው በየዕለቱ የሚበሰብሱ፣ በአካላዊ ቁመናቸው ግን በየቀኑ እያማረባቸው የሚታዩ ዞምቢዎችን በየቢሮው ቆጥረን አንጨርሳቸውም። አገር የሚባል ጉዳይ፣ ሕዝብ የሚባል ፅንሰ ሀሳብ ተሳስተው እንኳን ትዝ የማይላቸው፣ አገርና ህዝብን ማጭበርበር እንደ ጀብዱ ቆጥረው በየዓደባባዩ የሚኮፈሱ ዞምቢዎች በየቀኑ ይፈላሉ። አጥንትና ደም እየቆጠሩ የተማሪዎቻቸውን ውጤት የሚወስኑ፣ አንድ ሺህ ሰው በተሰለፈበት የወንዛቸውን ቋንቋ የሚናገረውን ሌላ ዞምቢ ቅድሚያ ሰጥተው የሚያስተናግዱ፣ ቋንቋቸውን እንደ ይለፍ ወረቀት እያስቀደሙ ሰተት ብለው ገብተው ሰተት ብለው የሚወጡ ዞምቢዎች በአስደንጋጭ መጠን እየተበራከቱ ነው።
ብዙዎች ዞምቢ መሆንን ለምን እንደመረጡ ማወቅ ከባድ አይደለም። ዞምቢነት ቀላል ነው። ዞምቢነት ዕውቀት አይጠይቅም፣ ዞምቢነት ድካም አይጠይቅም፣ ስለራስ እንጂ ስለሌሎች ወይም ስለ አገር መጨነቅን አይጠይቅም፣ ዞምቢነት ቀላል ነው። ዛሬ እያንዳንዳችን ከሕሊናችን ጋር ያለብን ሙግትም (የገባንም ያልገባንም) ዞምቢ የመሆንና ያለመሆን ነው።
ዞምቢዎች በሁሉም ስፍራ አሉ፣ በሁሉም የስልጣንና የሀብት እርከንም ውስጥ ይርመሰመሳሉ። ፖለቲከኞቹ ዞምቢዎች ግማሾቹ ከፍተኛ ስልጣን ለማጋበስ፣ ሌሎቹ በስርቆት ሀብት የቤተሰቦቻቸውንና የልጆቻቸውን መፃኢ ጊዜ ¨ብሩህ¨ ለማድረግ፣ የባሰባቸው ደግሞ የዕለት ውስኪያቸውንና ጫታቸውን ለማግኘት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ዞምቢዎች ሕልማቸውን ለማሳካት ይዋሻሉ፣ ያጭበረብራሉ፣ ወሬ ያመላልሳሉ፣ ወሬ ይፈበርካሉ፣ ሴራ ይጠነስሳሉ፣ የክስና የወቀሳ ፋይል ያዘጋጃሉ፣ ይመታሉ፣ ያስመታሉ፣ ይገላሉ፣ ያስገድላሉ።
ተቃዋሚ ሰፈር ውስጥም ያሉት ዞምቢዎችም እንዲሁ ናቸው። ዞምቢነታቸውን መቀበልና ማወቅ እንኳን ስለማይችሉ በዓደባባይ ስለ አገርና ስለ ህዝብ ሲያወሩ፣ ስለ ዴሞክራሲና ስለ መልካም አስተዳደር ገዢውን ፓርቲ ሲወቅሱ እፍረት እንኳን አይነበብባቸውም። አንዳንዶቹም ¨የዝውውር ክፍያ ሪኮርዱ¨ እስከተሻሻለላቸው ድረስ የገዛ ፓርቲያቸውን ከማመስና ከማፈራረስ ወደኋላ አይሉም። የዞምቢዎች አስደናቂ ነገር ግን ዞምቢነታቸውን ሌላው እንደሚያውቅ አለመጠራጠራቸው ነው። ወይም የምንረሳ ይመስላቸዋል።
ነጋዴው ዞምቢም በፊናው¨የዓለም ነገ ታልፋለች¨ የተባለ ይመስል የአንድ ዓመት ትርፉን በአንድ ወር ለማጋበስ ይተጋል። ንፋስ ነፈሰ ሲባል ዋጋ ይጭምራል፣ ነዳጅ ጨመረ ሲባል ዋጋ ይጨምራል፣ አልሸባብ መሪ ቀየረ ሲባል ዋጋ ይጨምራል። በየሱቁ፣ በየድርጅቱ የሚገኘው ዞምቢም በተመሳሳይ አካባቢው በፈቀደለት መጠን ሁሉ በየዕለቱ የሚበሰብስውን ስጋውን የሚሸፍንለት ከሚዘቅጠው ሕሊናው የሚደበቅበትን ሁሉ ይፈፅማል።
በመንግስትም ሆነ በሌሎች መስሪያ ቤቶች ጨረታ ያሸነፈውን ድርጅት ጠርተው¨ገንዘቡን እጥፍ አድርገህ ሰነድህን አሻሽለህ አስገባ¨ የሚሉ ዞምቢዎች የምናውቃቸው ባይመስላቸውም አሉ። ጠዋት ይህንን ዞንቢያዊ ውንብድና ፈፅመው ከሰዐት በኋላ ስለ አካባቢ ጥበቃ፣ ስለ አዲሱ ትውልድ በየሪሴፕሽኑ ሲደሰኩሩ ¨መቼ ንግግራቸውን ጨርሰው በተገላገልን¨ እንደምንል አያውቁም፣ ቢያውቁም ግድ የላቸውም ዞምቢዎች ናቸዋ!
የ¨ትሪለር¨ ዞምቢዎች የአካላቸውን መጎሳቆልና የልብሳቸውን በጭቃ መለወስ ከመቃብር እንደተነሱ ያሳብቅባቸዋል። የእኛዎቹ ግን እንደዚያ አይደሉም። በአገር ስም እየነገዱ፣ ህዝብ እያጭበረበሩ፣ ቀጥሮ የሚያሰራቸውን ድርጅት እየሰረቁ፣ ከእነርሱ ያነሰ ገቢ ካለው ምስኪን አፍ እየነጠቁ በሚሰበስቡት ገንዘብ ሳይቀበር መበስበስ የጀመረ ስጋቸውን ባማሩ ልብሶች ይሸፍናሉ።
 ሃይማኖተኞቹ ዞምቢዎች ቆብና ቀሚሳቸውን ከውጭ ለማስመጣት ይሯሯጣሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ የጣሊያን ጫማ፣ የእንግሊዝ ሱፍ እያሉ ያማርጣሉ። ዞምቢዎች ለንደን ለልብስ ገበያ፣ ፓሪስ ለሽቶ መሄዳቸውን ይነግሩናል። ዝቅተኛ ዞምቢም እንዲሁ ከጠጅ ቤት ሒልተን ሲቀላውጥ ይገኛል። በንግግራቸውና በድርጊታቸው የሚገለፀውን ሕሊናዊና መንፈሳዊ መበስበሳቸውን ደግሞ ንግግር በማሳመር፣ ጥቅስ በማዥጎድጎድ፣ የመፃህፍትና የደራሲዎች ስም በመደርደር ሊሸፍኑት ይሞክራሉ። በስነጥበብ ውስጥ ሰፈር የሚገኙት ዞምቢዎችም እንዲሁ ናቸው። ዞምቢ በዞምቢ ሆነናል።
ዞምቢዎች በሚበዙበት አገር ፍትሕን ማስፈን፣ ፍትሐዊ ልማትና ዕድገትን ማምጣት፣ እውነተኛ ዴሞክራሲን መገንባት ፈፅሞ አይቻልም። ይህ ሁሉ ደግሞ የሚጀምረው ከራስ ነው፣ ከቤት ነው። ምን ያህል አንባቢዎቼ በየዕለቱ በዚህ ጉዳይ ላይ እንደምታሰላስሉ አላውቅም፣ ብዙዎቻችሁን ግን ይህን አታደርጉም ብዬ ልጠራጠራችሁ አልፈልግም። ነገር ግን እያንዳንዳችን ራሳችንን በየዕለቱ በሕሊናም በመንፈስም ከመበስበስ ካልታደግነው አገራችን የዞምቢዎች መፈንጫ መሆንዋ አይቀርም።
(¨ይህማ ከሆነ ቆየ¨ ካላላችሁኝ) ምናለ በሉኝ!
© መስፍን ነጋሽ (አዲስ ነገር ጋዜጣ)
ዞምቢዎቹን መስፍኔ ያያቸው በ04/11/2001 ዓ.ም ነበር ዛሬ ዞምቢዎቻችን አድገዋል በቁጥርም፣ በምግባራቸውም። ይህ የተባ ብዕሩ ሁሌም ይናፍቀኛል ግን ምን ይደረግ? ዞምቢዎቹ ከአገሩ አባረሩት መስፍኔ ነብይ ነው ይህ እንደሚመጣ ቀድሞ ተረድቶታል። ባለህበት ሰላሙን ያብዛልህ!
Filed in: Amharic