>
5:16 pm - Wednesday May 24, 0609

ዶ/ር አብይ አህመድና እግዚአብሔር የወሰነለት ዘመን (የኪዳን ሰው)

ከፀሐይ በታች ለሚታቀድ፣ ለሚሰራና ለሚሆን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የወሰነለት ዘመንና ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፣ ለመሞትም እንዲሁ፤ ለመትከል ጊዜ አለው፣ ለመንቀልም ጊዜ አለው። ለመግደል ጊዜ አለው፣ ለመፈወስም ጊዜ አለው፣ ለመገንባት ጊዜ አለው፣ ለማፍረስም ጊዜ አለው። ለማልቀስ ጊዜ አለው፣ ለመሳቅም ጊዜ አለው፣ ለሃዘን ጊዜ አለው፣ ለመጨፈርም ጊዜ አለው። ድንጋይ ለመበተን ጊዜ አለው፣ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፣ ለማቀፍ ጊዜ አለው፣ ለመለያየትም ጊዜ አለው። ለመቅደድ ጊዜ አለው፣ ለመስፋትም ጊዜ አለው፣ ለዝምታ ጊዜ አለው፣ ለንግግርም ጊዜ አለው። ለመውደድ ጊዜ አለው፣ ለመጥላትም ጊዜ አለው፣ ለጦርነት ጊዜ አለው፣ ለሰላምም ጊዜ አለው።
እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር በጊዜ ውብ አድርጎ ሰርቶታል፣ ዘላለማዊነትንም በሰው ልቦና አሳድሯል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሰራውን ሁሉ እስከ መጨረሻ ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው እውቀት ሙሉ አይደለም። ስለዚህ ሰው በህይወት እያለ መልካም ነገር ከማድረግና ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የተሻለ ነገር እንደሌለ ሊያውውቅ ይገባል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ዶ/ር አብይ አህመድ በአገራችን ያለውን የፍርድ መጓደል፣ ግፍ፣ የፍትህ እጦት፣ የነፃነት እጦት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እጦት ለማስወገድ፣ የተገፉ ጭቁኖችን ለማፅናናትና ለመታደግ ብሎም እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለዚች ታላቅና ታሪካዊ አገር ለማምጣት እግዚአብሔር በሰጣቸው ዘመን ሁሉ የገቡትን ቃል በመፈፀም ኢትዮጵያን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ሚናፍቀው የነፃነትና የብልፅግና ዘመን ጋር ማገናኘት አለባቸው።
ዶ/ር አብይ አህመድ በበዓለ ሹመታቸው እለት ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ነፍስ ከመቆጣጠሩም በላይ በምድሪቷ ላይ ያንዣበበውን የመከራ ደመና ገፎታል፣ የጥላቻ ነጎድጓዱን አጥፍቶታል፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ስጋቱን እስከ ወዲያኛው አምክኖታል፣ የወያኔን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሴራ ዳግም እንዳይነሳ አድርጎ ቀብሮታል፣ በሙት መንፈስ ራዕይ ስትታመስ የኖረችውን አገራችንን በህያዋን መንፈሶች ሞልቷታል። የዚህ አንደበተ ርቱዕ ወጣት ቃል በሽተኞችን ፈውሷል፣ የእውሮችን ዓይን አብርቷል፣ አንካሶችን አዘልሏል፣ የተዘጉ በሮችን ከፍቷል፣ በትውልዱ ትከሻ ላይ በተንኮል የተቀመጠውን የዘር ቡትቶ አቃጥሏል፣ የጥላቻና የመለያየት ሰባኪዎችን አንገት አስደፍቷል፣ የፍትህ ፣ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ሰባኪዎችን ተስፋ አለምልሟል፣ ጉልበታቸውን አጠንክሯል፣ ህልማቸውንም በድል አሻግሮ አሳይቷል። ይህ ወጣት መሪ ምትሃታዊ ነው፣ የትግራይ ከሃዲዎች ኢትዮጵያዊነትን ማወደስ አማራን ማንገስ መስሎ ስለሚታያቸው ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አዋርደው ትግራዊነትን ባገነኑበት መድረክ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሃዘንና እምባ የወለደው ኢትዮጵያዊ ሙሴ ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያዊነትን እስከ ሰማዬ ሰማያት አግኖታል፣ የአባቶቻችን አኩሩ ገድል በክብር ዘክሮታል፣ የመጪው ዘመንን ብሩህ ተስፋ ለትውልዱ በፍቅር አሻግሮ አሳይቷል። በመሆኑም በእኔ አይታ ኢትዮጵያ ዛሬ ከጠላቶቿ መዳፍ ወጥታ ከትክክለኛ መሪዋ ጋር ተገናኝታለች ብዬ አምናለሁ።
በመሆኑም ዶ/ር አብይ አህመድ እግዚአብሔር በወሰነለት ዘመን ኢትዮጵያ የተባለችን ታላቅና ታሪካዊ አገር ለመምራት ታላቅ እድል አግኝቷል፣ እጣም ወድቆበታል። ቀሪው ዘመን የሚሆነው የገባውን ተስፋ ሳይሸራርፍ፣ በፍቅር ያወደሳትን ኢትዮጵያ ሳያስደፍር፣ ጎንበስ ብሎ በትህትና የተሳለመውን ታላቅ ህዝብ ሳያሳፍር፣ የተንኮለኞችን የክፋት መረብ እየበጣጠሰ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚናፍቁትን የነፃነት ቀን ለማምጣት የለውጡን ባቡር ማፍጠን አለበት። ምክንያቱም ለዶ/ር አብይ አህመድ እግዚአብሔር የወሰነለት ዘመን የምድሪቷን ቀንበር ለመሰባበር፣ የዘረኝነትን መሰረት ለመናድ፣ የኡትዮጵያ ጠላቶችን አንገት ለመቁረጥ፣ የኢትዮጵያዊያንን ነገ በተስፋ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በነፃነት የተሞላ ለማድረግ ነው።
______________________________
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፣ ዳርቻዋንም ያስፋልን!!
ተዶ/ር አብይ አህመድ ስኬት የሚለካው በገባው ቃል ፍፃሜ ነው!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
Filed in: Amharic