>

በህወሃት ሰማይ ላይ እየጠለቀች ያለችው የምሽት ጀንበር! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የህወሃት መሪዎች ስለኢትዮጵያ አንድነት ሳይሆን፤ እነሱ ከሌሉበት ተበጣጥሳ ስለምትጠፋዋ ኢትዮጵያ ነው ማውራት የሚያኮራቸው። በራሳቸው አምባገነናዊ ምህዋር ውስጥ ሆነው፤ ከነሱ ውጪ የሆነን ሰው ሁሉ በጠላትነት ይፈርጃሉ፤ እንደጠላትም ቆጥረው ህዝብን ያለርህራሄ ይፈጃሉ። ይህን መሰረታዊ የሆነ የህወሃት ባህሪ፤ በአጭሩም ሆነ በረዥሙ ስናብራራ ብንውል፤ በአማርኛም ሆነ በሌላ ቋንቋ ብንጽፈው… ስሜቱም ሆነ ውጤቱ ተመሳሳይ ነው። ጥያቄው “ይህ ጥላቻን መሰረት ያደረገ የህወሃት ባህሪ፤ ሄዶ ሄዶ መጨረሻው ምንድነው?” የሚለው ይሆናል።

ለጨዋታችን መነሻ እንዲሆነን የደብረጽዮንን ጉዳይ እናንሳ! የህወሃት መሪ… ደብረጽዮን በምርጫው እንደማይካፈል ከገለጸ በኋላ፤ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ተጭበርብሮ ሲታወጅ፤ በንጋታው ‘ምናልባት እኔም አጭበርብሬ ላሸንፍ እችላለሁ’ ብሎ ይመስላል… በምርጫው እንደሚካፈል ይፋ ማድረጉን እናስታውሳለን። ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን… መሸነፉን ሲያውቅ፤ ድፍረት የተሞላበት ውሸት ዋሸን። እንግዲህ ህወሃትን የሚመራው፤ የዶክተርነት ማእረግ የሰጡት ዋና ሰው እንዲህ የሚዋሽ ከሆነ፤ እታች ያሉት ትናንሽ ህወሃቶች፤ ምን አይነት ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምቱን ለ’ናንተ እንተዋለን። ዛሬ በኢትዮጵያዊነት ላይ ሳይሆን፤ መሰረቱን ጥላቻ ላይ ያደረገው ህወሃት እየሄደበት ያለው ጎዳና እንዴት እየጨለመ መምጣቱን እናወጋለን።

ባለፈው የኢህአዴግ የርስ በርስ ምርጫ ላይ፤ ዶ/ር አብይ መቶ ከምናምን ነጥብ አግኝቶ ሊቀመንበር ሆኖ ሲመረጥ፤ የህወሃቱ ደብረጽዮን ግን 2 ድምጽ ብቻ አስቆጥሮ፤ እንኳንስ ህወሃቶችን እኛንም ጭምር አስደንግጦናል። አንዳንዶች “ሁለት ድምጽ የተባለው፤ እራሱ ሁለት እጁን አውጥቶ፤ እንደሁለት ተቆጥሮለት ነው” ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ “ድምጽ የቆጠረው አባ-ዱላ ከሆነ እንደልማዱ ተሳስቶ ነው!” በማለት ሲያሾምሩ ሰምተናል። ከሁሉም የበለጠው አስቂኝ ተውኔት የመጣው ግን ጋዜጠኛው ዶ/ር ደብረጽዮንን ሲያናግረው ነው።

የምርጫው ውጤት ከታወቀ በኋላ፤ ጋዜጠኛው ዶ/ር አብይ አህመድን ከማናገር ይልቅ፤ ተሽቀዳድሞ ሄዶ… እኚሁ በከፍተኛ የሽንፈት መዝገብ ላይ የሰፈሩትን ሰው፤ የህወሃቱን መሪ ደብረ ጽዮንን አናገራቸው።

“እንዴት ነበር?” አላቸው።

እሳቸውም ከንፈራቸው እየተንቀጠቀጠ… “ያው እኔ እንዳልመረጥ ቅስቀሳ አድርጌ ስለነበር ነው…” ሲሉ የሳቁ ሰዎች ባይጠፉም፤ እኛን ግን በሚገርም ውሸታቸው ከማሳቀቅ አልፈው አሸማቀቁን። እናም “ዝይሃፍር ድሙ፣ ገብረማርያም ሽሙ!” ብለን እንለፈው።

እናም ያን ሰሞን ትልቁም ትንሹም በደብረጽዮን ሁለት ድምጽ ማግኘት፤ ተረብ እና ሽሙጥ እየቀላቀለ ብዙ ነገር ሲል ቆየ። አንደኛው ጨዋታ እንዲህ የሚል ነበር። ልጁ አያቱን ይጠይቃቸዋል።

“አያቴ?”

“አቤት?”

“በ1 ልደታ ነው፤ በ3 ደሞ ባዕታ ነው። በ2 ምንድነው?” ብሎ ይጠይቃል – ህጻኑ ልጅ።

አያት አሰብ አደረጉና “በ2ማ ደብረጽዮን መሰለኝ።” ብለው፤ አንድ ፍሬውን ልጅ ሳይቀር በሳቅ አፈረሱት።

ብዙ የትግራይ ሰዎች እንደሚሉት፤ “ህወሃት የተገነባው በብዙ ሺ ታጋዮች ሞት ነው”… ይህን አባባል እንቀበለውና የወጋችን መንደርደሪያ እናድርገው። አዎ ህወሃት ብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያንን ገድሎ፤ የራሱንም ሰዎች ለሞት ገብሮ ነው መቆም የቻለው፤ የተቋቋመው ግን በንጹሃን ዜጎች ደም እና ላብ ነው።

የሚገርመው ግን ይህ የሞት ታሪክ ህወሃትን እጅግ ከሚያኮሩት ታሪኮቹ አንደኛው መሆኑ ነው። ለዚህ ብዙ መረጃ ሳያስፈልገን፤ ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር ሰርተው የሚያቀርቡልንን ዶክመንተሪ መመልከት በቂ ይሆናል። የራሳቸውን ሰው ሰውተው፤ ሌላውንም ኢትዮጵያዊ ገድለው ሲያበቁ… አዲስ አበባ የገቡበትን ቀን “ጠላትን የገደልንበት ቀን” እያሉ፤ ግንቦት ሃያን በፈንጠዝያ ያከብሩታል። ራሷን ነጻ ያደረገችው ኤርትራ እንኳን፤ “የደርግ ወታደር…” የሚል ቃል ስትጠቀም፤ የትግራይ ህወሃቶች ግን አሁንም ድረስ… የቀድሞ የኢትዮጵያን ሰራዊት፤ “የጠላት ጦር” በሚል የጥላቻ ስም መጥራትን ይመርጣሉ። ይህ የጥላቻ ስሜት እንደ ጉንፋን የሚጋባ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነውን ህዝብ በተመሳሳይ፤ የጠላትነት ስሜት ያዩታል።

ሁሌም ግን የሚገርመን ነገር አለ። የትግራይ እና የኤርትራ ሰዎች በባድመ ምክንያት ያን ያህል ተጣልተውና ደም ተቃብተው፤ አንድም ቀን የሻዕቢያን ወታደር ሆነ ህዝብ፤ “ጠላት” ብለው ጠርተውት አያውቁም። “በትሪ ሃቡኒ፤ ዘህምቖ ኣሎኒ!” ነው ነገሩ። በአማርኛ ትርጉሙ፤ “የምችለው አለ፣ ዱላዬን ስጠኝ!” እንደሚባለው ነው – የሆነው – የህወሃት ነገር።

ወደራሳችን ታሪክ ስንመለስ ደግሞ፤ የራሳችን ነገር መላልሶ ይገርመናል። እኛ ኢትዮጵያውያን… ከጣልያን፣ ከሱዳን፣ ከሱማልያ እና ከኤርትራ ጋር ብዙ ደም ያፋሰሰ ጦርነት አድርገናል። ከዚህ ሁሉ ጦርነት በኋላ እንኳንስ ጣልያንን፤ የኤርትራን መንግስት “ጠላት” ብለን አንጠራውም። ትግራዋይን ግን ተመልከት። ከዚህ በፊት ያሉትንም በድጋሚ ተመልከት። ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር፤ በአማርኛም በትግርኛም በሚተላለፉ ዝግጅቶቻቸው ላይ… ሌላውን ህዝብ ወይም ጦር፤ ጥልቅ በሆነ የጥላቻ ስሜት “ጠላት” በሚል ስያሜ ይጠሩታል። ይህ ጥላቻ የፈጠረው እብሪትና ግፍ ነው እንግዲህ፤ እነሱን ገዳይ… እኛን ተገዳይ አድርጎ፤ ቀስ በቀስ ግን ዘርፈውም ቢሆን የፈነጠቀላቸውን ጸሃይ፤ ፈጣሪ እንደ”ዘመቻ ፀሃይ ግባት!” ጀንበሯን በላያቸው ላይ እያጨለመው መጣ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ በርካታ የርስ በርስ ጦርነቶች ተካሂደዋል። በአክሱማዊት ዘመን – ፈላሻዎች የአክሱም መንግስትን አሸንፈው ስልጣኑን ገልብጠዋል፤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን – ግራኝ አህመድ ከአጼ ልብነ ድንግል እና አጼ ገላውዲዮስ ጋር የከረረ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ብዙ ህዝብ ተፋጅቷል። ከሁለት መቶ አመት በፊት የኦሮሞ ተወላጅ የሆነው – ኢዮአስ ጎንደር ላይ ሲነግስ፤ የትግራይ እንደራሴ ራስ ስሁል ሚካኤል ተጣልተውት፤ በመጨረሻ ሞት እንዲፈረድበት አደረጉ። ከዚያ በኋላ በነበሩት ታሪኮች በሙሉ ኢትዮጵያ ከርስ በርስ ጦርነት አላረፈችም።

ይሄ ሁሉ የጦርነት ታሪክ አልፎ፤ ይሄ ሁሉ ትውልድ ሞቶ… በትረ ስልጣኑን የያዘው መንግስት ስልጣኑን ለበቀል ሲጠቀምበት እምብዛም አናይም። ይልቁንም ልጆቻቸውን ለባላንጣቸው ድረው፤ በይቅርታ መንፈስ ተዋደው አገር ሲመሩ እንጂ፤ አሸናፊ እና ተሸናፊ በሚል ዜማ – አንድን ህዝብ “ጠላት” ብለው ሲጠሩት አላየንም፤ አልሰማንም።

በሚገርም ሁኔታ… ይሄ ሁሉ ሆኖ አንደኛው ኢትዮጵያዊ ሌላውን ህዝብ፤ “ጠላት” ብሎ ሊጠራው ቀርቶ፤ ክፉ የሚባለውን የፋሽስት ጣልያን ጦር እንኳን… “ጠላት” ብሎ መጥራት ካቆመ አመታት ተቆጥረዋል። … ህወሃት ግን ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንደጠላት የመቁጠር ባህል፤ ከድሮም እያዳበረው መጥቶ ከፍተኛ እርከን ላይ አድርሶታል። ይህ አዲስ የተጀመረ ነገር አይደለም።

ለምሳሌ የህወሃትን መመሪያ ወይም ማኒፌስቶ ብንመለከት፤ “የትግራይ ህዝብ ዋነኛ ጠላት የአማራ ህዝብ ነው” ይላል። “2ኛ ጠላታችን ደግሞ ተፈጥሮ ነው።” በሚል ትንታኔ ጭምር ታክሎበት ተቀምጧል። ይህ አሁንም ድረስ ያልተሰረዘ የትግራይ ህወሃት መመሪያ ወይም ማኒፌስቶ ሆኖ የሚያገለግል ሰነድ ነው። መታሰር ወይም መገደል ካልፈለገ በስተቀር፤ ማንም ይሄን አንቀጽ ለመቀየር ወይም ለመሰረዝ የሞከረ ትግራዋይ የለም። ህወሃት ከምስረታው ጀምሮ የተቃወሙትን የራሱን ሰዎች “ጠላት” የሚል ስም ሰጥቶ ረሽኗቸዋል። ይህን ለመቃወም አቅም ያገኙ ትግራዋዮች ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው።

እንግዲህ በእንዲህ አይነት የጥላቻ መንፈስ ውስጥ ያለውን፤ ህወሃት የሚባለውን ድርጅት ነው የትግራይ ህዝብ ተሸክሞት ያለው። ይህ የጥላቻ እና የበቀል ፖለቲካ በህወሃት ውስጥ እንደባህል ሆኖ ከመቆየቱ ብዛት፤ ዛሬ ህወሃት እና እርቅ ወይም ይቅር መባባል አይተዋወቁም። “ጠላት” ብለው ከፈረጁት ግለሰብ ጋር ወይም ህዝብ ጋር መነጋገር ለነሱ እንደውርደት የሚቆጠር ነው። እዚህ ላይ ሌላ ምሳሌ እናቅርብ። ባለፈው አመት… የህወሃት ሊቀመንበር የነበረው አባይ ወልዱ ወደ አማራ ክልል ሄዶ፤ ከብአዴን ሰዎች ጋር ተሰብስቦ ሲመለስ፤ የራሱ ሰዎች “መርሃ አልባ ግንኙነት ፈጥረህ፤ ለአማሮች ተንበርክከሃል።” ብለው ገመገሙት። በውጤቱም ከህወሃት ሊቀመንበርነት ተነስቶ በምትኩ ደብረጽዮን እንዲሆን የተደረገበትን፤ የትግራዋይ ተውኔት ካየን ሰነባበትን።

እንግዲህ አስቡት። ህወሃት በእንዲህ አይነት ጠባብ ብሄረተኛ መንገድ ላይ ተረማምዶ፤ ሊቀመንበሩን ከስልጣን ካባረረ፤ ሌሎች ከአማራው ጋር ቢነጋገሩና ቢደራደሩ፤ ቢጋቡና ቢዋለዱ ምን ሊፈጸምባቸው እንደሚችል ግምቱን ለሌላው ኢትዮጵያዊ እንተዋለን።

በጣም የሚያሳዝነው ግን… የትግራይ ህዝብ በሌላው ህዝብ ላይ እምነት እንዳይኖረው፤ ሌላውን ህዝብ እንዲጠላ እና እንዲጠራጠር ያላሰለሰ ስራ መሰራቱ ነው። ይህ አይነቱ ስራ በተመሳሳይ መልኩ በብአዴን እና በኦህዴድ ውስጥ ለአመታት ሲሞከር ቢቆይም፤ በህዝቡ አሻፈረኝ ባይነት እነኦቦ ለማ መገርሳ እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ በቁ። በውጤቱም ዶ/ር አብይ አህመድን ለውጤት አበቁ።

ህወሃት እና ተከታዮቹ ግን “የሃይል ምንጭ እና የስልጣን ማስጠበቂያ ጠመንጃ ነው!” የሚል አስተሳሰብ እንደያዙ፤ አሁንም ሌላውን ኢትዮጵያዊ ለመግደል እና ለመጨፍጨፍ እንዲመቻቸው የመከላከያ፣ የፖሊስ እና ደህንነት ሃይል በነሱ ስር እንዲሽከረከር ይሻሉ። በሰጣቸው ስልጣን እና ጠመንጃ  ሌላውን ህዝብ መግደልና መጨፍጨፋቸውን እንደጀግንነት በመቁጠር ዛሬም ድረስ ይፎክራሉ። ይህ የህወሃት ጥላቻ በጽሁፍ ወይም በመመሪያ ብቻ ሳይሆን፤ ግጥም እና ዜማ ተደርሶለት፤ ሌላውን ብሄር የሚያጥላላ ዘፈን ሲያንጎራጉሩ ሰምተናል።

የአማራው ህዝብ በትግርኛ ዘፈኖች ሲሰደብ፤ ብአዴን ዝም ከማለት ሌላ ምንም አይነት ተቃውሞ አሰምቶ አያውቅም። የዚህ መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ በበረከት ስምኦን ተጽፎ፤ ለድርጅቱ የተበረከተው የፖለቲካ ፕሮግራም ነው። በረከት ስምኦን በ’ናቱም ባባቱም ኤርትራዊ መሆኑን ክዶ አያውቅም። እንደዚያም ሆኖ ብአዴን እንዲመራበት በጻፈው የፖለቲካ ፕሮግራም ውስጥ፤ የአማራን ህዝብ የሚሳደብ እና የሚያዋርድ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሉ የአማራ ገዢዎች የሌላው ህዝብ ጠላት እንደሆኑ አድርጎ ጽፏል። ይህ አሁንም በፕሮግራሙ ውስጥ አለ፤ አልተሰረዘም። እንግዲህ ልብ በሉ። ህወሃት ከራሱ አልፎ ሌላውን፤ በእንዲህ አይነት የህሊና ዝቅጠት ውስጥ የሚጨምር ድርጅት ነው።

አልፎ ተርፎ ከሌሎች ጋር ያለውን አንድነት ማጠናከር የሚፈልገው ጥላቻን መሰረት ባደረገ ፍልስፍና ላይ ተመስርቶ በመሆኑ፤ የህወሃትን ፖለቲካ የሚያሽከረክሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች፤ ከዝቅተኝነት ወይም ከእበላ ባይነት ባህሪ በመነጨ መልኩ ጭምር ከህወሃት ጋር እጅና ጓንት ሆነው ሰርተዋል፤ አሁንም እየሰሩ ያሉ ይገኛሉ።

ህወሃትን የሚደግፉ ሰዎች… መሰሪ ተግባሩን፤ እንደአዋቂነት ይቆጥሩታል። በነሱ ላይ እስካልደረሰ ድረስ፤ የነሱን ጥቅም እስካስጠበቀላቸው ግዜ ድረስ፤ ግድያ እና ዘረፋውን ጭምር የሚደግፉ የነሱ ሰዎች ብዙ አሉ። ይህ ግን ብዙ ርቀት አያስኬድም። ዛሬ ከህወሃት ሆነ መታደስ ካቃታቸው የድሮ ኢህአዴጎች ህዝቡም ሆነ ደጋፊዎቻቸው ተንኮል እና ሙስናን ካልሆነ በስተቀር የረባ ቁምነገር አያገኙባቸውም። በህወሃት አለም ውስጥ የአንድ አባል ብቃት የሚለካው በገደለውና በዘረፈው ሃብት መጠን ሲሆን፤ እንደምሳሌ የሚጠቀሱትም እንደአዜብ መስፍን እና ደብረጽዮን አይነት ሰዎች ናቸው።

አዜብ መስፍን አገር በሚያውቀው ሁኔታ በትግራይ ህዝብ ስም የተቋቋመውን ኤፈርት ሙልጭ አድርጋ ስትግጥ የኖረች ሴት ናት። ደብረጽዮን የኢትዮጵያ መብራት ኃይል የቦርድ ሊቀመንበር ሆኖ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በውጭ አገር ማስቀመጥ የቻለ ሰው ነው። አባይ ጸሃዬ የስኳር ኮርፖሬሽን ዳይሬክተር ተብሎ አይናችን ስር ሙስናን እንደ ስኳር የሚቅም ትልቅ ባለሃብት ነው። ስዩም መስፍን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተብሎ በግልጽ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያን ሃብት በቻይና ገበያ በማሻሻጥ ስራ ላይ አሁንም ድረስ አለበት። እንዲህ እንዲህ እያልን ብዙ ዝርዝር ማውጣት ይቻላል። በቴሌኮምዩኒኬሽን፣ በባንክ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ያለውን የዝርፊያ ጨዋታ እዚህ ላይ ማንሳቱ፤ “የአዋጁን በጆሮ” መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ትርፉ ንዴት እና ብስጭት ስለሚሆን “ተከድኖ ይብሰል” ብለን ማለፉን እንመርጣለን።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ የሚገኝ ወጣት ከህወት መሪዎች የሚማረው ነገር ቢኖር… እንደ ሳሞራ የኑስ እብሪትን፤ እንደአባይ ጸሃዬ ሌብነትን፤ እንደአዜብ መስፍን ባዶነትን፤ እንደደብረጽዮን ውሸትን፤ እንደነ እገሌ እና እገሌ ክህደትን… ይህንን ነው የትግራይ ወጣት እየተማረ ያለው። እነዚህ ሰዎች እንኳንስ ለታላቂቱ ኢትዮጵያ ቀርቶ ለራሳቸውም ህዝብ ሞዴል ለመሆን የሚችሉ አይደሉም። ሆኖም በህወሃት ላይ እንጂ በትግራይ ህዝብ ተስፋ አንቆርጥም። እነዚህ የምሽት ጀንበር በትግራይ ህዝብ ላይ እንድትጠልቅ የሚያደርጉ፤ በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱ፤ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው ግን በሚሊዮን እና በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብት ያካበቱ ሰዎች፤ ሲሆን በሰላም ካልሆነም በግድ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ማድረግ ያስፈልጋል።

የህወሃትን ግፍ በምንም አይነት ዘርዝረን የምንጨርሰው አይደለም። እንኳንስ ወላዷ እናት ቀርታ… ወንድ ልጅ እያለቀሰ፤ “ለምን ከኢትዮጵያ ተፈጠርኩ?!” ብሎ ያዘነበት ዘመን ላይ ደርሰን ነበር። ይህ ወቅት ለህወሃት ጥልቅ እና ትልቅ ትምህርት የሚማርበት፤ ራሱን የሚፈትሽበት፤ ከጥላቻ እና ከዘረኝነት ጸድቶ በኢትዮጵያዊነት የሚጠመቅበት፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚታረቅበት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ይህን አጋጣሚ አለመጠቀም ማለት፤ በህወሃት ላይ እየጠለቀች ያለችውን ጀንበር… ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተሰናብቶ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መኳተን ማለት ነው። መልካም ዘመቻ ጸሃይ ግባት… ለህወሃት እና ለህወሃት!

Filed in: Amharic