>

ከፀሃዩ ንጉስ፤ ወደ አምፖሉ መሪ (በእውቀቱ ስዩም)

መጋቢ ሀዲስ እሸቱ ከማደንቃቸው ጥቂት የሃይማኖት ሰባኪያን አንዱ ናቸው፤የጣፈጠ አንደበት እና ብሩህ አእምሮ ታድለዋል፤ የተናገሩት የሰበኩት አያመልጠኝም፤ ባሳለፍነው ቅዳሜ፤የፀሃይንና የመሪን ባህርይ አነፃፅረው፤ያቀረቡት አስተያየት ጋር መስማማት ከበደኝ፤
ምክንያቴን ከመናገሬ በፊት መጋቢ ከተናገሩት ይቺን ልቆንጥር፤
“በሃይማኖት አስተምህሮ፤መሪዎች በፀሃይ ይመሰላሉ፤ፀሃዩ ንጉስ ይባሉ ነበር፤ነገስታቱ፤መሪዎች የፀሃይነት ሚና ሊኖራቸው ይግገባል፤በዐለም ላይ ፀሃይ ትልቁ የብርሃን ምንጭ ነው፤ከዚያ ቀጥሎ ነው፤አምፖል ጡዋፍ ሻማ ኩራዝ የሚመጣው፤እነዚህን ደግሞ ሰው እየለኮሰ ራሱ ያጠፋቸዋል፤ፀሃይ ግን በሰው ትእዛዝ የምትወጣ የምትገባ አይደለችም፤ስለዚህ መሪዎች እንደ አምፖል በቆጣሪ ሳይሆን እንደፀሃይ በፈጣሪ የሚታዘዙ መሆን አለባቸው፤”
ንፅፅሩ በፍፁም ቅንነት የተሰነዘረ መሆኑን ባውቅም፤ የመሪና የተመሪን ግኑኝትና ባህርይ የሚያሳይ ሆኖ አልታየኝም፤ ሲጀመር መሪዎች እንደ ፀሃይ ”ትልቁ የብርሃን ምንጭ” ናቸውን?፤ በዚህ አለም ላይ ያለው የመሻሻል ፍሬ ያስገኙት ፈብራኪዎች፤ ፈላስፎች፤ሀኪሞች፤የትሩፋት ሰዎች፤ የኪነት ሰዎች፤እንዲሁም በፍፁም ስልጣን ላይ የሚያምፁ ያበጀ በለው ብጤ ሽፍቶች አይደሉምን?፤ ታሪክ እንደሚያሳየን ያብዛኞቹ የስልጣን ሰዎች ሙያ፤ የተለኮሰ ብርሃን ማኮላሸት ነው፤በየዘመኑ  አንዳንድ አሪፍ መሪዎች መነሳታቸውን አልክድም፤ግን ከፀሃይ ጋር መነፃፀራቸውን ኩሸት አይሆንም?
መጋቢ ሀዲስ እንዳስታወሱት፤ “ፀሃዩ” የሚል ቅፅል የተሸከሙ ነገስታት/ንግስታት ሞልተዋል ፤ግን ይህን የተጋነነ ቅፅል የሚያገኙት ከሰፊው ህዝብ ሳይሆን ከጥቂት ጥቅም ተቁዋዳሾች ነበር፤  እቴጌ  ምንትዋብ ስልጣን ስትይዝ ፤ “አሁን ወጣች ጀንበር፤ተሸሽጋ ነበር” ተብሎ እንደተዘፈናላት የዜና መዋእል ፀሃፊዋ መዝግቦታል፤ በዘመኑ ከስልጣኑዋ በረከት የቀመሱ ስዎች የዘፍኑት መሆኑ አያጠያይቅም፤የንግስቲቱ ስልጣን ሰለባ የነበሩ ሰዎች ይህንን ዘፈን የሚያስተጋቡ አይመስለኝም፤ፍፁም ስልጣን የሰበሰበ ሰው ለጭፍሮቹ ጀንበር ፤ለብዙሀኑ ግን የቀን ጨለማ መሆኑ ታሪካዊ ሀቅ ነው፤
የንፅፅሩ ትልቅ ችግር  “ፀሃይ በሰው ትእዛዝ የምትወጣ አይደለችም ”የሚለው ነው፤ መጋቢ ሀዲስ ስለ ነጂዎች (አምባገንኖች) የሚያወሩ ቢሆን ማመዛዘኛው ትክክል ይሆን ነበር፤ አምባገነኖች የሰውን ትእዛዝ ሳይሆን የገዛ ፈቃዳቸውን ነው የሚከተሉት፤ “እንደሻው” የሚል የጅምላ ስም ይመጥናቸዋል፤የግል ፈቃዳቸውን የግዜር ፈቃድ ብለው ይጠሩታል፤
መሪዎች ግን የህዝብ ትእዛዝ የሚንቀሳሱ መሆን አለባቸው፤ በህዝብ ፈቃድ የማይንቀሳቀስ ባለስልጣን “መሪ” የሚል ስም አይመጥነውም፤ከፀሃይ በተቃራኒ ያገር መሪ በህዝብ ትእዛዝ የሚወጣ የሚገባ መሆን አለበት፤ እንደኔ እንደኔ መሪ አምሳያ ፀሃይ ሳይሆን አምፖል ነው፤አምፖልን ትመርጠዋለህ፤አውጥትህ ትሰቅለዋለህ፤ከተበላሸ በሌላ የተሻለ አምፖል ትቀይረዋለህ፤
የቴዎድሮስ ዳኜ እይታ እና አረዳድ
ዌል እንግዲክ …. ለኔ እንኳን ችግሩ የመጋቢ ሃዲስ አባባል ሳይሆን፣ የበውቀቱ አረዳድ ይመስለኛል። እሳቸው መሪዎች ፀሐይ ናቸው አላሉም፣ ያሉት “መሪዎች ፀሐይ መሆን አለባቸው” ነው። ያ ማለት በውቄ እንደተረዳኸው ለሁሉም መሪዎች የተሰጠ መደምደሚያ አይደለም።
በትክክል ሃሳባቸውን አለመረዳትህ ደግሞ በግልጽ የሚታየው በመጨረሻው አንቀጽህ ላይ “መሪዎች እንደ አምፖል መሆን አለባቸው፣ አሞፖልን ትሰቅለዋለህ፣ ወይም አውጥተህ ትቀይረዋለህ” ማለትህ ነው። በአንድ አገር ላይ በቤት ቁጥር ልክ አምፖል አለ፣ ለዚያ አምፖል ሃላፊው እያንዳንዱ ቤት ነው፣ ያንተን ብትጥል የኔ ከተሰማማኝ እዚያው ይሆናል፣ መሪ እንደ ፀሐይ ነው ሲባል ግን ሁላችንም አንድ ፀሐይ እንዳለን ሁሉ፣ ለሁሉም የሚሆን መሪ አለ፣ ግለሰቦች እንደፈለጉ (ህዝብ አላልኩም) ግለሰቦች እንደፈለጉ እንደ ቦይ ውሃ የሚነዱት፣ በራሱ ሃሳብ የማይመራ፣ አሻንጉሊት መሆን የለበትም፣ ለሁሉም እኩል የሚያበራ፣ ሁሉንም (ያለ ልዩነት) የሚያገለግል ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
በውቀቱ የተረዳኸው በትክክል አልመሰለኝም። የመሪ ባህርይ ከፀሐይ ባህርይ ጋር አንድ መሆን አለበት የሚለውን ሃሳብ ፣ መሪ ሁል እንደ ፀሐይ ነውና ተገዙለት ያሉ አስመሰልከው። በውቄን ተሳስተሃል ለማለት በመድፈሬ ከይቅርታ ጋራ።
Filed in: Amharic