>

አብይ አህመድ፡ የቆሰለውን የህወሀት አውሬ በእራሱ የመጫወቻ ካርታ ሲረታው! (ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

(ክፍል 1) 

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ 

Original post in English available here: https://goo.gl/Rvm82i

ለኢትዮጵያ አቦሸማኔው (አዲሱ ትውልድ) ማሳሰቢያ፡ 

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ነገር የአገዛዝ ለውጥ እንጅ የአገዛዝ የወንበር መቀያየር ጨዋታ አይደለም፡፡ የሚያስፈልገው ነገር ስርነቀል ለውጥ ነው፤ ከወሮበላ ዘራፊ አምባገነናዊነት የጠነባ ስርዓት ወደ መሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ፡፡ የሚያስፈልገው ነገር የሙስናን ባህል፣ የዝምድና እና የጓደኝነት አሰራርን እና አድሏዊነትን ሊያከስም የሚችል እመርታዊ የስርዓት ለውጥ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ነገር በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን የሚፈጽሙ እና በሙስና የሚዘፈቁ ዋልጌዎችን ለሕግ ተጠያቂ ማድረግ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስፈልገው ነገር ደግሞ የሕዝባዊ እምቢተኝነት እና የአይበገሬነት ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እና ላቅ ባለ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡

ሁሉም ነገር እየተፈጸመ ያለው በቅን ልቦና ታስቦ ሕዝብን ለመጥቀም ሳይሆን ለታዕይታ፣ ርካሽ ተደናቂነትን ለማትረፍ እና የሕዝብ ትኩረትን ለመሳብ ብቻ የሚደረግ የመድረክ ላይ ተውኔት ነው!

ለዚህም ነው የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት (ወጣቱ ትውልድ) ሰላማዊ ትግሉን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረው መቀጠል ያለባቸው፡፡ ይኸ ያካሄድ ስልት ነው አብይ አህመድ ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችለው ብቸኛው የመድህን ፖሊሲ፣ ብቸኛው ዋስትና፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ ነው የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) አውሬ በእራሱ የመጫወቻ ካርታ ሊረታ የሚችለው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረግ ላይ የሚገኝ እንጅ በመሸነፍ ላይ ያለመሆኑ በውል ሊጤን እና ሊታወስ ይገባል፡፡

መግቢያ

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን ይፋ የስነስርዓት ዕለት መነሻ በማድረግ “ግልጽ ማሳሰቢያ” በሚል ርዕስ በተከታታይ ለማቀርበው ጽሁፍ ይህ የመጀመሪያው ክፍል ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው (ወጣት) ትውልድ አባላት እና 70 በመቶ የሚሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል ድምጽ የሚወክሉት ወጣቶች ምኞታቸውን ለማሳካት ይህንን መልካም ዕድል በማግኘታቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ (ወጣቱ ትውልድ) በአምባገነኖች ጉልበት እና ትዕቢት ጸጥ ማለት የማይችል፣ ለነጻነቱ እና ለመብቱ ቀናኢ ሆኖ አይበገሬነቱን በማሳየቱ እራሴን አኩርቻለሁ፡፡ የወጣቱ ኃይል በአሁኑ ጊዜ እንዲህ እንደሚታየው የተጠናከረ ኃይል ባልነበረበት ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ስለኢትዮጵያ ወጣቶች መብት ስከራከር እና እምነቴን ሳራምድ ቆይቻለሁ፡፡

እ.ኤ.አ በ2005 ተካሂዶ በነበረው ሀገር አቀፍ የይስሙላ የቅርጫ ምርጫ መለስ ዜናዊ በጠራራ ጸሐይ የሕዝቡን ድምጽ በመዝረፉ ተበሳጭተው ተቃውሟቸውን ያሰሙትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለብሩህ ተስፋ ወጣቶችን በጥይት እያስጨፈጨፈ ጭዳ በማድረጉ ምክንያት በብስጭት በመነሳሳት የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ሆኛለሁ፡፡ መለስ ያረዳቸውን የብሩህ ተስፋ ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉትን እምቦቃቅላ ወጣቶች በስም አስታውሳለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እነዚያን የብሩህ ተስፋ ባለቤት የነበሩትን ወጣቶች የፈጁትን ቅጥር ነብሰ ገዳዮች በስም አውቃቸዋለሁ፡፡

በተለያዩ ጊዚያት በተለያዩ አጋጣሚዎች “የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት ተባበሩ፣ በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) በፍጹም እንዳትሸነፉ!” በማለት በድፍረት አውጃለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየተሰራ ያለው ታሪክ በኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ ላይ የነበረኝን ጽኑ እምነት እንዳረጋገጠልኝ አምናለሁ፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገራቸውን ከጠነባ አምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሚለውጡ እና የእራሳቸውን ዕድል በእራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ያለኝን ጽኑ እምነት በተለያዩ አጋጣሚዎች ስገልጽ ቆይቻለሁ፡፡

ከብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውቅያኖሶችን በማቋረጥ ለኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት እንዲህ የሚል “በጠርሙስ ውስጥ ያለ መልዕክት” ልኪያለሁ፤ “ነጻ ሆናችሁ ተወልዳችኋል! ነጻ ሆናችሁ መኖር አለባችሁ!  ነጻ ሆናችሁ እንዳትኖሩ ታሪክ ፈርጃችህዋል!“

የአብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የመመረጡን ሁኔታ በልዩ ሁኔታ እመለከተዋለሁ፡፡

ከኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት ግፊት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንጻር የተፈጸመ ክስተት አድርጌ እመለከተዋለሁ፡፡

ለእኔ ጥያቄው ምን እንዳስብ ወይም ደግሞ ምን እንደምመርጥ አይደለም፡፡ በእርግጥ ጉዳዩ ስለእኔ ሁኔታ ወይም ስለእኔ የትውልድ አባላት ጉዳይ አይደለም፡፡

ለእኔ ብቸኛው ጥያቄ የአብይ አህመድ ሚና በይስሙላ እና በተግባር ለኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ ምንን እንደሚወክል የማየት ጉዳይ ነው፡፡

የአብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የመመረጥ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አቦሸማኔው ትውልድ አነቃቂ ምልክት በመሆኑ ደስታ የተሰማኝ ሲሆን የጥንካሬ ስንቅም ሆኖኛል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጂኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) የጂኒ ጠርሙስ ተሰብሯል፡፡ የዘ-ህወሀትም ቅስም እንዳይጠገን ሆኖ ተሰብሯል፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) የዙፋን የትውልድ ርስት የሌለው መሆኑን አብይ አህመድ የኦሮሞን፣ አማራን፣ ጉራጌን፣ ሶማሊን፣ አፋርን…ልጆች በመወከል ያመላክታል፡፡ እነዚህ ልጆች ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ጀኔራል፣ ሚሊየኒየር ወይም ደግሞ ሌላ የሚፈልጉትን ነገር መሆን ይችላሉ፡፡ ነጻ የመሆን፣ ነጻ ሆኖ የመኖር፣ በነጻነት የእራሳቸውን መንግስት የመምረጥ እና በሀገራቸው ውስጥ በክብር የመኖር  እና አንደኛ ደረጃ ዜጋ ሆነው የመኖር የትውልድ መብት አላቸው፡፡

የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ

የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ የቆሰለውን የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) በእራሱ የመጫወቻ ካርታ ጨዋታ ረቶታል፡፡

የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት በአሁኑ ጊዜ የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) እግሮቹ ሸክላ የሆኑ የቆሰለ አውሬ መሆኑን በጠራራ ጸሐይ መመልከት ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን (ዘ-ህወሀት) ከእግራቸው ስር ለማንበርከክ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን እና ሰላማዊ ተቃውሞን ተጠቅመዋል፡፡ ሕዝባዊ እና እልህ አስጨራሽ የሆነ ሰላማዊ ተቃውሞ ሃያል የተባለውን እና እጅግ ጨቋኝ አገዛዝ ሊያሸንፍ ይችላል፡፡ የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) የእጁን አግኝቷል ምክንያቱም የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት በየእለቱ በሕዝባዊ ተቃውሞ ተጠምደው ቆይተዋል፡፡

አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚል ስያሜ አግኝቷል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት ሌት እና ቀን፣ ሳምንት ከሳምንት እና ዓመት ከዓመት በሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) ላይ ባሰደሩበት ጫና ምክንያት ብቻ ነው፡፡

የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ (ዘ-ህወሀት) አለቆች አፍንጫቸውን ተሰንገው መሆናቸውን ክደው እርሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን የፈቀዱ ለማስመሰል ዲስኩራቸውን በመንዛት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም ግልጽ በሆነ መንገድ በአብይ አህመድ ላይ የንቀት አስተያት በማራመድ እርሱ ምንም ማድረግ የማይችል ትንሽ አድርገው ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ውድድሩ እራሳቸውን በፈቃዳቸው እንዳገለሉ እና ምክንያቱ ደግሞ ቦታውን የማይፈልጉት እንደሆነ አድርገው የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን ያገኘው ይህንን ስልጣን ማንም የሚፈልገው የሌለ በመሆኑ ነው በማለት ላይ ናቸው፡፡ ለማያውቁሽ ታጠኝ ወይም ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ መሆኑ ነው፡፡

አብይ አህመድን በአጋጣሚ እንደሾሙት አድርገው በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡ እንዲያውም በሕጉ መሰረት ድምጽ አግኝቶ አይደለም ምርጫውን ያሸነፈው ይላሉ፡፡

እርሱን መሾምም ሆነ ላለመሾም እንደሚችሉ ደረታቸውን ነፍተው ይናገራሉ፡፡

በመሰረቱ አንድ የዘ-ህወሀት የበታች አለቃ አጠቃላይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫ ሂደቱ የፖለቲካ ተውኔት የተካሄደበት ውስብስብ ጨዋታ ነው በማለት ተናግሯል፡፡

የዘ-ህወሀት የበታች አለቃ እና ዓለም አቀፍ ሴሰኝነትን አሳዳጁ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በከተማው ውስጥ አንድ ጨዋታ ብቻ አለ በማለት አምባርቋል፡፡ ይህም ዘ-ህወሀት በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥበት የአፓርታይድ የዘር ፖለቲካ ጨዋታ መሆኑ ነው፡፡

ዘ-ህወሀት የዘር ፖለቲካ ጨዋታ ሕጉን ያዘጋጃል፣ ተጨዋቾቹን ይሰይማል፣ ዳኝነቱን ይመራል፣ የገቡትን ግቦች ይቆጥራል፣ ከዚያም አሸናፊውን ያውጃል፡፡

ደብረጽዮን አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን ቢይዝም ምንም ዓይነት የሚለወጥ ነገር የለም ምክንያቱም ዘ-ህወሀት የወታደሩን፣ የደህንነት ኃይሉን፣ ኢኮኖሚውን፣ ቢሮክራሲውን እና የመንግስት ሰራተኛውን በበላይነት ተቆጣጥሯል የሚል እንደምታ ያለው መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንም ይሁን ማን ችግር የለውም ምክንያቱም ያለዘ-ህወሀት ፈቃድ ምንም የሚሆን ነገር የለም፡፡

አስተሳሰበ ትንሹ እና ዘረኛው ደብረጽዮን የተበሳጨ ላለመምሰል ስሜቱን በማፈን በአብይ የምርጫ ሂደት ላይ እንዲህ ብሏል፣

“ሶስት ሰዎችን እንዲሁ በዘፈቀደ መረጥን፡፡ ምርጫን ለማካሄድ ከታገልንለት በላይ ያልተለመደ ሂደት ነበር፡፡ እኔ ከእጩ ተጠቋሚዎች አንዱ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን እኔ ተጠቋሚ መሆን አልችልም በማለት እራሴን ተቃወምኩ፡፡ እራሴ እንዳልመረጥ በእራሴ ላይ ዘመቻ ጀመርኩ፡፡ ከሁለት ወራት በፊት የትግራይ ክልልን በበላይነት እንድመራ ተሾሜ ነበር፡፡ የክልሉን ሕዝብ ማክበር አለብን፡፡ 

[የአብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የመመረጥ ጉዳይን በሚመለከት…እንደምታውቀው ይህ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ የድርጅታችን ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም በአንድ ላይ ሆነን ውሳኔ እናሳልፋለን፡፡ ለአንድ ሰው ብቻ ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁን ያለውን የተለመደውን የጋራ አመራር የመስጠት ባህላችንን አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል“ ብሏል፡፡

የሸክስፒርን ጥቅስ በመውሰድ “ድምጹን ከፍ አድርጎ በሚጮህ እና በተበሳጨ አንደበት በሚናገር አስተሳሰቡ ዝቅተኛ በሆነ ሰው የተነገረ ተረት ምን የሚፈይደው ነገር ይኖራል?“

ወይም ደግሞ ሰውን ለማናደድ እየጣረ ያለው እና የሚመኘውን ያጣው ሰው ዋና ተሸናፊ ነውን? እውነት በሚመስል መልኩ ደብረጽዮን ከ180 ድምጽ ውስጥ ያገኘው 2 ብቻ ነው፡፡

ደብረጽዮን መፍቻ ቁልፍ በሚያስፈልገው መልኩ በሚስጥር እየተናገረ ነውን?

ደብረጽዮን በሚናገረው ንግግር ውስጥ ምን ወእንደሚል ይገባናል፡ አባባሉም እንደዚህ ነው።

አትሳሳቱ! ዘ-ህወሀት አብይ አህመድን የእርሱ አድርጎታል፡፡ እንደተነገረው ይሰራል፡፡ እራሱን በተለመደው የጋራ ውሳኔ የመስጠት ሂደት ውስጥ ያስቀምጣል፣ እናም በዚህ እንይዘዋለን፡፡ ወደላይ እንዲዘል እንነግረዋለን፣ እናም ብቸኛው ምላሹ የሚሆነው ምን ያህል ከፍታ ልዝለል የሚል ይሆናል፡፡ በኃይለማርያም ደሳለኝ ላይ እንዳደረግነው ሁሉ እርሱንም አሻንጉሊት እናደርገዋለን፡፡ ተስፋችሁን አታጥፉ፡፡ ምንም የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ እስከዘላለም እኛ የአፓርታይድ ጌቶቻችሁ ነን!

ደብረጽዮን እንዲህ እየተናገረ ያለው በእራሱ አንደበት ከውስጡ በመነጨ መልኩ ነው ወይስ ደግሞ በልዩ ትዕዛዝ በአለቆቹ ይህንን እንዲናገር ታዝዞ ነው?

እኔ ስለዚህ ጉዳይ አላውቅም፣ ጉዳየም አይደለም።

ደብረጽዮን የተለመደውን ዓይነት እርባናቢስ ንግግር ለአድማጮቹ በጆሯቸው በማንሾካሾክ ላይ ነው፡፡ ከፍ ያለ ድምጽ እና ንዴት የተቀላቀለበት እርባና ቢስ ንግግር፡፡

ያም ሆነ ይህ ለእኔ ትልቁ ዋናው ቁምነገር አብይ አህመድ በሚያሰራጨው የጭላንጭል ብርሀን አማካይነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት አብዮች፣ ለማ መገርሳዎች፣ እስክንድር ነጋዎች፣ አንዷለም አራጌዎች፣ እማዋይሽ ዓለሙዎች ርዕዮት ዓለሙዎች እና ሌሎችም በርካታዎቹ ዕንቁ የኢትዮጵያ ልጆች በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በእራስ የመተማመን ስሜት እና ኃይል የመጨመር ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ፣ በላያቸው ላይ ማንም ሳይሾምባቸው በነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ በእራሳቸው መብት ተጠቅመው የፖለቲካ ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ጨምሮ መያዝ እንደሚችሉ የሚያሳይ እውነታ ነው፡፡

ለእኔ በአብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሚና የዘ-ህወሀት የጭቆና አገዛዝ የመጨረሻ ምእራፍ የሚዘጋበት እና አዲስ አይነት የሕዝብ መንግስት በኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ በሕዝብ ለሕዝብ የሚጀመርበት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚጻፍበት ጊዜ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት ነጻ እና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ የእራሳቸውን መሪ መምረጥ በሚችሉበት ጊዜ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ይሆናል።

ስለሆነም በጨለማው የዘ-ህወሀት አገዛዝ ዳመና ላይ ለታዕይታነትም ቢሆን አብይ አህመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ደረጃ ከፍ በማለቱ ደስተኛ ነኝ ምክንያቱም የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት የእራሳቸውን መንግስት በነጻ በመምረጥ በነጻ መኖር እንደሚችሉ ተጨባጭ ተስፋ የሚሰጥ ክስተት ነውና፡፡

አብይ አህመድ የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ መሪ በመሆኑ ምንም በማያጠራጥር መልኩ ሙሉ ድጋፌን እሰጠዋለሁ፡፡ ተደጋግሞ ሲነገር የሚሰለች ቢመስልም የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ የኢትዮጵያ የወደፊት አለኝታዎች ናቸው፡፡

ሊታወስ ይገባል…

ይህ ትውስታ በዋናነት ለኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ የተላለፈ ነው፡፡ ማስታወሻውን እንደሚያገኙት እና በጥንቃቄ እንደሚመረምሩት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ለዚህ ተከታታይነት ላለው ትችት ግልጽ ደብዳቤ በማለት ፋንታ በትውስታ መልክ ማስቀመጡን የመረጥኩት፡፡ በዋናው የላቲን አገላለጽ ትውስታነት “memorandum est“ ማለት መታወስ አለበት ማለት ነው…

የወደፊቷን ኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ እንደማስበው ከሆነ የዘ-ህወሀትን የተዛባ አገዛዝ፣ ስህተት እና ያለፉትን የ27 ዓመታት ዕድለ ቢስ ክስተቶች ማስታወስ አለብኝ፡፡

27 ዓመታት ለመሙላት አንድ ወር አካባቢ ከቀረው በኋላ እንኳ የቆሰለው አውሬ ዘ-ህወሀት ስልታዊ ማፈግፈግ በማደረግ ላይ እንጅ በመሸነፍ ላይ አይደለም፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ የአቦሸማኔን ትውልድ ኃይለኛ ምት አስተናግዷል፡፡ ሆኖም ግን በሞት ሽረት ትግል ውስጥ እየተንጠራወዘ እስከ አሁንም ድረስ በህይወት አለ፡፡

ላለፉት ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ የአቦሸማኔ ትውልድ አባላት የዘ-ህወሀትን ካንሰር ለመዋጋት የጦር ቀስት ሆነው ቆይተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በማሸነፍ ላይ ናቸው ምክንያቱም ሁለት ጠንካራ የሆኑ መሳሪያዎችን አግኝተዋል፡ እነርሱም ኢትዮጵያዊነት እና ህዝባዊ ተቃውሞ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?

እንዲህ የሚለውን ለማ መገርሳን ጠይቁ፣ “ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ሱስ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለ መንፈስ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ምን እንዳለ ተከፍቶ ሊታይ የሚችልበት መንገድ ቢፈጠር ይኸው በዛሬዋ ዕለት የምናየው ነገር የሚሆነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በዛሬዋ ዕለት እያየነው ያለ ነገር ነው፡፡ የእኛ አንድነት የእኛ ኢትዮጵያዊነት ነው…ኢትዮጵያዊነት ነጻ መሆን ነው“ የሚል መልዕክት ነበር ያስተላለፈው፡፡

እንዲህ የሚለውን ቴዲ አፍሮን ጠይቁ፣ “ኢትዮጵያዊነት በሰውነታችን ውስጥ እንዳለ ኦክስጂን ነው፡፡ በውስጣቸው ኢትዮጵያዊነት ያለባቸው በውስጣቸው ለዘላለም ይኖራል፡፡ ያ ምን ጊዜም ሊጠፋ አይችልም፡፡ እንደ ኃይማኖት ሁሉ የጠለቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በእራሱ ውስብስብ የሆነ ሚስጥር አለው፡፡ ጥልቅ የሆነ መሰረት አለው፡፡ በበርካታ መልካም ነገሮች ላይ ስምምነት ማድረግ ስንችል በጋራ ሆነን በሰራናቸው ጉድለት ያለባቸው ነገሮች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ጠቃሚ አይደለም“ ነበር ያለው፡፡

እንዲህ እያልኩ ያለሁትን እኔን እራሴን ጠይቁ፣ “ፍቅር ዘላለማዊ እንደመሆኑ ሁሉ ኢትዮጵያዊነትም እንደ አልማዝ ዘላለማዊ ነው፡፡“

ከዘ-ህወት የማጭበርበር ጨዋታዎች ማስታወስ እና መማር፣

“ከታሪክ መማር የማይችሉ ስህተቶቻቸውን ይደግማሉ“ ይባላል፡፡

እኔ በበኩሌ ደግሞ እንዲህ እላለሁ፣ “ከዘ-ህወሀት የማጭበረበር ጨዋታዎች የማይማር ሞኝ ነው፡፡“

ከጥቂት ቀናት በፊት የአሜሪካ የቀድሞው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ኃላፊ የነበሩት እና እ.ኤ.አ በ1991 ዓ.ም ዘ-ህወሀት ወደ ስልጣን ማማ ላይ እንዲወጣ ያደረጉት ብቸኛ ተጠያቂው ኸርማን ኮሆን በትዊተር ገጻቸው እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላለፉ፡

“ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፡ ወደ ዴሞክራሲያዊ መሻሻሎች ለመድረስ  ምንም ሳያመነቱ ጠንካራ እርምጃዎችን ይውሰዱ፡፡ የህወሀት የፖለቲካ -ኢኮኖሚ ጠቅላዮች አጭበርባሪዎች እንደሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡ እናም ከትግልዎ የሚያዘናጋዎ ምንም ነገር የለም፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከጎንዎ ነው“ ነበር ያሉት፡፡

ከኸርማን ኮሆን ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፡፡ ሆኖም ግን ሚስተር ኮሆን የ-ዘህወሀት ወንጀለኞች ሰይጣናዊ አጭበርባሪዎች ለመሆናቸው ዝቅ ያለ ግምት የሰጡ ይመስላል፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመቆየት የቻሉት ሕዝቡን በመጨፍጨፍ፣ በማሰር እና በንጹሀን ዜጎች ላይ ስቅይትን በማድረስ ብቻ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሁሉንም ዓይነት የማጭበርበሪያ ጨዋታዎችን በመጫዎት ጭምር ነው፡፡

የዘ-ህወሀትን የቆሰለ አውሬ ለማሸነፍ የተሻለው መንገድ እራሱ ያመጣቸውን የማጭበርበሪያ ጨዋታዎች እና ሸፍጦች በመጠቀም ነው፡፡

ለዚህም ነው ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ የስልጣን ኮርቻ ላይ ለዘላለም ተፈናጥጦ ለመኖር ማለቂያ የሌላቸውን ጨዋታዎች ማስታወስ እና በጥልቀት መገንዘብ አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው፡፡ ከእነዚህ የማጭበርበሪያ ጨዋታዎች መካከል ስልታዊ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትውልድ አባላትን ሞራል ከፍ ለማድረግ እስቲ ለግንዛቤ ያህል ጥቂቶችን ልቃኝ፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለዘላለም ለመኖር ሲሉ የጭንቅላት ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለየ ሁኔታ እነርሱ አዋቂዎች፣ ንቁዎች፣ ጀግናዎች፣ ጠቃሚዎች፣ እና ሀገሪቱን እንደፈለጉ መግዛት የሚችሉ እነርሱ ብቻ መሆናቸውን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመጮህ የጎሳ የበላይነታቸውን ለመመስረት ሲፍጨረጨሩ እና ሲዋትቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ልንማረው የሚገባን ቁም ነገር የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በግንኙት ድረገ ገጽ ከዲፕሎማ እና ዲግሪ መቀፍቀፊያ ማሽን ተቋማት እየገዙ ምሁር ነን እናም አክብሩን የሚሉ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብ ደናቁርት ተራ የጫካ ሽፍታ ከመሆን ያለፈ እንዳልሆነ መታወስ አለበት፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የምርጫ ኮሮጆን የመዝረፍ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 ዓ.ም ለክልሎች ፓርላማ ምርጫ ዘ-ህወሀት ከ1,904 መቀመጫዎች ውስጥ 1,903 መቀመጫዎችን በማጭበርበር አሸነፈ፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም ዘ-ህወሀት ምርጫውን በማጭበርበር 99.6 በመቶ መቀመጫዎችን አሸነፍኩ በማለት ለይስሙላው ፓርላማ አወጀ፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ተሞክሮን በመፈጸም ዘ-ህወሀት ምርጫውን በማጭበርበር ዓይን ባወጣ መልኩ ለይስሙላው ፓርላማ መቶ በመቶ ማሸነፉን አወጀ፡፡ ከዚህ ልንማር የሚገባን ቁም ነገር የሕዝብን ድምጽ በመስረቅ ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት በሌቦች፣ ለሌቦች የተቋቋመ የወሮበላ ዘራፊዎች መንግስት እንደሆነ መታወስ አለበት፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የዜሮ ድምር ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ይህም ማለት ዘ-ህወሀት ሁሉንም ነገር አሸናፊ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ መሬትን መቶ በመቶ ተቆጣጥሯል፡፡ (አንድ የዘ-ህወሀት ፓርቲ አለቃ “ለእኛ ታማኝ ላልሆኑ ሰዎች መሬት አንሰጣቸውም“ ብሏል፡፡) የሀገሪቱን ሕግ የሚያወጣውን ፓርላማ ዘ-ህወሀት መቶ በመቶ ተቆጣጥሯል፡፡ ዘ-ህወሀት ቁልፍ የሆኑ የወታደራዊ አመራር ቦታዎችን፣ የደህንነት አመራር ቦታዎችን፣ ዋና ዋና የንግድ  ድርጅቶችን እና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሥራዎችን እና የፖለቲካ ሹመቶችን መቶ በመቶ ተቆጣጥሯል፡፡ ከዚህ ልንማር የምንችለው ቁም ነገር “ሁሉን ነገር ሁልጊዜ የሚፈልጉ ሁሉ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ያጣሉ“ የሚለው ነገር መታወስ አለበት፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የከፋፍለህ ግዛ ሕጎችን ሲጠቀሙ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ዘ-ህወሀት በኢትዮጵያ ውስጥ የአናሳ ጎሳ አፓርታይድ ስርዓት ለመፍጠር እና ለመንከባከብ በማሰብ የሸፍጥ የጎሳ ፌዴራሊዝምን ፈጥሯል፡፡ የዘ-ህወሀት የጎሳ ፌዴራሊዝም ክልሎች እየተባሉ የሚጠሩ የአፓርታይድ ዓይነት ባንቱስታንን ፈጥሯል፡፡ ዘ-ህወሀት ለ27 ዓመታት ለተቃዋሚዎቹ ፍርፋሪ እየወረወረ እንደተራበ ውሻ ሲታገሉ እየተመለከተ በስልጣን ኮርቻ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ልንማር የሚገባን ቁም ነገር በአሁኑ ጊዜ የተራቡ ውሾች የቆሰለውን አውሬ እንደተቆጡ ተኩላዎች በመክበብ በመጮህ ላይ የሚገኙ መሆኑ መታወስ አለበት፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ ማባበያ ከረሜላዎችን የመስጠት ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ዘ-ህወሀት የሚታገሉ ኦሮሞዎቸችን መሬት እጅግ እርካሽ ፍትሀዊ ባልሆነ ዋጋ እየወሰደ ፍጹም ተቀባይነት በሌለው እጅግ ከፍተኛ ዋጋ እየሸጠ ተመልሰው እንዲመጡ በማድረግ እንዲህ ዓይነት የኦሮሞ ማባበያ ከረሜላዎችን ይሰጣል፡ በመናገሻ ከተማው ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል “ከሊዝ ነጻ  የሆነ መሬት“ መስጠት፣  “የልገሳ፣ ባህላዊ ህንጻዎችን እና የገበያ ቦታዎችን“ መሰየም፣ በከተማ አስተዳደሩ የሚቀርቡትን የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶችን ለመግዛትም ሆነ ለመከራየት 15 በመቶ ለኦሮሚያ ቅድሚያ መስጠት፣ “የሕዝብ አደባባዮችን፣ ማዕከሎችን፣ ስታዲየሞችን የቅድሚያ ተጠቃሚነት መብት“ መስጠት እና ለከተማው የኦሮሞ ኗሪዎች በኦሮምኛ ትምህርት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶችን ማቋቋም የሚሉት ይገኙበታል፡፡ ከዚህ ልንማር የምንችለው ቁም ነገር መሬት የሌላቸው ሰዎች ምንም የሚያጡት ነገር የለም፣ እናም ያጡትን መሬት ለማስመለስ መታገል ወይም በመታገል መሞት እንደሚኖርባቸው መታወስ አለበት፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን በማወጅ ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ዘ-ህወሀት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃል ምክንያቱም ሁልጊዜም እንደ ሰርገኛ ጤፍ አንድ ሆነው መለየት የማይቻሉት ኦሮሞዎች እና አማሮች ህብረት ሲፈጥሩ ስለሚፈራ ነው፡፡ ለማ መገርሳ ዘ-ህወሀትን እንዲህ በማለት  አስተምሮታል፣ “ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ እንደተለመደው የምግብ እህል እንደ ጎመን ዘር ፍሬ ጥቃቅን የሆነው እንደ ሰርገኛ ጤፍ እና በምጣድ ላይ ተጋግሮ እንደሚበላው እንጀራ እየተባለ እንደሚጠራው ናቸው፡፡ በአንድ ላይ ያሉ እህሎች ናቸው፣ በአንድነት ይፈጫሉ፣ እናም በአንድነት ይበላሉ“ ብሏል፡፡ ዘ-ህወሀት ከደረሰበት የመጨረሻ ተስፋ የመቁረጥ ድርጊት እና እራሱን ለማቆየት እና ከአጠቃላይ ውድቀት ለመዳን ሲል ሶስት (አንደኛው የታደሰውን ጨምሮ) የአስቸኳ ጊዜ አዋጆችን አውጇል፡፡ ከዚህ ልንማር የምንችለው ቁም ነገር የዘ-ህወሀት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ጥንካሬን ወይም የኃይል ሚዛንን አያመላክቱም፡፡ ሆኖም ግን በከፍተኛ አለቆች እና በተራ ወታደሮች መካከል ያለው ጥልቅ የሆነ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ሽብር እራስን መቆጣጠር የማያስችል ፍርሀት መኖሩን ነው፡፡ ዘ-ህወሀት ይገድላል ምክንያቱም በሞት ፍርሀት ተዘፍቋልና፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የዘር ፍጅት ይመጣል የሚል ጨዋታ ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ የዘ-ህወሀት ሸፍጠኞች ወደፊት ኢትዮጵያውያንን ሊያጠፋ የሚችል የእርስ በእርስ እልቂት ይመጣል በማለት ሁልጊዜ የጎሳ ማስፈራሪያውን ማስመሰያ ያቀርባሉ፡፡ አሁን በህይወት የሌለው የዘ-ህወሀት አውሬ አለቃ መለስ ዜናዊ ህወሀት ከሌለ በሩዋንዳ የሁቱ ሚሊሻዎች የቱትሲ ጎሳዎችን እንደጨረሷቸው ያለ ኢንተርሀሞይ በኢትዮጵያም ላይ ይመጣል እያለ ያስፈራራ እና ያሟርት ነበር፡፡ ዜናዊ ይህንን የዘር ፍጅት ትንበያውን በየጊዜው ይደጋግመው ነበር፡፡ የመለስ ጓደኛ የሆነው በረከት ስምኦን እንደ ህጻን ጨዋታ  “በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች መካከል የሚካሄደው ጥላቻ የርዋንዳን ዓይነት የዘር መተላለቅ ያስከትላል“ በማለት ተንብዩአል፡፡ የዘ-ህወሀት ጀኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ ዘ-ህወሀት የታሪክ ቆሻሻ ሆኖ ወደ ታሪክ  ቆሻሻ ማከማቻ ቅርጫት ለመጣል እየተዘጋጀ ባለበት ሁኔታ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደሚኖር በቀጥታ ተንብዮአል፡፡ የዘ-ህወሀት አለቃ አባይ ጸሀዬ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ርዋንዳ ትሆናለች በማለት ተንብዮአል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ እና ኢትዮጵያ ቀጣዩ ርዋንዳ ወደምትሆንበት መንገድ እየሄደች ነው ብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሌላው የዘ-ህወሀት አለቃ ስዩም መስፍን የእርስ በእርስ ጦርነት እንደሚኖር እና ዘ-ህወሀት ተቃዋሚዎችን ሁሉንም ጨፍልቆ የበላይነቱን አስጠብቆ እንደሚቀጥል ተንብዮአል፡፡ በአንድ አዲስ በሆነ ቃለ መጠይቅ ስዩም ኢትዮጵያውያንን በጀርመን ሶስተኛ ግዛት እንደነበረው እንደ ናዚ፣ ትግራዮችን ደግሞ ከአይሁዶች ጋር እኩል አድርጎ አቅርቧል፡፡ የዘ-ህወሀት የክርስትና አባት የሆነው ሸባው ስብሀት ነጋ ብቻ ትክክል ነው፡፡ “ሕዝብ ሲታፈን እና ሲያመር ይፈነዳል፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ነው፡፡ ካላመረረ በስተቀር የሚያምጽ ሕዝብ አሁንም፣ በታሪክም የለም፣ ወደፊትም አይኖርም፡፡“ ከዚህ ልንማር የምንችለው ቁም ነገር የኢትዮጵያዊነት ደም በኢትዮጵያውያን የደም ስር ውስጥ እስከተዘዋወረ ድረስ ምንም ዓይነት የኢትዮጵያውያን የዘር ፍጅት አይኖርም ሊኖር የሚችለው በሌላው ስሙ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር እንጅ፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የመረጃ ማዛባት፣ የፕሮፓጋንዳ እና የሕዝብን ቀልብ የማስቀየስ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ጠላትነትን እና ጥላቻን ለመፍጠር ዘ-ህወሀት አማሮች እና አሮሞዎች ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው እናም ቅንነት ያለው መቀራረብ እና አንድነት ሊፈጥሩ አይችሉም የሚል የተዛባ መረጃ ያሰራጫሉ፡፡ አማራ እና ኦሮሞ እንደ ዘይት እና ውኃ እሳትን ጭድ ናቸው በማለት በተዛባ መልኩ ሕዝብን ለማሳመን የተዛባ የመረጃ ዘመቻ አካሂደዋል፡፡ ዘ-ህወሀት የአማራ እና የኦሮሞ ህብረት በትግራይ ላይ የርዋንዳ ዓይነት ኢንተርሀሞይ ሊያስከትል ይችላል የሚል የተዛባ መረጃ አሰራጭቷል፡፡ ከዚህ ልንማር የምንችለው ቁም ነገር ኦሮሞዎች እና አማሮች ለሺህ ዓመታት በሰላም በአንድነት ኖረዋል፡፡ ለማ መገርሳ እንዳለው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደ ሰርገኛ ጤፍ ናቸው፡፡ ሰው በመሆናቸው ብቻ ይተባበራሉ እናም በጎሳ ሊለያዩ አይችሉም፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የድርድር ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ዘ-ህወሀት ከተቃዋሚዎች መካከል ለእርሱ ታማኝ ተቃዋሚ የሆኑትን በመለየት ኑ እንደራደር በማለት ለድርድር ይቀመጣል፡፡ ዘ-ህወሀት ተቃዋሚዎችን ከሀገሪቱ ለዘላለም ለማጥፋት በትጋት ይሰራል፡፡ ከዚህ ለመማር የምንችለው ቁም ነገር ከዘ-ህወሀት ጋር የሚደራደሩት የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ለእራት ምንድን (ለማን) መዘጋጀት እንዳለበት ለመወያየት ከጅብ ጋር ተሰብስበው እንደሚደራደሩ የአጋዘን መሪዎች ናቸው፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የይቅርታ ጥያቄ ጨዋታዎችን የማቅረብ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ ዘ-ህወሀት ንጹሀን ዜጎችን የሽብር ወንጀል ሰርታችኋልና ይቅርታ ጠይቃችሁ ከእስር ቤት ውጡ ይላቸዋል፡፡ በፍጹም ባልሰሩት ወንጀል በግዴታ ይቅርታ ጠይቁ በማለት ዘ-ህወሀት ንጹሀኑ ዜጎች ጥፋተኛ እንደሆኑ የማስመሰል ሙከራውን እያደረገ በሌላ ጊዜ ሲፈልግ ይቅርታውን ጥሰዋል በማለት እንደገና ወደ እስር ቤት ወስዶ ሊያጉራቸው ይችላል፡፡ ከዚህ ለመማር የምንችለው ቁም ነገር እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ እና ሌሎች በርካታዎቹ ከዚህ አንጻር ምን እንዳደረጉ መገንዘብ ነው፡፡ ዘ-ህወሀት ይቅርታ የሚለዉን ጨዋታ እራሱ ይጫወጥበት፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ ስልጣንን በፈቃድ የመልቀቅ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ የዘ-ህወሀት አቅጣጫ አስቀያሾች በአንድ ጊዜ የስራ መልቀቂያ የማቀረብ እና ወዲያዉኑ ደግሞ የስራ መልቀቁ ጉዳይ ይሰረዝ እና ያንኑ ስራ መቀጠላቸውን በመተግበር የተካኑ ናቸው፡፡ ከስክሮዲንገር ድመት ፖለቲካ ጋር መሳ ለመሳ ናቸው፡፡ ሕዝቡን ለማሳመን እና እውነተኛ ለውጥ  የሚያመጡ ለማስመሰል የስልጣን መልቀቂያ የማቅረብ ጫዋታዎችን ይጫወታሉ፡፡ ከዚህ ለማመር የምንችለው ቁም ነገር የዘ-ህወሀትን አሻንጉሊት በሌላ መሰል አሻንጉሊት በመተካት የሚታለልላቸው ማንም ሰው እንደሌለ እንዲገነዘቡ ነው፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የቅጥረኛ ወታደሮችን በማሰማራት ሕዝብን እያስፈጁ የኮማንድ ፖስት አዋጅ ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ ደህንነት (Global Security) ዘገባ ከሆነ ዘ-ህወሀት ተጠሪነታቸው ለዘ-ህወሀት ጥቂት የበላይ አመራሮች የሆኑ የእራሱን የግል ቅጥር ነብሰ ገዳዮች  በማሰማራት የመደበኛውን ወታደር የሚመስሉ ሆኖም ግን ያልሆኑ አጋዚ የሚባል ቡድን በማቋቋም ሕዝብን በመፍጀት ላይ እንደሚገኝ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ የዚህ ቅጥር ነብሰ ገዳይ ቡድን ህልውና ዋና ዓላማውም በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ምንም ዓይነት የስልጣን ተቀናቃኝ እንዳይኖረው ለመጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ለመማር የምንችለው ቁም ነገር የአጋዚ ቅጥር ነብሰ ገዳይ ቡድን ወይም የዘ-ህወሀት የወታደራዊ እና የደህንነት ኃይሎች የኢትዮጵያን የአቦሸማኔ ትውልድ ሰላማዊ የትግል ተቃውሞ ማሸነፍ እንደማይችሉ ነው፡፡

የዘ-ህወሀት ልዩ ጨዋታ፣

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ደግሞ የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች በስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጥጠው ለመቆየት እና እና የጎሳ አፓርታይድ ስርዓታቸውን ለማጠናከር ሲሉ የፖለቲካ እስረኞችን የመልቅ እና የማሰር ጨዋታዎችን ሲጫወቱ መቆየታቸው መታወስ አለበት፡፡

ዘ-ህወሀት እስክንድር ነጋን፣ አንዷለም አራጌን፣ ተመስገን ደሳለኝን እና ሌሎች በርካታዎችን እንደገና ያሰረ ለምንድን ነው? መልሱ ቀላል ነው፡ የዩኤስ ኮንግረስ ኤች.አር. 128 (H.R. 128) በተባለው የሕግ ረቂቅ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ዕቅድ ስለያዘ ያንን ለመበቀል ታስቦ ነው፡፡

እ.ኤ.አ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ ሚክ ኮፍማን ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማስታወቂያ ከተቀበሉ በኋላ የተወካዮች ምክር ቤት ኤች.አር. 128 በተባለው የሕግ ሰነድ ላይ በዚህ በሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ውስጥ ውሳኔ ይሰጥበታል የሚል መረጃ ለቀዋል፡፡ እ.ኤ.አ መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዘ-ህወሀት በቅርቡ የተፈቱትን እና  ከፍተኛ ታዋቂነት ያላቸውን በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እንደገና በቁጥጥር ስር በማዋል አስሯቸዋል፡፡ የቀድሞ የፖለቲካ እስረኞችን እንደገና በማሰር ዘ-ህወሀት ለዩኤስ ኮንግረስ እንዲህ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ፈልጓል፣ “የፈጋችሁትን ነገር ብታደርጉ ደንታችን አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁንም ድረስ እኛ የጎሳ አፓርታይድ አለቆች ነን፡፡ እስቲ ምን ታረጋላቸሁ!?፡፡ ዘ-ህወሀት መርሳት የማይገባው ነገር ቢኖር ዉሻ የምያበላዉን እጅ አይነክስም እንዲሉ ነው።

ይህንን ትችት እየጻፍኩ ባለሁበት ጊዜ ዘ-ህወሀት በሸራተን አዲስ ሆቴል አዲስ የብሄራዊ የሰላም ፌስቲቫል ጨዋታ በመጫወት ላይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከታዳሚው ከፍተኛ የሆነ ነቀፌታን አስተናግደዋል፡፡ ተሳታፊዎች ዘ-ህወሀት ኢትዮጵያዊነትን እንዲያቅፍ እና የጥላቻ እና የልዩነት ፖለቲካን እንዲያቆም ጠይቀዋል፡፡ ዘ-ህወሀት አንድ ወይም ሁለት ጨዋታዎችን ለመጫወት ያስባል፣ ሆኖም ግን ከዚህ በኋላ ጨዋታው ተጠናቋል፡፡

ዘ-ህወሀት ላለፉት 27 ዓመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት ማንኛውንም መስዋዕትነት እየከፈለ የማታለያ ጨዋታዎችን ሲጫወት የቆየ መሆኑ ሊታወስ ይገባል፡፡ ዘ-ህወሀት እንዲህ የሚል አንድ እና አንድ ተልዕኮ ብቻ አለው፣ “አሁን እንደአሉበት ሁኔታ በተመሳሳይ መልኩ ለአንድ ተጨማሪ ቀን፣ ለአንድ ተጨማሪ ሳምንት፣ ለአንድ ተጨማሪ ወር ለአንድ ተጨማሪ ዓመት፣ ለአንድ ተጨማሪ አስርት ዓመት… በስልጣን ላይ መቆየት፡፡“ ከዚህ ለመማር የምንችለው ቁም ነገር የዘ-ህወሀት ጨዋታው ተጠናቆበታል! የሚል ነው፡፡

ዘ–ህወሀት እ.ኤ.አ በ2018 አዲስ ጨዋታ ወይም ደግሞ አሮጌውን ጨዋታ በሂደት ይጫወታል፡፡

ዘ-ህወሀት ጨዋታው የተጠናቀቀ መሆኑን ያውቃል፡፡ ግን እውነት ነውን?

ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እንደማውቀው የዘ-ህወሀት ሸፍጠኛ አጭበርባሪዎች በጨዋታ ላይ ከቆሻሻ ላይ ተዘርረው ይወድቃሉ፣ አፈር ልሰው ይነሳሉ እንደገና ኳስ ጨዋታውን ይቀጥላሉ፡፡

ዘ-ህወሀት ከዚህ ቀደም ለብዙ ጊዜ ሲጫወት እንደቆየው ሁሉ አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በመሾም ለብዙ ጊዜ መጫወት ይችላልን?

ዘ-ህወሀት የአብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመቀበል እንደ ቀድሞው ሁሉ የፖለቲካ እግር ክዋስ ጨዋታውን ለመቀጠል ዝግጁ ነውን?

ላለፉት ሶስት ዓመታት የዘ-ህወሀት አታላዮች እና አጭበርባሪዎች የኢትዮጵያን አቦሸማኔ ትውልድ (ወጣት ትውልድ) ሊግ ለማሸነፍ የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል፡፡ ሁሉንም ነገር ሞክረዋል፡ ግድያን፣ እስራትን እና ማሰቃየትን ጨምሮ፡፡ አቦሸመኔዎቹ በመምጣት ላይ መሆናቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ ወጣቶቹ በእያንዳንዱ መንደር፣ ትንሽ መንደር እና ከተማ ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ ዘ-ህወሀት በፍጹም ሊያሸንፍ አይችልም፡፡

ዘ-ህወሀት ለ90 ደቂቃ ያህል ሲያካሂድ የነበረውን ጨዋታ ጨርሷል እናም ጀርባውን ወደ ጎል መለያ ምልክቶች አዙሮ ቆሟል፡፡ በወሳኝነት ለማሸነፍ በማሰብ አሁን 30 ደቂቃ በተጨማሪነት ለመጨዋት ይፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ እንደማይችል ስለሚያውቅ በቅጣት ምት ለማሸነፍ ተስፋ ያደርጋል፡፡ በቅጣት ምት፡፡ ማለቴ የቅጣት ምት በኤኬ 47 እና በከባድ መሳሪያ፡፡

እንግዲህ እ.ኤ.አ በ2016 አቅርቤው በነበረው ክፍል አራት “ምንድን እንፈልጋለን እና አሁን ምንድን እያደረግን ነው ምንስ ዕድል አለን?“ በሚል ርዕስ የቀረበውን ትችት መሰረት በማድረግ እና ከዚያም የተሰነዘሩ ምልከታዎችን በመያዝ አሁን ለኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ ግልጽ ማሳሰቢያ በሚል ርዕስ ያዘጋጀሁትን ከፍል 1 ጽሁፍ በዚሁ እደመድማለሁ፡፡

በአሁኑ ጊዜ በአንድነት በመስራት የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ወሮበላ የዘራፊ ቡድን ስብስብን (ዘ-ህወሀት) ከስልጣን በማስወገድ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ልንመሰርት የምንችልበት የተለየ ምቹ ዕድል አለን፡፡ ሆኖም ግን ለእኔ አስቸጋሪው ጥያቄ ጊዜውን በአግባቡ እንጠቀምበታለን ወይ? ብረቱ እንደጋለ እንቀጠቅጣለን ወይስ ደግሞ ያው የተለመደውን አሮጌ ልምድ በመያዝ ያለፈውን ዕድል ላለማጣት አሁን የተገኘውን ዕድል እናጣለን? የሚለው ነው፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነኝ እና የሚያብሰለስለኝ ነገር ህብረትን በማጣት የገኘውን መልካም አጋጣሚ እንዳናጣው ነው!

ባለፉት አስርት ዓመታት በተቃዋሚዎች እና (ዘ-ህወሀትንም ጨምሮ) እኔ በግሌ የተመለከትኩት እውነታ ቢኖር የተገኘ መልካም ዕድልን ላለማጣት መልካም ዕድልን ማጣት የለብንም የሚለውን ነገር ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ ትክክል እንዲሆኑ እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች በትክክል እንዲሰሩ በርካታ መልካም አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ሆኖም ግን በየጊዜው የተገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ስናመክነው ይታያል፡፡

ይህንን እስቲ የበለጠ ግልጽ በማደረግ ላፍታታው፡፡ ባለፉት አስርት ዓመታት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህብረት በመፍጠር የኢትዮጵያን ሕዝብ ለምርጫ ተሳትፎ እና ሌሎች የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርግ አንቀሳቅሰውት ነበር፡፡ በአንድ ድምጽ ለመናገር የነበራቸው ጽናት እጅግ በጣም የሚደነቅ ነበር፡፡ ያ አንድ ዓይነት ድምጽ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተስፋዎች እና ፍላጎቶች በማነሳሳት በዘ-ህወሀት ልብ ውስጥ ፍርሀት እና ድንጋጤን ፈጥሮ  እንዲርድ አድርጎት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያ ህብረት የዴሞክራሲ እና የነጻነት ፍንጣቂን አምጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያ ሁሉ እንቅስቃሴ እድሜው አጭር ሆኖ ቀረ፡፡ እነዚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ ህብረት የመምጣታቸው ሁኔታ በተመሳሳይ መልኩ መፈረካከሳቸውም በፈጣን ሁኔታ ነበር፡፡ ያ ህብረት ጠንካራ ሆኖ እና የተባበረ ሆኖ ቢቀጥል ኖሮ ዘ-ህወሀት በአሁኑ ጊዜ በሚገባው የታሪክ ቆሻሻ ላይ ተጥሎ በቀረ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ግላዊ የስልጣን ጉጉት ባላቸው የስልጣን ጥመኞች ዘ-ህወሀት ሰርስሮ በመግባት ኃይል በማሳጣት እንዲበታተኑ አደረገ፡፡ የስልጣን ጥማት ያላቸው ግለሰቦች የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋጋ እንዲከፍል አደረጉ፡፡ እነዚህን ሰዎች ታሪክ ለይቅርታ የሚያበቃቸው ይሆን? ያም ሆነ ይህ ያ ጊዜ የትውልድ መልካም አጋጣሚ ያመለጠበት ሆኖ ሲታወስ ይኖራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ጎሳ አቀፍ እና የኃይማኖት ጥምረት ያካተተ ብዙሀን በአንድ ወገን ሆኖ ዘ-ህወሀትን በማስፈራራት እና በልቡ ውስጥ ሽብር በመፍጠር ግራ ሲያጋባው ዘ-ህወሀት የአስቸኳይ ጊዜ በማወጅ በዚያ ውስጥ ተወሽቆ ይገኛል፡፡ የሕዝባዊ እምቢተኝነቱ መንፈስ፣ ተስፋ እና አመጽ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ፊት በጉልህ ሲንጸባረቅ በዘ-ህወሀት ላይ ደግሞ የህመም እና የመድከም መንፈስ ይስተዋላል፡፡ የመተባበር እና አንድ የመሆን መንፈስ ዘ-ህወሀትን በየጊዜው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እያወጣ በጦር ኃይል ተንጠልጥሎ እንዲቀመጥ አድርጎታል፡፡ ጊዜው አሁን ነው እናም ከዋክብቶቹ በአንድ ላይ ሆነው በመተባበር ዘ-ህወሀትን ታግለው ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ሌላ የህይወት ዘመን መልካም አጋጣሚ የምናጣ ይመስላል፡፡ በተለይም እኛ በዲያስፖራው ጎራ የተሰለፍነው ወገኖች በዘር የመደራጀትን ጠቃሚነት እያስተጋባን እንገኛለን፡፡ በዘር እየተቧደነ እንዴት ተደርጎ ወደ አንድነት መስመር እንደሚመጣ የሚያቀርቡት መፍትሄ የለም፡፡ እራሳቸውን የዘር ፖለቲካ ጌቶች እና ሻምፒዮን አድርገው የሰየሙት ወገኖች መርዛማ የጥላቻ እና የበቀል መርዛቸውን በመርጨት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ እነዚህ እራሳቸውን የጎሳ ጌታ አድርገው የሰየሙ ሰዎች የስልጣን ሱሰኞች እና የፖለቲካ አታላዮች የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆኖ የፖለቲካ ቀልድ በመቀለድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን በቅርቡ በዩኤስ አሜሪካ የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዚህ ዓይነት ተጻራሪ ሁኔታ ነው፡፡

የጎሳ ልዩነትን እና የኃይማኖት ጽንፈኝነትን የሚሰብኩትን አካሎች ዘ-ህወሀትን አጥብቀን የምንቃወመውን ያህል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መቃወም አለብን፡፡ በዘ-ህወሀት እና የዘ-ህወሀትን የጎሳ ልዩነት በዘፈቀደ በሚያራምዱ አካሎች መካከል ያለው ልዩነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነው፡፡ የአቁማዳ እና የቀልቀሎ ልዩነት ነው፡፡ ሁለቱም አንድ እና አንድ ናቸው፡፡ ዘ-ህወሀትን ለመተካት ይፈልጋሉ፣ እናም ዘ-ህወሀትን የሚያካሂደውን ወስደው በሌላ የጎሳ ስያሜ አዲስ እና የተሻሻለው ዘ-ህወሀት ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡  እነዚህ በሕዝቦች መካከል የበቀልን፣ የጥላቻን እና የቡድናዊ ግጭትን ዘር የሚዘሩትን ሰዎች ማንነት አበጥረን በመለየት እና እውነተኛ ማንነታቸውን ለይቶ በማጋለጥ ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲገለሉ በማድረግ በጎሳዎች እና በኃይማኖቶች መካከል ትክክለኛ የሆነ ህብረትን ለመፍጠር የምንችልበት ትክክለኛው ወቅት እና መልካም አጋጣሚ አሁን በእጃችን ላይ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከዘ-ህወሀት እና ከዘ-ህወሀት ጎን ቆሞ አዲስ የጎሳ ስያሜን ይዞ ከተነሳው ጎራ በተቃራኒው ለተሰለፈው ለተቃዋሚው ንቅናቄ ትክክለኛ አመራር ሊሰጥ የሚችል መልካም ዕድል አለን፡፡ እዚህ ላይ በተለይ የፖለቲካ መሪዎችን ማለቴ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ እያልኩ ያለሁት በተለያዩ ጊዚያት ትክክለኛውን ጊዜ እና የአመራርነት መልካም አጋጣሚ አጥተው የቆዩትን የሲቪክ ድርጅቶችን ማለትም የእምነት እና የማህበረሰብ መሪዎችን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንን እና የፖለቲካ አክቲቪስቶችን  የወጣቶች እና የሴቶች ቡድኖች መሪዎችን፣ የሙያ ማህበራት መሪዎችን እና የሠራተኛ ማህበራትን፣ ወዘተ… ማለቴ ነው፡፡

አሁን እንኑር! ጊዜውን እንጠቀምበት!

ዘ-ህወሀቶች አብይ አህመድ እንደሚወድቅ ዝግጅት አድርገው እራሳቸውን አሳምነዋል፡፡

ከዘ-ህወሀት ጽ/ቤት የሚመጣው ጩኸት እንደሚነግረን አብይ አህመድ እንዲወድቅ እና ስኬታማ እንዳይሆን አቅደዋል፡፡

ሊወድቅ የሚችል መሆኑን እንዴት እንደሚያረጋግጡም በእርግጠኝነት ተናግረዋል፡፡ እርሱን በጋራ አመራር ሂደት በመካከላቸው ውስጥ በማድረግ እንዴት ሊያምቁት እንደሚችሉ ግልጽ አድርገዋል፡፡ ሞራሉ እንዲነካ፣ ተስፋ እንዲቆርጥ እና በማስፈራራት እጁን እንዲሰጥ ያደርጋሉ።

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ አባላት ማድረግ የሚገቧቸውን መልካም ነገሮች ሁሉ እየተከታተሉ በወቅቱ የሚያደርጉ ከሆነ ዘ-ህወሀት አብይ አህመድን ማመቅ አይችልም፡፡ ለዚህም ስኬት የአቦሸማኔው ትውልድ ሰላማዊ ትግላቸውን በስፋት እና በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡ አብይ አህመድ ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ከተፈለገ ብቸኛው ዋስትና ይኸው መንገድ ብቻ ነው፡፡ የዘ-ህወሀት አውሬ በእራሱ የመጫወቻ ካርታ እንዲረታ ሊያደርግ የሚችለው ብቸኛው መንገድ ይህ ብቻ ነው፡፡

ለዘ-ህወሀት እንዲህ የሚል ዜና አገኘሁለት፣ “ውድቀት ምርጫ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ሁላችንም አንድ ነን፡፡ ሆኖም ግን እኛ እናሸንፋለን ምክንያቱም የተባበሩትን ኢትዮጵያውያን በፍጹም ልታሸንፉ አትችሉም!

የስኬት ዋናው መሰረቱ ህብረት ነው፡፡ እባካችሁ የታሪክን ስህተት አንድገመው፡፡ ልናጣው የማይገባንን መልካም አጋጣሚ ማጣት ለእኔ መሪር ሀዘን ነው፡፡ እባካችሁ ይህ መልካም አጋጣሚ እንዳያመልጠን፡፡

ታሪክ የሚሰራው ጊዜውን በያዙት የህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡

ጊዜውን አሁኑኑ እንጠቀምበት እና ኢትዮጵያዊነትን አንግበን አንድነትን በማጠናከር የዘ-ህወሀትን አውሬ በእራሱ የመጫወቻ ካርታ በመርታት ታሪክ እንስራ፡፡

አሁን እያደረግነው ያለው ትግል ለወደፊቱ የኢትዮጵያ አቦሸማኔ ትልውድ ደህንነት ነው፡፡ በእርግጠኝነት የወደፊቷ ኢትዮጵያ ተስፋ እነርሱ ናቸውና፡፡

የእራሴ ግላዊ ስተያየት…

ለአብይ አህመድ የእኔ የግል መልዕክት እንዲህ የሚል ነው፣ “ቀጥ ብለህ ቁም፣ ከጎንህ ነኝ ወንድሜ!“

ዘ-ህወሀት ጨዋታው ተጠናቋል!

ኃይል ለኢትዮጵያ የአቦሸማኔው ትውልድ! ረዥም እድሜ ለአቦሸማኔው ትውልድ! 

ኢትዮጵያዊነት ዛሬ! 

ኢትዮጵያዊነት ነገ! 

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም!

(ይቀጥላል…)

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!   

ሚያዝያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም

Filed in: Amharic