>

እስረኞቹን ለፋሲካ! (ደረጄ ደስታ)

የአስቸኳይ አዋጁ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ በሳምንቱ መገባደጃ መግለጫ ሰጥተዋል። እንደ መግለጫው በ6ቱ የኮማንድ ፖስት ቀጠናዎች 1ሺ 107 ሰዎች ታስረዋል፡፡ የታሰሩበትም ምክንያትን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን “ወንጀሎች” ፈጽመው በመገኘታቸው ነው። እነ እስክንድርና አንዷለም የትኛውን ፈጽመው ይሆን?
1. በጸጥታ ኃይልና ሰላማዊ ዜጋ ግድያ ወንጀል
2. ቤት በማቃጠል
3. የመንግሥትና ህዝባዊ ተቋማትን በማጥቃት
4. ተሸክርካሪዎችን በማውደምና መንገድ በመዝጋት
5. የመማር ማስተማር ሂደትን በማስተጓጎል
6. የንግድ እንቅስቃሴን መግታት
7. ዶክመንት ማጉደል
8. ህገወጦችን መሣሪያዎችን በማዘዋወር
9. ብሔርን ከብሔር በማጋጫት
10. አመጽና ሁከትን በማነሳሳት ….
ከእነዚህ ውጭ የተዘረዘሩ የወንጀል አይነቶች የሉም። ታዲያ ጥፋታቸው በዚህ ውስጥ ካልተካተተ ወይ አላጣፉም ወይም የታሰሩት በአስቸኳይ አዋጁ አይደለም ማለት ነው።
የኮማንድ ፖስቱን ሰዎች ለምን አትጠይቋቸውም ብዬው ነበር አንድ ወዳጄን። አዬ እነሱንማ የት ታገኛቸዋለህ፣ እነሱ ሲፈልጉህ ያገኙሃል እንጂ አንተ ፈልገህ አታገኛቸውም- ብሎኛል። ዶ/ር አብይ እንደሚያገኟቸው ተስፋ እናዳርጋለን። እስረኞቹ ፋሲካን ከቤተሰባቸው ጋር እንደሚውሉም እንጠብቃለን። ሰላማዊ ትግልና ይቅርባይነትን የሰበኩ እንደ እስክንድር ነጋ እና አንዷለም አራጌ ዓይነት ሰዎች በመታሰራቸው መንግሥታቸው እሚያተርፈው ነገር አይኖርም። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳላሰሯቸው ብናውቅም ከማሰር ይልቅ መፍታት እሚችለው ትልቅ ባለሥልጣን መሆኑንም እናውቃለን። ማሰርና መፍታቱ የህግና የሥርዓት ሳይሆን በመንግሥት ፍላጎት ብቻ እሚፈጸም የእብሪት ተግባር መሆኑንም አይተናል። ጀግንነታቸውን በጀብደኝነታቸው ያውም ምንም አቅም በሌላቸው እስርና ግፍ ባደቀቃቸው ሰዎች ላይ ማዋላቸው እሚያሳዝንና ለመንግሥታቸውም እማይበጅ መሆኑንም ጠቅላይ  ምኒስትሩ በስብሰባቸው አንስተው እንደሚከራከሩ እንጠብቃለን። መቸም ለማዘዙ ገና ናቸው ብለን ጊዜ አውሰናቸዋል። ይህኛው ግን ጊዜ አይሰጥም!
Filed in: Amharic