>

ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም ከአዲሱ ጠ/ሚ/ር አፋጣኝ የሆነ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሾችን እንሻለን !!! (ሰማያዊ ፓርቲ)

                                                 ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ከቅርብ አመታት ወዲህ በመላ አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሰደድ እሳት የተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ገዢውን ፓርቲ ብርቱ መቀራቀር ውስጥ እንደከተተው ይታወቃል፡፡ የህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አገሪቱን በተደጋጋሚ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እያዋለ የዜጐችን ደም ማፍሰሱን፣ በጅምላ ማሰሩን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መጣሱን ተያይዞታል፡፡ ይሁን እንጂ ሕዝባዊ ትግሉ የመንግስት አፈና ከቶውንም አላስቆመውም ፡፡ በተለይም የወጣቱ ትውልድ የነገ አገር ተረካቢነት ተስፋ ፅልመት ያጠላበት መሆኑን መገንዘብና ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን ምላሽ፰ መስጠት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ሰማያዊ ፓርቲ በጽኑ ያምናል ፤ ለዚህም ተግቶ ይሰራል ፡፡
በቅርቡ የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ ተከትሎ የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች ለሣምንታት ሲመክሩ ከሰነበቱ በኋላ የኦህዴድን ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድን የግንባሩ ሊቀመንበር በማድረግ መድበዋል፡፡ ይህ ምደባ ሕዝባዊ ቅቡልነቱ ጥያቄ ውስጥ በገባው የአገሪቱ ፓርላማም ጠቅላይ ሚኒስትርንነታቸውን አረጋግጦ ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ንግግር አድርገዋል፡፡ በእርግጥ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 27 ዓመታት አምባገነናዊ አገዛዙ ካደረሰበት እጅግ የከፋ ስቃይ አንፃር አሁን የሚነሳው ጥያቄ ሥርዓቱን የመጠገን ሳይሆን ስርዓቱን የመለወጥ ነው፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ ምንግስት እንዲቋቋም፣ ከአፋኝ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ሠላማዊ በሆነ መንገድ አሁንም አጠናክሮ ይቀጥላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚ/ር ሆነው የተመደብት የዶክተር አብይ አህመድን ንግግር ፓርቲያችን ሰማያዊ አፅንኦት በመስጠት አድምጦታል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚ/ር በንግግራቸው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባማከለ መልኩ ማለትም ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ አርሶ አደሩን፣ ዲያስፖራውን፣ባለሀብቶችን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማህበራትን ወ.ዘ.ተ ለመዳሰስ ሞክረዋል ፡፡ ንግግራቸው ኢትዮጵያዊነትን በፍቅር ከማቀንቀን ጋር ተያይዞ ዘመን ተሻጋሪ ታሪኮችን በማጣቀስ ፣በፀና አንድነት ላይ መቆም እንደሚገባ ጥሪ ማስተላለፋቸው ከተለመደው  ከኢህአዴግ ንግርት ውጪ መሆኑ ሰማያዊ ፓርቲ በእጅጉ ያደንቃል ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በፍጥነት መቀረፍ አለባቸው ያሏቸው ጉዳዮችም ጠቃቅሰዋል፡፡
ስር የሰደደውና ሥርዓቱን ያነቀዘውን ሙስና ኮንነዋል፡፡ በአገሪቱ ዲሞክራሲን ማስፈን ተገቢ እንደሆነና ዴሞክራሲም ያለነፃነት የማይታሰብ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ የመደራጀትና የመሰብሰብ መብቶች ሊከበሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ሕዝቡ አገልጋዩን የመተቸት መብት፤ መንግስትም ህግን የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ጠቃቅሰዋል፡፡ በተለይም ከፍትህ ጋር በተያያዘ የሕግ መኖር ብቻ ፍትህን እንደማያሰፍንና ለፍትህ የቆመ የሕግ አካል በጠንካራ መሠረት ላይ እንደሚገነባና የፍትህ ተቋማቱም ገለልተኛ ሆነው የሕግ የበላይነት እውን እንዲሆን አሁን የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ቃል ገብተዋል፡፡
በተለይም ሙስናን እና ሙሰኞችን በተመለከተ ጠንካራ ሃሳብ ሠንዝረዋል፡፡ አንዱ ሰርቶ ሌላው ቀምቶ የሚኖርባት አገር ልትሆን እንደማይገባ እና የሕዝቡን ብሶት ያጋጋለው የሙስና መንሰራፋት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ባለመስፈኑ ህዝብን እንዳስኮረፈውም ገልፀዋል፡፡ እንደ ጨው ዘር በመላ ምድርቱ የተበታተነው ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራም ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲያለማና  በአገሪቱ መፃኢ እድል ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍ ጥሪ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተቃዋሚ ሳይሆን ተፎካካሪ መሆናቸውን ከጠቀሱ በኋላ እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠላት ሳይሆኑ ለዚህች አገር ሁለንተናዊነት አማራጭ ሀሳብ አንግበው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው ፍትሃዊ የሆነ የመወዳደሪያ ሜዳው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰፋ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ የጠቅላይ ሚኒሲትሩን ንግግሮች በበጎ ጎን በመመልከት ቃላቸውን ካከበሩ እና ለሕዝብ የገቡትን ቃል ኪዳን የሚፈጽሙ ከሆነ ለአገራችን ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥ የሚረዳ በመሆኑ ፓርቲያችን የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡
1ኛ. የአዲሱ ጠቅላይ ሚ/ር ንግግር ውሃ የሚቋጥርና ሚዛን የሚደፋ ቢሆንም ችግሩ መሬት ወርዶ በተግባር መተርጎሙ ላይ ጥርጣሬያችንን መግለፅ እንሻለን፡፡ በአገሪቱ ከተፈጠረው ብርቱ ችግር የአዲስ አመት መግቢያ ላይ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከህዝባዊ እምቢተኝነቱ መጠንከር የተነሳ ህገመንግስትን እስከማሻሻል ለማድረስ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ቢገልፁም ችግሩ በጊዜው ረገብ እንዳለ የገቡትን ቃል ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲሱ ጠቅላይ ሚ/ር የገቡትን ቃል በተለይም አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ሲቪክ ማህበራትን በጠረጴዛ ዙሪያ በማቀራረብ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ የሆነው ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አለባቸው እንላለ፡፡ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ ጉዳይ ለሚያደርጋቸው ማንቸውም ጥሪ እና እንቅስቃሴ ጠ/ሚ አስፈላጊውን ትብብር እና ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል በማለት ጥሪ እንስተላልፋለን ፡፡
2ኛ. የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠላት ሳይሆኑ ለዚህች አገር ሁለንተናዊነት አማራጭ ሀሳብ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው በማለት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት በገቡት ቃል መሠረት፣ ቃላቸውን ይተገብሩ ዘንድ በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ የህሊናና የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ በሙሉ በመፍታት ከወዲሁ ጥሪጊያ መንገዱን ሊያመቻቹ ይገባል እንላለን፡፡
3ኛ. በወቅት አገሪቱ ላይ የተጫነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ጥያቄና ህዝባዊ እምቢተኝነት ችግር ፈቺ ምላሽ መስጠት የሚችል አይደለም፡፡ከዚህ አንፃር አዲሱ ጠ/ሚ/ር ሥራቸውን በይፋ በጀመሩ ቀናት  ይህንን አፋኝ አዋጅ በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እንዲያነሱ በአፅንኦት እንጠይቃለን፡፡
4ኛ. በመንግስት ቸልተኝነት እና የአስተዳዳር በደል ምክንያት ብቻ በተፈጠረው አለመግብብት ከመላ አገሪቱ በተለያየ አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሰው እንዲቋቋሙ አዲሱ ጠ/ሚ/ር ትልቅ አላፊነት አለባቸው፡፡ዜጎቻችንን ለዚህ ችግር የዳረጉ የመንግስት ሹመኞች በበደሉት መጠን በፍትህ ሊዳኙ ይገባል እንላለን ፡፡
5ኛ. የፍትህ ተቋማትና ምርጫ ቦርድን የመሳሰሉ ለመድበለ ፓርቲ መጠንከር እና ሊዴሞክራሲና ለፍትሕ እድገት ዋንኛ ማኖቆ በመሆን  በገዢው ፓርቲ ጉልበት ሥር የተንበረከኩ መሆናቸው የማይካድ ሀቅ ነው ፡፡ይህም በመሆኑ እነኚህ ተቋማት በአዲስ መልክ ተዋቅረው በነፃነት ህዝብን እንዲያገለግሉ ማድረግ ይጠበቃል፡፡
6ኛ. ነፃና ገለልተኛ ብዙሃን መገናኛዎች በሌሉበት ህዝብን ማገልገል ከቶውንም አዳጋች ነው፡፡ ያሉትም ብዙሃን መገናኛዎች ቢሆኑም በገዢው ፓርቲ የእጅ ጥምዘዛ ተደፍቀው የሚገኙ ናቸው ፡፡ ከዚህ አንፃር ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ያለምንም ጫና ሊያገለግሉ የሚችሉ ብዙሀን መገናኛዎችን መፍጠር የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን መግለፅ እንሻለን፡፡
በመጨረሻም አዲሱ ጠቅላይ ሚ/ር አገራዊ መግባባትን በመፍጠር፣ ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድረድር ተከሂዶ ከአፋኝ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን የለውጥ ሂደት በመደገፍ ፣ከሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲቋቋም በታማኝነት ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ፤ ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን በድምና በአጥንታቸው ባቆዩልን፤ እኛም ያሁን ትውልዶች ለነገ አገር ተረካቢ ትውልድ ክብሯና ታሪኳን  ለማስተላለፍ አለንልሽ በምንላት በእናት ሃገራችን ኢትዮጵያ ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን ፡፡
“ ኢትዮጵያ በነፃነትና በክብር ለዘላለም ትኖራለች ! ”
መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic