ይህን የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ሳስተላልፍ ብዙ ጥልቅ ስሜቶች ይሰሙኛል። ውድ ወገኖቼ እንደምታስታውሱት እኔና በተመሳሳይ ወቅት ለረዥም እስር ተዳርገን የነበርን ጓደኞቼ ሰባት አዲስ ዓመታትን፣ ሰባት በዓለ ልደትን፣ ሰባት በዓለ ጥምቀታትን፣ እናም ሌሎች ሰባት ትርጉመ ብዙ ዓመተ ነበሮችን… ሲዘክሯቸው በሚቀሉ ሲኖሯቸው በሚከብዱ የተገለሉ የጨለማ እስር ቤቶች ባጅተናል። ሰባተኛውን በዓለ ትንሳኤ ግን እነሆ ፈቃዱ ሆኖ እንኳን አደረሳችሁ ለመባባል በቃን። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!
እንዲህም ሆኖ በዓሉን በሙሉ ደስታ እንዳናሳልፍ የሚያደርጉን ብዙ ጉዳዮች መኖራቸው ይታወቃል። አንዱ ተመሳሳዩን ፅዋ አብረውን የቀመሱ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የእስርን የመከራ ገፈት እየተፋተቱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መኖራቸው ነው። በቅርቡ አብረውን የነፃነትን አየር እንዲተነፍሱ እመኛለሁ፤ እፀልያለሁ። እግዚአብሔር አዋቂ ነው!
ሁለተኛው በሩቅ የሚታይ የተስፋ ጭላንጭል ቢኖርም አገራዊ ችግሮቻችን የገዘፉና የተወሳሰቡ መሆናቸው ናቸው። አንዳንዶቹን ገዢዎቻችን ሆን ብለው ያውተበተቧቸውና በመጨረሻ ውሉ እነሱኑ ሳይቀር ጠፍቶባቸው ተጨንቀው እንድንጨነቅ ያደረጉበት፤ በዓለም ፊት ታሪካዊቷን አገራችንን ትዝብት ላይ በመጣል ኩራታችንን የተነጠቅንበት ቢያንስ ሳንፈልግ ወደፊት እየሄድን ወደሇላ ለማየት የተገደድንበት የቅርብ ጊዜው ገመና ነው።
ኢትዮጵያችን በአንድ የታሪክ ወቅት ክፉውን ቀን ለማሳለፍ እንዳልተጠለሉባት ሁሉ ዛሬ ሁኔታው በአንፃራዊ ፅንፍ ክፉውን ቀን ለማምለጥ እያፈቀሯት ጥለዋት የሚነጉዱባት አገር ሆናለች። በሩቅ አሻግረው እያዯት በቁጭት “ዋ አገሬ!” የሚሉ ውዶቻችን ቁጥር በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሆኗል። እግዚአብሔር በቃ ይበለን።
ወድ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼ እህቶቼ፤ እነዚህና ተያያዥ ነገሮች በሙሉ በጥልቀትና በፅሞና ተፈትሸው መፍትሄ ሊደረግባቸው የሚገቡ ብንፈልግም ለነገ ልንላቸው የማንችላቸው አንገብጋቢ ጉዳዮቻችን ናቸው። እነዚህን የጉድ ገመናዎቻችንን ሳንገላገል በዓል መጣ ብለን ብንፈነጥዝ ። “ተሸንፎ ፉከራ፣
ሬሳ አስቀምጦ ጭፈራ” የሚሉት የዘአልተገናኝቶ ምፀት ከመሆን አያልፍም።
ትንሳኤው የደስታና የሰላም እንዲሆንላችሁ ከልቤ ስር እመኛለሁ። ፍቅርና መደማመጡን ይስጠን። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!