>
5:13 pm - Friday April 19, 3872

ጸያሔ ፍኖት ዶ/ር ዓቢይ ቃል በተግባር እንዲገለጥ የምንሻ  ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል!

                                                                            ከይኄይስ እውነቱ

በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው ሰማዕቱ ዮሐንስ መጥምቅ በብሉይ ማብቂያ በሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ የተገኘ ኹለቱን በድልድይነት ያገናኘ፣ ለንጉሠ ሰማይ ወምድር መድኅን ዓለም ክርስቶስ መንገድ በመጥረግ÷  ጥርጊያውን በማቅናት÷ በመደልደል እና ሕዝቡን በንስሓ ስብከት በማዘጋጀት ከብሉይ ወደ ሐዲስ ለተደረገው ሽግግር ለነገሥታቱ ንጉሥ እንደራሴ ሆኖ አገልግሏል፡፡

በዚሁ ምሳሌነት ሀገር ዐባይ ኢትዮጵያን የሥልጣን መንበር በመረከብ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ የተሰየመውን ዶ/ር ዓቢይን ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ/ጥርጊያ አቅኒ) ብዬዋለሁ፡፡ በእኔ እምነት (የሕዝባችንና የኢትዮጵያ አምላክ ቸርነት ታክሎበት) የጠ/ሚኒስትሩ ሚና – ኢትዮጵያን ላለፉት 27 ዓመታት ከገባችበት ማጥ በማውጣት ለሰላም፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ፣ ለሕግ የበላይነትና ለመንግሥተ ሕዝብ ለማብቃት ኢትዮጵያውያን በሕይወት፣ በአካልና በእስር እየከፈሉ ያለውን መሥዋዕትነት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ለማሸጋገር፣ ኢትዮጵያችንን ወደ ቀደመ ክብሯና ገናናነቷ ለምትበቃበት አዲስ ዘመን ለማድረስ – የድልድይነት፣ መንገድ አቅኒነት/ጠራጊነት ይሆናል ከሚል መነሻ ነው፡፡ (ንጽጽሩን በተወሰነ ገጽታው ብቻ እንድትገነዘቡልኝ እጠይቃለሁ) አንድም ዘረኛው ወያኔ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መቀመቅ ለማውረድ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት በሚያደርግበት አሥራ አንደኛው ሰዓት ላይ ከአረሞች መካከል የተገኘ ‹መልካም ዘር› በመሆኑ ምናልባት በዚህ ‹ልባም ብላቴና› አመጣጥ ውስጥ  ጥበበ እግዚአብሔር ይኖርበት ይሆን? የሚልም እሳቤ አለኝ፡፡

ለማንኛውም ይህንን በመግቢያነት ካልኩ፣ በዚህ አስተያየት ላስተላልፍ የፈለግኩት ቁም ነገር በታላላቆቼም ተነስቷል፡፡ እኔም አጥብቄ ምስማር ልመታበት የምፈልገው ጉዳይ አለኝ፡፡ እንደተረዳሁት ዶ/ር ዓቢይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረገው ንግግር እምብርቱ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡  በዚህ አንኳር መልእክት ኢትዮጵያውያን (በአገር ውስጥ ለምንገኝም ሆነ በውጭው ዓለም ለምትገኙ) በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ተሰባስበን አገራችንን እንድንታደግ ጥሪ ማድረጉ አይደለምን? በወያኔያዊ ቋንቋ የዚህ ጎሣ የዚህ ክልል አላለም፡፡ ጥሪው የኅብረት የአንድነት ነው፡፡ አሁን ዶ/ር ዓቢይ የእገሌ ድርጅት አይደለም፤ የእገሌ ጎሣ አይደለም፤ የእገሌ ሃይማኖት አይደለም፤ የእገሌ አካባቢ አይደለም፤ የሚወዳቸውና የሚኮራባቸው እናቱም አይደለም፡፡ ከመቶ ሚሊየን በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ እና የአገራችን ገጽና ወኪል መሆኑን ከንግግሩ አንድምታ መረዳት ይቻላል፡፡

ለጠ/ሚኒስትር ዓቢይ ከየአቅጣጨው (ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጭምር) የጎረፈለት የጥያቄ ዓይነት፣ አንዳንዱም በትእዛዝ መልክ ይህን በቅድሚያ መፈጸም አለብህ በማለት ያስቀመጣቸው ዝርዝሮችን በመታዘብ መልክ አይቻቼዋለሁ፡፡ የአንዳንዱ ጥያቄ ዶ/ር ዓቢይ የሕዝብ ትግል ውጤት ነህና አቅምህ በፈቀደ መጠን ጥያቄአችንን መልስልን ከሚል ቅንነት የመነጨ፣ አንዳንዱ በተቃዋሚዎች ኅብረት ማጣትና ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ለማስተባበር ባለመቻላቸው ተስፋ በመቁረጥ፣ ሌላው ደግሞ በስንፍናው ያልሠራውን የቤት ሥራ በአቋራጭ መንገድ ተፈጽሞለት የድል አጥቢያ አርበኛ ሆኖ ብቅ ለማለት ወዘተ. ይመስላል፡፡ ያም ሆነ ይህ አብዛኛው ሕዝብ ዘንድ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በቃሉ እንደሚገኝ ተስፋ ያደረገውን ያህል ሥጋቱንም ሲያንፀባርቅ ይሰማል፡፡ አብዛኛው የሚጋራው ሥጋት አገራችን ለሕወሓት ተጠሪ በሆነው ቅጥረኛ የወታደራዊ እዝ ስር ሆና፣ ወያኔ ሠራዊቱንና ደኅንነቱን የግሉ ንብረት ባደረገበት፣ ቁልፍ መንግሥታዊ ተቋማትን በራሱ ጎሣ ባሰባሰባቸው ታማኞች በተያዘበት እና ቁልፍ የኢኮኖሚ አውታሮችን በተቆጣጠረበት ሁኔታ ጠ/ሚኒስትሩ ምን መላወሻ ያገኛል? ሥልጣኑ ሰይፍ አልባ ነው፡፡ የሚለው ይመስለኛል፡፡ በሌሎች አስተያየቶቼ ደጋግሜ እንደገለጽኩት የወንበዴውን የሕውሓት አገዛዝ እስከመጨረሻው ከማያምኑ ወገኖች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ወያኔ ጊዜያዊ ማሸለብ አደረገ (አደፈጠ) እንጂ አላንቀላፋም፡፡ ቀስቱን ኹሉ ወርውሮ የጨረሰ ቢሆንም ህልውናውን ያቆየባቸው ጉልበት፣ መከፋፈል እና የሐሰት መረጃዎችን መንዛት በቀጣይም ከመጠቀም ወደኋላ አይልም፡፡ ወያኔ በሚዘረጋው የመከፋፈያ ወጥመድ ውስጥ ዳግም እንዳንገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡

ስለሆነም አሁን የተፈጠረው ዕድል እንዳይመክን ከተፈለገ (በጠ/ሚኒስትሩ በኩል ያለው ዝግጅት እንደተጠበቀ ሆኖ) በአገር ቤት የምንገኝና በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ክፍተት ሳንፈጥር ታሪክ ለሕዝብ መሣሪያ እንዲሆን ያዘጋጀውን ወጣት ‹መሪ› ኹለንተናዊ ድጋፍ ልንሰጠው ይገባል፡፡ የዚህ ድጋፍ ዋና መገለጫው ወያኔ ከሰው በታች አዋርዶ የገፈፈንን የዜግነት መብትና ክብር ለማስመለስ በአራቱም ማዕዘናት የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በስብሶ ወደመርዝነት የተቀየረውን ወያኔ ወደታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ለማስወገድ ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የምናደርገው ሕዝባዊ እምቢተኝነት/ተቃውሞ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻልን ጸያሔ ፍኖት ዶ/ር ዓቢይ የመንግድ አቅኒነት ሚናውን በሚገባ መወጣት ይችላል፡፡ ጥያቄአችንም (‹እጅህ ከምን› በማለት የጠየቅነው) ተገቢውን መልስ እንዲሚያገኝ እምነታችን የጸና ይሆናል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዓቢይን የምንፈትነው እኛ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ከሆንን ብቻ ነው፡፡ ሕዝቡም በተቃውሞው፣ ዓቢይ ተቀናቃኝ ያላቸው ተቃዋሚዎችም ኢትዮጵያን ለመታደግ ኅብረት ሲፈጥሩና የሕዝብን ትግል ማስተባበር ሲችሉ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ትግሉ በዋናነት የዐቢይ ብቻ ሳይሆን የኹላችን ነው፡፡ ወያኔ ለጥፋት ቀን ከሌት ሲያሤር ሲዶልት፤ እኛ አገራችንን እና ሕዝባችንን ለመታደግ ግማሹን ያህል እንኳን ጥረት ማድረግ እንዴት ይሳነናል?

አምላከ ኢትዮጵያ ለወንድማችን ዐቢይ ጥበቡንና ማስተዋሉን ያድለው፡፡ በባርነት ስለማቀቅንበትን ዘመነ እኪት (መከራ) ፈንታ ነፃነት ደስታን ለምንጎናጸፍበት ዘመነ ትንሣኤ ያብቃን፡፡

Filed in: Amharic