>

የዐመት በዐል ወጎች (በውቄ ፤ ከየረር በር)

ከሁሉ አስቀድሜ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድየ እንኩዋን አደረሰዎት ለማለት እፈልጋለሁ፤ (በስምአብ!ካድርባይነቴ የተነሳ ያባታቸውን ስም ሳይቀር አቆላመጥኩትኮ)
አቢሻ ፤በቀጣይ በሚያዋቅሩት ካቢኔ ውስጥ እኒህን ቁልፍ ሰዎች ቢያካትቱልኝ ደስታውን አልችለውም፤ባልችለውም ከጉዋደኞቼ ጋር ተጋግዥም ቢሆን እሸከመዋለሁ፤

የቀድሞው ዋናተኛ ሮቤል ኪሮስ (የውሃና መስኖ ሚኒስትር)
የቀድሞ ወጣት ፤አበበ ቶላ ፈይሳ (በንግሊዝ የኢቶጵያ አምባሳአደር )
አሳ-የ ደርቤ (አሳ ሃብት ሚኒስትር፤ )
ሻምበል ለማ ጉያ (የቆዳና፤ ሌጦ ምኒስትር )

ሌሎችን በዳግማይ ትንሳዔ ይጄ እመለሳለሁ፤

አሁን ፖለቲካውን ዳር አስይዘን እናቁመውና የሚያስተክዙ ያመት በዐል ወጎችን እንገርብ፤
ወንጌል ያነበባችሁ ሰዎች እንደምታስታውሱት፤ ኢየሱስ በተሰቀለበት ወቅት በግራና በቀኙ ሁለት ሌቦች አብረው ተሰቅለው ነበር፤ አንደኛው እንዲያውም አርፎ መሞቱን ትቶ ‘እስቲ የግዜር ልጅ ከሆንክ ራስህን አድን”ምናምን እያለ ሲሳፈጥ የነበረ ነው፤እና የሱስ በአለም ላይ ብዙ ደቀመዛሙርትን ያፈራውን ያክል ፤እኒህ ሁለት ሌቦች ያቅማቸውን ያክል ተከታይ አፍርተዋል፤ይህንን የሚጠራጠር ባመት በዐል ዋዜማ ወደ መርካቶ ብቅ ይበል፤

ሰሜ ከተሜው ይባላል፤(ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስሙ የተለወጠ) ባመት ባል ዋዜማ ሙክት በግ ሽጦ ያገኝውን ሶስት ሺ ብር እንደ ቡዳ መዳኒት በሚያንጠለጥለው፤የቆዳ ቦርሳ ውስጥ ከተተው፤በላዩ ላይ ወፍራም ሹራብ ደረበበት፤በሹራቡ ላይ መለስተኛ ድንኩዋን የሚያክል ካቦርት ገደገደበት፤በካቦርቱ ላይ ፤ከጥጥ የተሰራ ግድግዳ የመሰለ ጋቢ ጣል አደረገበት፤

ግን ይህ ሁሉ የጨርቅ አጥር በመርካቶ ኪስ አውላቂ ፊት ምን ዋጋ አለው? ጋሽ ሰሜ ቤቱ ገብቶ እጁን ወደ ቦርሳው ቢሰድ ብሩ በቦታው የለም፤ሰሜ በድንጋጤ ሲነስረው ያፈሰሰውን ደም ለቀይ መስቀል ቢለግሰው ብሄራዊ ጀግና ይሆን ነበር፤ብቻ ከሁለት ቀን ኮማ ነቅቶ፤ ከምታስታምመው ሚስቱ እጅ ላይ ፤ወገቡ ድረስ የተላጠ ሙዝ እየተቀበለ” እኔ እምልሽ ማሬ!ያንን ሁሉ ልብስ ደራርቤበት በምን ዘልቆ መነተፈኝ?”አላት

“አይ አንተ!” አለች ሚስቱ “ በግ ላቱዋ ቢወፍር መች ከስርያ ያስጥላታል!”

አንድ አዛውንት ከወንቃ ጊዮርጊስ ተነስተው መርካቶ ገብተው ማራቸውን ሸጡ፤ እና ፍራንካውን ማሩን ባጋቡበት ከረጢት ውስጥ ይከቱና ፊታቸውን ወደ ጎጃም በረንዳ ይመልሳሉ፤ይህንን የሾፈ ርጉም የላዳ ሾፌር “ አባት ልሸኝዎት?”

“ተባረክ ዘር ይውጣልህ”

ምርቃቱን እያዘነቡት ገቡ፤

ሾፌር ጥቂት ነዳና “ፋዘር መኪናው ተበላሸ፤ ከሁዋላ ይግፉልኝ እስቲ”
ሰውየው ከረጢታቸውን ትተው ወርደው፤ ከሁዋላ ሲገፉ ሹፌሩ መኪናውን ቆስቆሶ ተፈተለከ፤

ያልታደሉት ሽማግሌ፤አንዱ መአዘን ላይ ቆመው፤ በወባና በእስክስታ መሃል የሚመደብ እንቅጥቅጥ ሲንቀጠቀጡ አንድ የሚያውቃቸው አልፎሂያጅ ያያቸዋል፤

“አባት ምን ሆነው ነው?”

“ብሬን ገፍቸ ሰድጄው”

Filed in: Amharic