>

ቴዲ አፍሮ "ኢትዮጵያ" ለተሰኘው 5ኛና ታሪካዊ አልበሙ  ታላቅና ታሪካዊ ሽልማት ይጠብቀዋል!! (ጴጥሮስ አሸናፊ)

ዘንድሮ 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በአሉን የሚያከብረው ማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (Society of Ethiopians  Established in Diaspora- SEED (ሲድ) እ.ኤ.አ. ከ 1994 ዓ/ም ጀምሮ ካለማቋረጥ የዘር ግንዳቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዝና እንዲሁም በትውልድ የሌላ አገር ተወላጅ ሆነው ለኢትዮጵያ መልካም ነገርን በተለያዩ የሙያ ዘርፍ  ያበረከቱትን በየአመቱ በሚያካሂደው የእውቅናና የሽልማት መርሃ ግብር ” ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ”  በሚል መርህ በሳይንስ፣ በኪነ ጥበብ፣ በስፖርት፣ በሰብአዊ መብት ፣ በበጎ አድራጎት፣ በፖለቲካ፣ በልዩ ፈጠራና በተለያዩ የሙያ መስኮች ታላቅ አስተዋፅዖ ያደረጉ ግለሰቦችን እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃና በኮሌጅ ትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ታዳጊና ወጣት ተማሪዎችን ይሸልማል፣ እውቅናም ይሰጣል።
ሲድ እ.ኤ.አ ጥቅምት 17 ቀን 1993 ዓ/ም በአሜሪካ የተቋቋመ መንግሥታዊ ያልሆነ የግብረ ሰናይ ድርጅት ነው። እውቅናና ሽልማቱን የሚሰጠውም በህይወት ለሌሉትም ጭምር ነው።
ሲድ እውቅና ከሰጣቸው ታላላቅ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች መካከል: በሥነ ፅሑፍ እና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን፣ ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ፣ ኘሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ፣ አለምፀሃይ ወዳጆ፣ ታማኝ በየነ፣ ወጋዬሁ ንጋቱ፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሺኦታ ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ አባተ መኩሪያ፣ እማሆይ ፅጌ ማርያም ገብሩና ሌሎችን።
በሳይንስ፣ በህክምናና በምርምር ዘርፍ: ዶ/ር  ገቢሳ ኤጄታ፣ ዶ/ር መላኩ በያን፣ ዶ/ር በላይ አበጋዝ፣ ዶ/ር አክሊሉ ለማ፣ ዶ/ር ኖኅ ሳማራ፣ ፕሮፌሰር አቻ ደበላ፣ ታዋቂዋ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ሶስና ጌታቸው፣ ፕሮፌሰር ረዳ ተክለሃይማኖትንና ሌሎችን።
በፖለቲካና አመራር፣ በትምህርት፣ በሕዝብ አገልግሎትና  በማኀበራዊ ተሳትፎ: ፕሮፌሰር አስራት ወ/የስ፣ ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት፣ ፕሮፌሰር አለማዬሁ ገ/ማርያም፣ ፕሮፌሰር ሁሴን አህመድ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፣ ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃ/ወልድ፣ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ ዶ/ር አክሊሉ ሃብቴ፣ ዶ/ር ኅሩይ ሚናስ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር መምኅር ዘበነ ለማ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ ሥላሴ፣ እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ አቶ ገብረየስ ቤኛ፣ ራስ አሉላ አባነጋና ሌሎችን።
በበጎ አድራጎት ዘርፍ: ዶ/ር አበበች ጎበናን፣ ወይዘሮ መቅደስ ዘለለውን( ወላጅ እናቴ ነች) ፣ ወይዘሮ ቦጋለች ገብሬ፣ ዶ/ር ጀንበር ተፈራ፣ አርቲስት ስለሺ ደምሴ( ጋሽ አበራ ሞላ) እና ሌሎችን።
በስፓርት ዘርፍ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬንና ሌሎችን
እንዲሁም ሲድ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ባይሆኑም ስለ ኢትዮጵያ ስለ መልክዐ  ምድሯ፣ ባህሎቿ፣ ሃይማኖቶቿ፣ ነፃነቷና ሉዐላዊነቷ፣ ጀግኖች አርበኞች ልጆቿ፣ የፃፉላትንና የመሰከሩላትንም የአክብሮት እውቅና ሰጥቷቸዋል። ከነዚህም መካከል ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን፣ ዶ/ር ስኩንደር ቦጎሲያን፣ ፕሮፌሰር ጆን ሰፔንሰር፣ ኮንግረስማን ዶናልድ ፔይን፣ ኮንግረስማን ሚኪ ሌላንድ፣ የተከበሩ ክሪስ ስሚዝ፣ ወይዘሮ ጄን ኩርትዝና ሌሎችን ሸልሟል።
ሲድ ዘንድሮ የምስረታውን 25 ኛ አመት የብር ኢዮቤልዩ በልዩና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር በተዘጋጀበት ወቅት የአመቱን ምርጥ ተሸላሚዎችንም አሳውቋል።
የሲድ የ25ኛው አመት ልዩ የክብርና የእውቅና መርሐግብር  ተሸላሚዎች መካከል አንድ ልዩ ተሸላሚን መርጧል። ቴዎድሮስ ካሳሁን ገርማሞን!
ቴዲን ልዮ ተሸላሚ የሚያደርገው በሥነ ፅሁፍ ዘርፍ ታላቅ የግጥም ፀሐፊ፣ በሙዚቃው ዘርፍ ታላቅ ድምፃዊና የዜማ ደራሲ፣ በታሪክ ዘርፍ ስለ ኢትዮጵያ ምድሯና ህዝቦቿ፣ ባህሏና ትውፊቷ፣ ጀግኖቿና አንፀባራቂው ድሏ፣ የሃይማኖት መቻቻልና የታላላቅ ልጆቿን ገድል በሥራዎቹ በማሳየቱና ለትውልዱ ልዩ የታሪክ ተናጋሪ በመሆኑ እንዲሁም በበጎ አድራጎት ዘርፍም የእርዳታ እጆቹን ከመዘርጋትም አልፎ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተቋማትን ለመርዳት በሙያው የጎላ አስተዋፅኦ በማድረጉና የኢትዮጵያ የዩኒሴፍ አምባሳደር በመሆን በሚያደርገው የላቀ  እንቅስቃሴ የበርካታ የሙያና የሰብአዊ አገልግሎቶች ባለቤት በመሆኑም ጭምር ነው።
ቴዲ አፍሮ ለሕዝብ ባቀረባቸው አራት የሙዚቃ አልበሞቹና በርካታ ነጠላ ዜማዎቹ እስካሁን በኢትዮጵያ ምድር ድምፃዊነትን ከግጥምና ዜማ ደራሲነት ጋር አዳምሮ በብዛትም፣ በጥራትም በሕዝብ ተቀባይነት በማገኘትም እንዲሁም በሽያጭም ተወዳዳሪ ያልተገኘት የሙያ ባለቤት ነው።
በሼመንደፈር የሐይማኖት መቻቻልን፣ በጥቁር ሰው አርበኝነትን፣ በያስተሰርያል እርቅን፣ በካብ ዳኀላክ የመለያየት ከባድነትን፣ በፀባዬ ሰናይ ትዳርን ፣ በአቡጊዳ ፊደል አስቆጣሪዎቻችንን ፣ በስለ ፍቅር ያሳለፍነው ዘመናችንን፣ በሰባ ደረጃ የጥንቷን ሸገርን፣ በኡኡታዬ የዘመናት ጩኸታችንን፣ በታሪክ ተሰራ እና ኃይሌ ኃይሌ የኦሎምፒክ ውሏችንን፣ በግርማዊነትዎ አፄ ኃይለ ሥላሴንና ፓን አፍሪካን፣ በዋልያ ብሔራዊ ቡድናችንን፣ በኮርኩማ አፍሪካ ስደታችንን እና ስለ በርካታ የሰው ልጆች የሕይወት ውጣ ውረድን፣ ስኬትን፣ ሃዘንን፣ ደስታን ወዘተርፈ የሚዳስሱ ስራዎቹን ላለፉት 20 አመታት ለአድማጭው አድርሶ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አገኝቷል። በተለይም ኦ አፍሪካ በሚለው ዘፈኑ ስለ ዮቶርና ስለ ፍቅር በሚለው ስለ ተዋነይ መዝፈኑ ምን ያህል የታሪክ አንባቢና አስተዋይ መሆኑን በገሃድ ያስመሰከረበት ነው።
ለቴዲ አፍሮም ቢሆን ይሄ ሽልማት ትልቅ ቦታ አለው። በተለይም 4ኛውን የሙዚቃ አልበሙን ለህዝብ ካቀረበ በኋላ ላለፉት 5 አመታት ቀጣዪ አልበም በጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ከትንሳኤ በዓል ማግስት ለህዝብ እንደሚያቀርብ ባሳወቀበትና የስራው አድናቂዎቹም ቀኑን በከፍተኛ ናፍቆት እየተጠባበቁ ካለበት ወቅት ጋር በመገጣጠሙ ደስታውን እጥፍ ድርብ አድርጎለታል።
በዘንድሮው የሲድ ልዩ የ25ኛ አመት ተሸላሚዎች ከቴዲ አፍሮ ጋር ስምንት ሲሆኑ እነሱም:  ከ50 አመት በላይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ስማቸው ከገነነው ድምፃውያን መካከል በተለይም የትዝታው ንጉስ በመባል የሚታወቀው ማህሙድ አህመድ፣ ታዋቂው ገጣሚና የእንግሊዙ ማን ቼስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ለምን ሲሳይ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቿና በአለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ሴቶች ማኀበር ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ተወዳጇ ዶ/ር ማይገነት ሽፈራው፣ ዶ/ር አምባቸው ወረታ፣ ዶ/ር ዛኪ ሼሪፍ ፣ አባ ከፍያለው አበራ እና አቶ ቴድ አለማዬሁ ይሆናሉ።
የዘንድሮው የ25ኛው የማኅበረ ግሩያን ዘረ ኢትዮጵያ ልዩ የእውቅና፣ የአክብሮትና የሽልማት መርሐ ግብር ቅዳሜ ሜይ 28 ቀን 2017 ዓ/ም በአሜሪካን አገር ሜሪላንድ ግዛት ሃያትስቪል በሚገኘው ኮሌጅ ፓርክ ማሪዮት ሆቴል የስብሰባ ማዕከል ይካሄዳል።
ለሁሉም የዘንድሮው አመት ተሸላሚዎችና ቤተሰቦቻቸው በሙሉ እንኳን ደስ ያላችሁ እንዲሁም የማኀበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ(ሲድ) የቦርድ አባላት፣ መስራች አባላት፣ የቦርድ አማካሪዎችና ጠቅላላው የማኀበሩ ቤተሰቦች እንኳን ለ25ኛው የብር ኢዮቤልዩ በአላችሁ በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ።
( ምስጋና ይህን ፖስተር ለሰራው ለዊኒፔጉ መሳይ ናስር ይሁን)
Filed in: Amharic