>

ሽግሽግ እንጂ ሽግግር የለም!!! (መሳይ መኮንን)

አንድ አባባል ነው። በአገዛዙ ሚዲያዎች በሚቀርቡ እንግዶች፡ በጋዜጠኞቹም እየተደጋገመ ይጠራል። ከውጭ ወደ ሀገር ቤት በሚተላለፉ ሚዲያዎች ላይ በተለያዩ እንግዶች እየተነሳ ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርም በመጀመሪያው ቀን አፋቸውን ሞልተው”ለአፍሪካ ተምሳሌት” ሲሉት ሰማሁ። የህወሀት መሪዎች በቤተመንግስት በተደረገ የእራት ግብዣ ላይ በሰልፍ ሆነው ”የመጀመሪያው” እያሉ ሲጠሩት ሰምቼ በሀፍረት ጥፍሬ ውስጥ መደበቅ ነበር የቀረኝ። አቶ ለማ መገርሳም በፈገግታ ተሞልተው ይህንኑ ሲሉት ነበር። …….”በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ሰላማዊ የሰልጣን ሽግግር”
የህወሀት ሚዲያዎች ዘንግተውት ነው እንጂ በ1985 አቶ መለስ ዜናዊ ዋናውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ሲጨብጡ ፕሬዝዳንትነቱን ለዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ያስረከቡ ጊዜ ”በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር” እያሉ ሲያደነቁሩን ነበር። አሁንም ”የመጀመሪያው……” እያሉ ነው። ደጋግመው ሲጠሩት የእውነት አስመሰሉት። ወግ መቼም አይቀርም።
የሆነው በአጭሩ እንዲህ ነው። እንደ ህወሀት ሁለት መጥፎ ምርጫዎች ቀረቡለት። በአጭር ጊዜ ጠራርጎ የሚያጠፋውን የህዝብ ማዕበል መጠበቅ ወይስ ለዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መስጠት። ሁለቱም ለህወሀት መጥፎ ምርጫዎች ነበሩ። ከበጣም መጥፎ፡ የተሻለ መጥፎን ይመርጥ ዘንድ ግድ ሆነበት። የዶ/ር አብይን ጠቅላይ ሚኒስትርነት መቀበል የተሻለ መጥፎ ምርጫ ነበር። ቢያንስ ትንፋሽ ይሰጣል። ያኛው ማዕበሉ ግን አስፈሪ ነው። ምንም ሳያስቀር ጠራርጎ ያጠፋል። ጊዜ አይሰጥም። ለህውሀት የዶ/ር አብይ መምጣትም ቢሆን ጊዜያዊ እፎይታን እንጂ ዘላቂ መረጋጋትን አያመጣለትም። ህወሀት አከርካሪው ተሰብሯል። እያቃሰተ ትንሽ ጊዜ ይቆይ እንደሁ እንጂ ዕድሜም የለውም። ቢያንስ ግን የተሻለ መጥፎ በመምረጥ ለጊዜው ከአስፈሪው ማዕበል ተርፏል።
እናም ሽግሽግ እንጂ ሽግግር የለም!!!
Filed in: Amharic