>
5:30 pm - Friday November 1, 1382

HR 128  መጽደቅ ለመሰረታዊ የመብት ትግላችን ታላቅ  ድጋፍ ነው (ሸንጎ)

HR 128    መጽደቅ ለመሰረታዊ የመብት ትግላችን ታላቅ  ድጋፍ ነው

ሸንጎ ህጉን ይደግፋል፤ ለተፈጻሚነቱም ተግቶ ይፋለማል

HR 128   ተብሎ  የሚታወቀው  ባሜሪካ ኮንግረስ  (ፓርላማ ) ውስጥ  ለውሳኔ ቀርቦ የነበረው በኢትዮጵያ መንግስት የመብት አያያዝ ላይ ያተኮረ የህግ ረቂቅ እነሆ ትናንት መጽደቁ ተነገረ። በውጭ አገር ያሉ የሰብዓዊ መበት ተከራካሪዎችና የተደራጁ ኢትዮጵያውያን ይህ የህግ ረቂቅ እንዲጸድቅና በስራ ላይ እንዲውል ለረጅም ጊዜ ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያድርጉ ቆይተዋል። ሸንጎ ለዚህ ስኬት ታጥቀው ለታገሉ ሃይሎች በሙሉ ያለውን አድናቆትና ክብር እያስታወቀ፤ የረቂቁ ህግ ሆኖ መጽደቅ ለኢትዮጵያ ህዝበና  ለመላው የዴሞክራሲ ሃይሎች ታላቅ ድል መሆኑን ይገልጻል።

ይህ ህግ ካካተታቸው ዋና ዋና ድንጋጌወች ውስጥ፤

    • አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በግልጽ ይጠይቃል
    • በተለያዩ ክልሎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተፈጸሙ ግድያዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩ ይደነግጋል
    • መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች በተለይም የሚዲያ ነጻነት ሀሳብን በነጻ የመግለጥ መብት እንዲከበር አጥብቆ ይጠይቃል
    • የሰብአዊ መብት ጥሰት ያካሄዱ በተለይም የገደሉና ሌሎችንም ስቃዮች የፈጸሙ ወንጀላቸው ተጣርቶ ለፍርድ እንዲቀርቡ ያወሳል
    • በቀጣይነትም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ መውሰድ እንዲያቆሙ ወዘተ የሚያስገድዱ ድንጋጌዎች ይጨምራል
    • አዲሱ ህግ የኢትዮጵያ መንግስት ቢያፈነግጥ ወይም ይህን አላደርግም ቢል እንደማስገደጃ ሆነው ሊጠቅሙ የሚችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመሳሌ  ማእቀብ መጣል እርዳታ መከልከል ወዘተ ማስገደጃወችን  ያካተተ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በዓመት እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ እርዳታ ከአሜሪካ መንግስት ስለሚቀበል ይህን ከፍተኛ እርዳታ እንዳያጣ ይህን  ህግ ሳይወድ ተግባር ላይ ለማዋል ይገደዳል የሚል አንደምታ አለ። አሁን እንግዲህ ህጉ ስለጸደቀ ሀገራችን ውስጥ ሰብአዊ መብትን ለማስከበር ታላቅ ድጋፍን ለህዝባችን ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

ዶክተር አብይና ደጋፊወቻቸውም መሰረታዊ የመብት መከበርን፣ የህግ የበላይነትን ወዘተ ለማስከበር ቆርጠናል ብለው በተናገሩት መሰረት የሰጡትን ቃል ጠብቀው ተግባራዊ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ይህን ድንጋጌ መቀበላቸውን ሊያሳዩን ይገባል። ይህንንም በይፋ ቢያሳውቁ ለህዝባችን መብት መከበር ያላቸውን ፍላጎትና ቁርጠኛነት ይበልጥ ያሳያል፣ ይበልጥ የህዝብ ድጋፍም ያሰገኝላቸዋል።

ሸንጎ ከአገራችን ዜጎች ጎን ቆሞ ለሁላችንም መብት መከበር አሁንም ጠንክረን መታገል እጅግ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። በውስጥም በውጭም የሚደረገው ሰላማዊ ትግል ውጤት እያሰመዘገበ ቢሆንም ገና የሚፈለገውን ግብ አልመታም፤ የምንፈልገውን መብት አላጎናጸፈንም። ለዚህም ነው እንደ ቀደምት ተማሪወች አሁንም

ነጻነት ነጻነት የምትሹ

ታገሉለት አትሽሹ           

የሚለውን መፈክር ከፍ አድርገን በማሰማት ትግሉን አጠናክሮ መግፋት ያለብን፡

የተባበር ትግል ያሸንፋል!

ለሰብዓዊ መብታችን፤ ለፖለቲካ ነጻነታችን ሳናሰልስ እንሟገታለን !

Filed in: Amharic