>

“ኢትዮጵያ ለዘላለም ብትኖር ምን ችግር አለው?” (ናትናኤል መኮንን)

ተወዳጁ ሸገር 102.1 ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ፤ “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር” የሚለውን ቃል እንደ መፈክር በማስተጋባት ይታወቃል። ከመፈክርም በላይ ግን የጣቢያው መሪ ቃል ሆኗል፡፡ የሬዲዮ ጣቢያው የፕሮግራሞች መክፈቻና መዝጊያ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የሸገር ሬዲዮ ሌላ ስሙ እስከ መሆን ደርሷል – “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር”!! በሚያስገርም ሁኔታ ግን ሸገር ይሄን ቃል መጠቀሙ የማያስደስታቸው ወገኖች እንዳሉ የጣቢያው ሃላፊዎች ይናገራሉ። “የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች” ለሚል ፍረጃም ዳርጓቸዋል፡፡ “ይሄን ቃል ለምን እንደማይወዱት ግን አናውቅም” ይላሉ – ሃላፊዎቹ፡፡
እንዲያም ሆኖ ይህ በሸገር ለዓመታት ሲዘመር የዘለቀው “ኢትየጵያ ለዘለዓለም ትኑር” የሚል የመልካም ምኞት ቃል፣ በሬዲዮ ጣቢያው ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎች የሚያዜሙት ቃል እየሆነ መጥቷል። አዲሱ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትርም ታሪካዊውን ንግግራቸውን የቋጩት በዚህ ቃል ነው፡፡ ሸገሮች ምን ተሰምቷቸው ይሆን? ለመሆኑ ቃሉን ለጣቢያቸው የመጠቀም ሃሳብ ከየት መነጨ? ምን ተግዳሮትስ ገጠማቸው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ሸገር ሬዲዮን ከመሰረቱትና ከሚመሩት አንዱ የሆነውን አርቲስት ተፈሪ ዓለሙን በዚህ ዙሪያ አነጋግሮታል፡፡
“ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር” የሚለውን መሪ ቃል መጠቀም የጀመራችሁት እንዴት ነው?
 ከዛሬ 19 ዓመት በፊት በኤፍኤም አዲስ 97.1 ሬዲዮ ላይ የ”ጨዋታ” ፕሮግራምን በጀመርን ወቅት ፕሮግራማችንን ስናስተዋውቅ፣ ”ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር” እንል ነበር፡፡ በመጀመሪያ የ”ጨዋታ” ፕሮግራምን ስናዘጋጅ ዝም ብለን ጀመርነው፡፡ ከዚያ በኋላ የፕሮግራማችን መሪ ቃል (Moto) አደረግነው፡፡
ጣቢያው ውስጥ ተነጋግራችሁበትና ተመካክራችሁበት ነው የጀመራችሁት?
አይደለም፡፡ ስለ ሀገር ጉዳይ በምናነሳ ወቅት በማሳረጊያችን በልማድ “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር” እንል ነበር፡፡ በኋላ ግን ለምን የፕሮግራማችን መክፈቺያና መዝጊያ አይሆንም ብለን ሲጀመርም ሲጠናቀቅም ቃሉን ወደ መጠቀም ገባን፡፡ በዚህ ሁኔታ እየተለመደ መጣና አጠናክረን ቀጠልንበት። በኋላ እንደውም ያልተገባ ትርጉም ሲሰጠው፣ እኛ አጠናክረን ነው  የቀጠልንበት፡፡ አሁን ግን ሸገር ላይ የምንጠቀምበት አውቀን፣ ሆን ብለን መሪ ቃላችን (Moto) በማድረግ ነው፡፡
መሪ ቃሉን መጠቀም ከጀመራችሁ በኋላ የገጠማችሁ ተግዳሮት ነበር?
ብዙ ጊዜ ቃሉ እንዲባል አይፈለግም ነበር። በወቅቱ እንደውም አንድ የጣቢያው ኃላፊ፤ ”ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር የምትሉት የምን መፈክር ነው? በመፈክር ሃገር አያድግም” ብለው አነጋግረውን ነበር። በወቅቱ እኔም፤ “ኢትዮጵያ ለዘላለም ብትኖር ምን ችግር አለው?” ብዬ ለመመለስ ሞክሬ ነበር፡፡ እሳቸው ግን “አይ ተፈሪ፤ ልክ እናንተ ቃሉን ስትሉት፣ ሀገሪቷ ላይ ችግር ያለ ይመስላል” ብለውኛል፡፡ ከዚህ ውጭ ሌሎች ለምን ቃሉን እንደማይወዱት አይገባኝም፡፡ ብዙ ጊዜ ደስ አይላቸውም ነበር፡፡ “የትኛዋ ኢትዮጵያ…?” ምናምን በሚል ለማጣጣል ነው የሚሞከረው፡፡ መቼም “የዚህኛው የዚያኛው መንግሥት ኢትዮጵያ” ማለት አይቻልም፡፡ ግን ቃሉ አይወደድም ነበር፡፡
ኃላፊዎች ከማነጋገር ባለፈ የወሰዱት እርምጃ የለም?
የለም፡፡ ዝም ብለው “ለምንድን ነው የምትጠቀሙት” ነበር የሚሉት፡፡ እኛም ክርክራችን፤ “ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ብትኖር ችግሩ ምንድን ነው?” የሚል ነበር። ምናልባት እነሱ ድሮ የሚባል ነገር ስለሆነ እንዲሁ ቃሉ ከብዷቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ሃገር መውደድ ድሮም ነበር፤ አሁንም አለ፡፡ ለሃገር ጥሩ መመኘት ድሮ ኖሮ፣ አሁንም ብትመኝ ምን ችግር አለው? ብዙ ጊዜ ተፅዕኖ ነበር እንጂ ሌላ እርምጃ ውስጥ አልተገባም። አሁን በሸገር ላይ ያሉ ፕሮግራሞች በሙሉ ቃሉን ይጠቀሙበታል። በዚች ቃል ምክንያት “የድሮ ስርአት ናፋቂዎች” የሚሉ ፍረጃዎች መስፋፋት ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም “ውሾች ይጮሃሉ ግመሎች መንገዳቸውን ይቀጥላሉ” እንደሚባለው እኛም ቀጥለንበታል፡፡
ግን በታሪክ ይህን ቃል መጠቀም የተጀመረው መቼ ነው? ማንስ ጀመረው?
ድሮ ከአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ በንግግሮች ማብቂያ ላይ የሚባል ልማዳዊ ንግግር ነው። ረጅም እድሜ ለንጉሡ ወይም ለጳጳሱ ማለት የተለመደ ነበር። በመጨረሻ ላይም ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር! ይሉ ነበር፡፡ በጣም ጎልቶ መባል የተጀመረው እንደውም ከፋሽስት ወረራ በኋላ ነበር። ምክንያቱም ሃገር ያለመኖር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በወቅቱ አይታወቅም፡፡ ከወረራው በኋላ ግን በብዙ ንግግር ውስጥ ይገባ ነበር፡፡ እኛም ያንኑ ነው የተጠቀምነው፡፡ ስለ ታሪክ፣ ስለ ማንነት እየተናገርን፣ በዚያው መጠን መደምደሚያችን ይሄ ቃል ነበር፡፡ አሜሪካኖቹም እኮ የራሳቸው የሚሉት፣ ስለ ሀገራቸው የሚግባቡበት የጋራ ቃል አላቸው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ፤ ይሄን ቃል ባልተለመደ መልኩ ተጠቅመውበታል …
ከአሁን በፊት የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ እዚህ መጥተው ንግግር ሲያደርጉ፣ ሁልጊዜ  ቃሉን ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በአማርኛ ነበር ቃሉን የሚሉት፡፡ የቀድሞ ጠ/ሚ ያረፉ ሰሞንም፤ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር የሚለው ቃል፣ ከፎቶግራፋቸው  ጋር ተደርጎ  ይሸጥ ነበር፡፡
ዶ/ር አብይ በንግግራቸው መዝጊያ ላይ  ይሄን ቃል በመጠቀማቸው ምን ተሰማህ?
ለኛማ ደስ ነው የሚለን፡፡ ሁሉም ሰው ቢያስተጋባው መልካም ነው፡፡ ሁሉም እየተቀበለው ሲሄድ፣ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር መባሉ ልክ እንደነበርን ያረጋግጥልናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሰው ቢለው ደስ ይለኛል፡፡ የዕለት ፀሎታችን ቢሆን ደስ ይለናል። ለሀገራችን ያለንን ምኞት የምንገልፅበት ስለሆነ ቃሉ መልካም ነው፡፡
Filed in: Amharic