>

የወያኔን  የጫካ ትግል «እነ ዶክተር ዓብይን ለማንገሥ የተከፈለ መስዕዋትነት» ሲባል ሰማሁ ልበል?  (አቻምየለህ ታምሩ)

ወያኔዎችና አክራሪ የተከዘ ማዶ ብሔርተኞች ጦፈዋል። የማሕበረሰብ ሜዲያው ካድሬዎችማ  ለቅሶ ተቀምጠው ሙሾ እያወረዱ ናቸው። በጦርነት የተጎዱ የሕወሓት የገበሬ ወታደሮችን ፎቶ እያሳዩ «እነ ዶክተር ዓብይን ለማንገስ የተከፈለ መስዕዋትነት» እያሉን ናቸው።  እዚያ መንደር እሳ የሚባል ነገር ስለሌለ ልካቸውን አለማወቃቸው አያስገርም ይሆናል!  በሕይወት ያለን ሰዎች አይናችን እየተመለከተ ትናንትና የነበረው እውነት ዛሬ ተቀይሮ አዲስና ያልነበረ ታሪክ በግፈኞች ሲደረት  ግን ዝም ብለን አናይም። ወያኔም ሆነ «የትግራይ ሕዝብ» ደርግን ለመጣልና እነ ዶክተር ዓብይን ለማንገስ የጀመሩት አንዳች ትግል የለም።
ለምን ይዋሻል ወያኔም ሆነ «የትግራይ ሕዝብ»  ከፈልን  የሚሉንን መስዕዋትነት የከፈሉት  አማራን አጥፍተው «ቅኝ ገዢ» ከሚሏት ኢትዮጵያ ነጻ ወጥተው የታላቋ ትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ነው። ይህንን አላማ ትግል ሲጀምሩ በጻፉትና እስከ ኢሕአዴግ ምስረታ [1981ዓ.ም.] ድረስ ወያኔን ያስተዳድሩበት በነበረው ፍኖተ መርህ [manifesto] ላይ በግልጽ አስቀምጠውታል። የወያኔ የነፍስ አባት የሆነው ኢሳያስ አፈወርቂም በ1990 ዓ.ም. ባደረገው ንግግር ወያኔ ለዚህ አላማ እንደተፈጠረ ነግሮናል።
ወያኔ ከ1967—1981 ዓ.ም. በተዳደረበት የትግል ማኒፌስቶ ሲገለበጥ «የትግራይ ብሔራዊ ጭቆና እና በደል አስቆጥቶ ጭቆናውንና በደሉን ከሥሩ ለመንቀል የፖለቲካና የትጥቅ ትግል መጀመሩን» ያትትና የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል የመጀመረበትን አላማ ፤«የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ፀረ-የአማራ ብሔራዊ ጭቆና፣ ፀረ-ኢምፐርያሊዝም እንዲሁም ፀረ-ንኡስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው። ስለዚህ የአብዮታዊው ትግል ዓላማ ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፐርያሊዝም ነፃ የሆነ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ማቋቋም ይሆናል።» ሲል ይነግረናል።
ስለዚህ ወያኔና «የትግራይ ሕዝብ»  ጫካ ወርዶ እነ ዶክተር ዓብይን ለማንገስ የተከፈለ መስዕዋትነት ከፍሏል  እያላችሁ ያልዋላችሁበትን  በመደስኮር  አታደንቁሩን! ባጭሩ  ሕወሓት የታገለው ለኤርትራ ነጻነትና የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመስረት እንጂ  በኢትዮጵያ መንበረ መንግሥት ማንንም ለማንገሥ አልነበረም። If at all እነ ዶክተር ዓብይን ለማንገስ መስዕዋትነት ተከፈለ ከተባለ የተከፈለው መስዕዋትነት የኦሮሞና የአማራ ልጆች  ደምና አጥንት እንጂ   የሕወሓት ታጋዮች ሕይወት አይደለም። የሕወሓት ታጋዮች ደምና አጥንት የፈሰሰው ኤርትራን ለማስገንጠልና የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ብቻ ነው።
እኔ እንደሚመስለኝ ወያኔዎችና አክራሪ የተከዘ ማዶ ብሔርተኞች ለቅሶ እንዲቀመጡ ያደረጋቸው እውነተኛው ምክንያት  «ታላቁ መሪ» የሚሉት የቅያቸው ልጅ  የሆነው መሪያቸው መለስ ዜናዊ  ያላገኘውን ክብር ዓብይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በማግኘቱ ይመስለኛል። ዓብይ አሕመድ ስለ ኢትዮጵያ በተናገረው ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በኋላ ስለኢትዮጵያችን  አንድ የኢትዮጵያ መሪ እንዲህ ሲል  ተናገረ ብለን ልንጠቅሰው  የምንችለውን ድንቅ  ንግግር ያደረገ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ «መሪ» ይመስለኛል። ዶክተር ዓብይ አሕመድ «ኢሕአዴግነቱ» እስኪረሳ ድረስ የሕዝብ ክብር ያተረፈው መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መጥራት ተጠይፎ  «አገሪቱ፣ አገርቱ፣ አገሪቱ»  እያለ ዝቅ ሲያደርጋት የኖራትን አገር   «ኢትዮጵያ አገራችን» ፣ «ኢትዮጵያችን»፣ «ስንኖት ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ የምንሆንባት» እያለ  ስንት ጀግኖች መስዕዋት የሆኑላትን ኢትዮጵያ ባለፉት አርባ አራት አመታት ሰምተነው በማናውቀው ሁኔታ  ከፍ አድርጎ ስላከበራት ነው።
ዓብይ አሕመድ በንግግሩ  የካራማራ ጀግኖችን  በክብር ማንሳቱ  ወያኔዎችን   ሳያስቆጣ  የቀረ አይመስለኝም።  እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ካራማራ ላይ አፈር ሲሆኑ  እነ መለስ ዜናዊ የሶማሊያ ፓስፖርት ይዘው ከጠላታችን ከሶማሊያው መሪ ከዚያድባሬ ጋር  በመሆን ኢትዮጵያን  ሲወጉን እንደነበር መቼም የሚዘነጋ አይደለም።  ወደፊት  በምናትማቸው ዶሴዎች የወያኔው አለቃ መለስ ዜናዊና  የኢሕአፓው አምበል  ክፍሉ ታደሰ የካራማራ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ይዘውት ይንቀሳቀሱት የነበረውን  የሶማሊያ ፓስፖርት ይዘን መውጣታችን አይቀርም።
« ስም ዓላማና ሥራ ገላጭ ነው» እንዲሉ ወያኔ ወይንም ሕወሓት ትናንትናም ሆነ ዛሬ የሚታገለው  ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖርና  እነ ዶክተር ዓብይን ለማንገስ ሳይሆን  ሕወሓት የሚለው የነጻ አውጭ ስሙ እንደሚነግረን  ኢትዮጵያውያንን በተለይም አማራና ኦሮሞን እሳትና ጭድ አድርጎ በጎሳ አጥር የምትተራመስ ኢትዮጵያን ፈጥሮ  ከመረብ እስከ ባሮ የተዘረጋች ታላቋን የትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት ነው።  ወያኔና «የትግራይ ሕዝብ» ያካሄዱት ትግል አላማ ከታች በተለጠፈው ማኒፌስቷቸውና የነፍስ አባታቸው የሆነው ኢሳያስ አፈወርቂም  በአንድ ወቅት በሰጠው ንግግር በግልጽ ተቀምጧል! እነሆ ሁሉም ዶሴው!
Filed in: Amharic