>
5:31 pm - Monday November 12, 9106

ጎንደር በእስር ላይ የሚገኙ 6 ወጣቶች ይናገራሉ! (በጌታቸው ሽፈራው)

1) መስፍን  አረጋ
የተወለድኩት ጎንደር ክፍለ ሀገር ወልቃይት ጠገዴ ነው።  አባቴ አዲስ አበባ አሜሪካን ኢምባሲ   ሰራተኛ ስለነበር ያደኩት አዲስ አበባ ነው።
በ1989  ወደ አሜሪካን ሀገር ተሰደድኩ።  በ2006 ወደ ሀገሬ ተመልሼ የኢንቨስትመንት መሬት ብጠይቅም ማግኘት አልቻልኩም።  ለመስራት በነበረኝ  ፍላጎት መሬት ተከራይቼ ስሰራ ቆይቻለሁ። በ2008 ዓም ጎንደር ላይ በነበረው ሰልፍ  ከሕዝብ ጋር በመሆን የአቋም መግለጫ ሰጥተሃል በሚል  ከታህሳስ 4/2009 ዓም ጀምሮ  በመከላከያ ካምፕ ከታሰርኩ በኋላ፣ ጥር 13 ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስጀ ታስሬያለሁ።  እስከ ሰኔ 22/2009 ዓም  ማዕከላዊ ታስሬያለሁ። ከእስር ተፈትቼ ወደ ጎንደር ከተመለስኩ በኋላ መሬት በመከራየት ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ እያለሁ  የካቲት 14/2010 ዓም  ጠዋት 1 ሰዓት  ወደ ቤተ ክርስትያን እየሄድኩ  ከ30 በላይ በሚሆኑ የታጠቁ ሀይሎች ተይዤ  እና  በአደባባይ ተደብድቤ ያለ ወንጀሌ እስር ቤት እገኛለሁ።
2) ጓዴ ፈለቀ:
ጓዴ ፈለቀ እባላለሁ። በ1990 በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በ15 አመቴ ሀገራዊ ጥሪ ተቀብዬ  ሰራዊቱን ተቀላቅያለሁ።  በ1997 ዓም አመታዊ እረፍት ወስጄ ስመለስ  የተወሰነ ቀን አሳልፈሃል በሚል ከሰራዊቱ አስወጥተውኛል።  7 አመት በላይ አገልግሎቴን በ305 ብር የትራንስፖርት  ብር ብቻ ሰጥተው አባርረውኛል።
ይህ ሳይበቃቸው የካቲት 12/2010 ዓም ጠዋት 11 ሰዓት ከቤቴ ድረስ በመምጣት “አድማውን ያሳደምከው አንተ ነህ” ብለው አስረውኛል። በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ እገኛለሁ።
3) ካሳሁን ጥላሁን እንየው:_
የተወለድኩት  በ1983 ጎንደር ከተማ ቂርቆስ አካባቢ ነው። እስከ 10ኛ ክፍል እድገተ ፈለግ ተማርኮ። የኮሌጅ ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ።  ስራ አልያዝኩም። የካቲት 14/2010 ዓም “አድማ አስደርገሃል” በሚል ሰበብ በእስር ላይ እገኛለሁ።
4) አብርሃም:_
አብርሃም እባላለሁ። የተወለድኩት ጉራጌ ዞን ነው። ትምህርቴን አቋርጬ ወደ ንግዱ አለም የዞርኩ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ሰርቻለሁ። ወደ ጎንደር በመምጣት በሆቴል ስራ ተሰማርቻለሁ። ግሪን ሀውስ እና አደት የሚባል ሆቴል ከፍቼ በመስራት ላይ እገኛለሁ።   የካቲት 11/2010 ዓም ከሌሊቱ 11 ሰዓት ወደ ሚካአል ቤተክርስትያን እየሄድኩ እያለ “አድማ አድርገሃል፣ አድማ አስደርገሃል” በሚል ሰበብ ተይዤ ታስሬያለሁ። በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ  እገኛለሁ።
5) ግርማቸው ያለው:_ 
<ግርማቸው  ያለው  እባላለሁ። የተወለድኩት ጎንደር ከተማ አባጃሌ ቀበሌ ነው።  ጎንደር ውስጥ  እየሰራሁ እኖር ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  መንግስት ስራ እንዳንሰራ፣ ሰርተን እንዳንጠቀም ተንኮል እየፈፀመብን ይገኛል። በዚህም ምክንያት ስራ አጥቼ  ቆይቻለሁ። ሁሉም ነገር በዘር እየተለካ ከምንም አይነት ስራ እንዳንደርስ ብዙ ችግር ደርሶብናል።
በማንነታችን በሚደርስብን በደል ሳንሸማቀቅ  ሌቦችንና ሀሰተኞችን ስንቃወም ኖረናል። ጎንደር ከተማ በተደረገ ተቃውሞ ሰበብ ወከባ ሲደረግብኝ ቆይቷል። በዘንድሮው ጥምቀት  ንፁሁን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዘሃል በሚል፣ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለኝን ልዩነትና  ተቃውሞ ስለምፅፍ  በጥምቀት በዓል የያዝኩትን ሰንደቅ አላም ሰበብ በማድረግ  የካቲት 13/06/2010 ዓም ጀምሮ ጎንደር አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሬ እገኛለሁ።
6) መሳፍንት መዝገቡ (ዱቼ):_
∠ ከታሰሩት መካከል መሳፍንት መዝገቡ፣ መጋቢት 3/2010 ዓም ቀበሌ 18 የታዘ ሲሆን 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ ይገኛል።  “ተደራጅተህ ካልሰራህ አንፈታህም” የሚል ጥያቄ ቀርቦለታል። መሳፍንት  ከሁለት አመት በፊት በመካኒካል ኢንጅነሪንግ  ተመርቆ፣ ስራ አላገኘም።
አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች በ2008 ዓም ሕዝባዊ ሰልፍ መርተዋል በሚል ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩ እንዲሁም በ2009 ዓም በኮማንድ ፖስቱ ታስረው የተፈቱ እንደሆኑ ተገልፆአል።
(ፎቶው የመሳፍንት መዝገቡ እና   የግርማቸው ያለው ነው)
Filed in: Amharic