>

ለጻድቃን ይተርፋል (ደረጀ ደስታ)

ሌተና ጄኔራል ጻድቃን በቅርቡ ለሪፖርተ ሲናገሩ እሚከተለውን ብለዋል። የተሾሙትን ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹሞች ሁሉንም አውቃቸዋለሁ፡፡ ከተሾሙት መካከል ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጄኔራል ብርሃኑ ጁላን ነው ለውድድር የማቀርበው፡፡ ጄኔራል ሰዓረን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ነው የማውቀው፡፡ ረዥም ልምድ ያለውና በብቃቱም በስትራቴጂካዊ አመራሩም የሚታወቅ ነው፡፡ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላንም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አውቀዋለሁ፡፡ ክፍለ ጦር እየመራ በብቃት ኃላፊነቱን የተወጣ ነው፡፡ እኔ የክፍለ ጦር አዛዥ እያለ ነው የወጣሁት፡፡ ከዚያ በኋላ በሱዳን ሰላም ማስከበር ተሳትፏል፡፡ የምዕራብ ዕዝ አዛዥም ነበር፡፡ እኔ ካወቅኩት 17 ዓመት አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ሥልጣን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ግዳጆችን ተወጥቶ የመጣ አመራር ነው፡፡ ጄኔራል ብርሃኑ ከጄኔራል ሰዓረ በልምድ በትንሹ ዝቅ ቢልም፣ ቀጣዩ የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም እንዲሆን ነው የምመርጠው፡፡ አሁን ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ትልቅ ነው የሚሆነው፡፡ የትግራይ ተወላጆችን እንደ እንቁላል የሚጠብቅ ሥርዓት ነው የሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲቀር ለማድረግና የብሔር መመጣጠንን ለማምጣት ጠቃሚ ነው፡፡
ሌሎች በጠላትነት ተፈርጀው፣ ሲሰደዱ፣ ሲታሰሩና ሲገደሉበት እሳቸው እንደፈለጋቸው እየተናገሩና እንደፈለጋቸው እንዲነግዱ እንደ እንቁላል እሚጠበቁት ጀኔራል ፃድቃን የሰጡት አሰተያያት አሁን ተፈጻሚ እሚሆን ይመስላል እየተባለ ነው። ጀኔራል ሳሞራ ተነስተው ብርሃኑ ኤታማዦር ሹም እንዲሆኑ ታጭተዋል። ጌታቸው አሰፋን በማንሳት ወርቅነህ ገበየሁን ደህንነት ሹም ለማድረግ በወርቅነህ ፋንታ ደግሞ ተሾመ ቶጋን ለውጭ ጉዳይ በማጨት ዝርዝርና ክርክር እየተካሄደ መሆኑም እየተሰማ ነው። ጻድቃን ምንም እንኳ ሰዓረ የተሻሉ ቢሆኑም ብሄር አመጣጥኖ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲቀር ብርሃኑን ማድረጉ ጠቃሚ ነው ሲሉ ባንድ ሰው ቦታ መለዋወጥ የአገር ግንዛቤ ይስተካከላል ብለው ማሰባቸው ምንኛ ንቀት አላቸው ብሎ ማሰብ ይቻላል። ከአንድ ጎሳ የተቀዳውን ያን ሁሉ ጀኔራልና የአዛዦች መንጋ የተሳሳተ ግንዛቤ ብቻ ብሎ ማቅለሉም ልክ አይደለም። እንደዚያ ያለ ንቀትና ድርቅና ላይ መግባባት ከሌለ ለሳሞራ የመጣው ቁጣ ለጻድቃንም መትረፉ አይቀርም ። ጨዋታው ሠራዊቱ ውስጡን እንዲቀይር በሚፈለጉ እና ሠራዊቱ ራሱ እንዲቀየር በሚፈልጉ መካከል መሆኑ አልገባቸውም። ለውጥ በሚናድ ቡድን ጭምር እንጂ በሚቀየር ሰው ብቻ አይመጣም መባሉም ለዚህ ነው። ዛሬ ነቅሎ የወጣው የአምቦ ህዝብ አብይን ደግፎ ሳይሆን ህወሓትንም ነቅፎ ነው። የተሳሳተ ግንዛቤ ስላለው ብቻ ሳይሆን የቡድን አገዛዝ ሊያበቃ መንገድ የተያዘም መስሎት ነው።

Filed in: Amharic