>

ጦሩ ምን አለ? (ደረጀ ደስታ)

ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል ይባላል። ስብሐት ነጋ ግን ብቅሉም ባይኖር እሚያምኑትን ከመናገር ወደ ኋላ አይሉም። ሲጎነጩ ደግሞ የበለጠ ይዘረግፉታል። አሁንም ዛሬ የጠቅላይ ምኒስትር አብይን ሹመትና ንግግር ክፉኛ ሲኮንኑት ተሰምተዋል።
“እኔ መጀመሪያውኑ ሽፈራው ሽጉጤ ላይ ሥሩ ብያችሁ ነበር። ደመቀ ደመቀ ብላችሁ ነገር አበላሻችሁ። አሁን ደግሞ ይሄ ጨርሶ ከኢህአዴግ አስተሳሰብ ውጭ የኒዮ ሊብራል ንግግሩን አገር ላይ በትኗል። ንግግሩ ለምን እንዳልታየና እንዳልተመከረበት አይገባኝም…አሁንም የካቢኔዎች ሹመት በሚገባ መታየትና መጠናት አለበት …

ስብሐት እንደድሮው አቅም ባይኖራቸውም አቅም ባላቸው ሰዎች መከበባቸው እሚታወቅ ነው። ጀኔራል ሳሞራ ብዙም ባያስጠጓቸውም ደህንነቱ ጌታቸውና ሳሞራን ለመተካት የታጩት ጀኔራል ሰዓረ አይለይዋቸውም።
ለመሆኑ አሁን ሠራዊቱና የደህንነቱ አባላት ስለ አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ምን እያሰቡ ነው? የሁለቱ ተቋማት ቁንጮ ሳሞራና ጌታቸው ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ የቆዩ ናቸው። እነሱ ያሰቡትን ለማወቅ እንደ ስብሐት ሆድ ያባውን ብቅ ያወጠዋል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ሁለቱም መጠጥ እሚባል ነገር አይነኩም። ስለዚህ አይሰክሩም። ሴራና ጎሰኝነት ካላሰከራቸው መጠጥ አይደርስባቸውም። በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች በሙሉ የሚጠጡ በመሆናቸው አዳሜ በሞቅታ ሲቀባጥር ማን ምን እንደሚያስብ ያውቃሉ። እነሱ እሚያስቡትን ግን ማንም አይደርስበትም። ደህንነቱ ጌታቸው እንኳ አንዳንዴ ቱግ ብድግ ይላሉ፣ በዚያ ላይ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ፖለቲካው ውስጥ ስለገቡ ቢያንስ እሚያስቡትንና እሚፈለጉትን መገመት ይቻላል። ሳሞራ ግን ስብሰባ ላይ ያጉዋሩ ካልሆነ ብዙ አያወሩም። እንዲሁ ሲታዩም እንደመቅለስለስ ያደርጋቸዋል። ሁሉ ነገር ከመለስ ጋር የሞተ እየመሰላቸው ሐዘኑ ገና ከሆዳቸው አልወጣም።
ለዚህም ይመስላል መለስን ለመቅበር ነቅሎ ከወጣው ከዚያ ሁሉ ጄኔራል አንድስ እንኳ ብቅ ብሎ ስለ አዲሱ ጠ/ሚ/ር አስተያየት የሰጠ አልታየም። ምክንያቱም ሠራዊቱ ተጠሪነቱ ለህገመንግስቱ በመሆኑ ከፖለቲካ ነጻ ነው እሚሉት ፈሊጥ አለ። ነጻ መሆኑ ጥሩ ነው። ግን ህገመንግስታዊ መብቶችን ለመጣስ አዋጅ እያስደለቀ በኮማንድ ፖስት ስም እሚገድል እሚያስርና የፖለቲካውን ሥልጣን እድሜ ለማራዘም እሚተጋ ሰራዊት አሁን አፉ ተለጉሟል። በፀረ ኢትዮጵያዊነት የተከሰሱት ሳይቀሩ ድጋፋቸውን ሲሰጡ፣ በኢትዮጵያዊነት ቀልድ አላውቅም እሚለው ጦር ኢትዮጵያዊነት ሲሰበክ የቀፈፈው መስሏል።
ደህንነቱ ጌታቸውና የጦሩ ሳሞራ ግን አንድ አዳራሽ ውስጥ እንኳ አብረው መገኘት እሚቀፋቸው እጅግ እሚጠላሉ ሰዎች ሆነዋል እሚባልም ነገር አለ። የሁለቱ መለያየት የለውጥ ቀዳዳ ፈጥሯል እሚልም ግምት አለ። ስብሐትን እሚያስለፈልፋቸው ይህ ቀዳዳ ታይቷቸው ይመስላል። የሳሞራን ሥልጣን ለመክፈል ወይም ከሳሞራ በኋላ ሊመጣ እሚችለውን ኃይል ምናልባትም የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ለመገደብ አዲስ አወቃቀር ቀደም ሲል መዘጋጀቱም ይታወቃል። በዚህም መሰረት ጀነራል ሰዓረን አጅበው ጀነራል ብርሃኑ ጁላ እና ጀነራል አደም መሐመድ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሆነው መሾማቸውን እሚዘነጋ አይደለም። ያው ይሉኝታ ስላልፈጠረባቸው ሳሞራን በሰዓረ ለመተካት ማሰባቸውም ይገመታል። የደህንነቱ ሹሙና የህወሃት ሥራ አስፈሳሚው ጌታቸው ጀኔራል ሰዓረ ጋር በየቀኑ ሊያስብል በሚችል ሁኔታ የጋራ ሳውና ለመውሰድ ከሸራተኑ ሆቴል እሚመላለሱ ወዳጆች ናቸው። ሳሞራን የማሽቀንጠሩ ድል ከቀናቸው አዲሱን ኤታማዦር ሹም እናይ ይሆናል። እሚነሱ እንኳ ቢሆን አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አነሷቸው ስንል እነማን ጎተቷቸው ማለቱም ተገቢ ነው። ሠራዊቱን ህዝባዊ ሠራዊት ለማድረግ ግን መንገዱ ገና ረጅምና ውስብስብ ነው። ከታች ያሉትን የበታች መኮንኖችና ወታደሮችን ማንቃትና የትግሉ አካል ማድረግ ይገባል። ይህ ኃላፊነት የለውጥ አካል ከሆኑት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ይጠበቃል። ያ ካልሆነ ግን ደህንነቱም ጸረ ደህንነት፣ ሠራዊቱም የአገር ሳይሆን የለውጥ መከላከያ ሠራዊት መሆኑ እማይቀር ነው። ነገሩ ሁሉ የነብር ጭራ አይዙም ከያዙም አይለቁም እንደሚባለው፣ አብይም የያዙትን ጭራ አለመልቀቅ ነው። አንበሳው ህዝብ ግን የነብር ጭራ አይዝም ምክንያቱም ራሱ አንበሳ ነው። አሁን እንደ ጀመረው ሁሉንም በጊዜው ይደባልቀዋል- መልካም ፋሲካ!

Filed in: Amharic