በሳውዲ አረቢያ መንግስት በሙስና ተጠርጥረው አብዛኛው የሃብታቸውን
መጠን ከተወረሰባቸው ቱጃሮች አንዱ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሼህ
መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ችግር ከነጓዙ የመጣባቸው ይመስላል። አሁንም
ድረስ በሳውዲ መንግስት የቁም እስር ውስጥ የሚገኙት ሼሁ ከነበራቸው የ8
ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሃብት በሳውዲ መንግስት 7.1 ቢሊዮን ዶላሩ መወረሱ
ለከፋ ህመም እንደጣላቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ
በተለያዩ አካባቢዎች ለበርካታ ዓመታት በሼሁ የሚድሮክ ኢትየጵያ ታጥረው
የተያዙ ሰባት ይዞታዎች ውል ሊቋረጥ መሆኑ ተሰምቷል። ባሳለፍነው ሳምንት
በሚድሮክ ኢትየጵያ በ 55 ሺህ ካሬ ሜትር የተያዙ ሁለት ይዞታዎች ውላቸው
በከተማው አስተዳደር እንደሚቋረጥ ታውቋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት
ባንክና ማሰተላለፍ ጽህፈት ቤት የሊዝ ክትትልና አፈጻጸም ዳይሬክተር አቶ በየነ
ላጲሶ ቢሮ አካባቢ ካሉት ምንጮቻችን እንደሰማነው ባሳለፍነው ሳምንት
ውላቸው የተቋረጡ ሁለት ይዞታዎች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ-ከተማ ለበርካታ
ዓመታት ሳይለሙ ታጥረው የተያዙት ናቸው ተብሏል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ውላቸውን
ለማቋረጥ ዝግጅት ከተደረጉባቸው መካከልም በሚድሮክ “ኢትየጵያ ለልማት”
በሚል ታጥረው ሳይለሙ የተቀመጡ ሰባት ይዞታዎችም ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ከነዚህም ይዞታዎች መካከል በሜክሲኮ፣ በሰሚት፣ በቦሌ ወሎ ሰፈር ሁለት
ይዞታዎች በየካ፣ ቂርቆስ፣ ባጠቃላይ ከ104 ሺህ በላይ ካሬሜትር የታጠሩ
ቦታዎች ናቸው ውላቸው ይቋረጣል የተባለው። እንዲሁም ሚድሮክ ኢትዮጵያ
አጥሮ የያዛቸው የሸራተን ማስፋፈፊ እና በፒያሳ ለበርካታ ዓመት የታጠረው
ይዞታ በቀጣይ ጊዜ የሚታይ ይሆናል ተብሏል። ይህ በፒያሳ የታጠረው ቦታ ከ
10 አመት በላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ ደብረ ገነት ጽጌ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንና በሚድሮክ ኩባንያ መካከል የይዞታ ይገባኛል
የፍርድ ቤት ክርክር አሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን የሚድሮክ ውል የሚቋረጥ
ከሆነ ይዞታው ወደ ቤተክርስቲያኒቷ የሚመለስበት እድል አለው። ይህ ስፍራ
ቤተክርስቲያኒቷ በቀደምት ጊዜ ለመስቀልና ለጥምቀት በአላት ትጠቀምበት
እንደነበር ይታወቃል። እንዲሁም በማዕድንና በእርሻ ላይ የተሰማሩት እንደ
ሳውዲ ስታር ያሉ የሚድሮክ ኩባንያዎችም በሃገሪቱ በተከሰቱ የአለመረጋጋት
ሁኔታ ከፍተኛ ኪሳራ የገጠማቸው ሲሆን ደርባ የሲሚንቶ ፋብሪካም በውጭ
ምንዛሬ ግሽበትና እጥረት ምክንያት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ላይ ችግር በመፈጠሩ
ኩባንያው ምርት እስከማቆም ድረስ ለችግር መጋለጡ ታውቋል። ሚድሮክ
ኢትዮጵያ ሊፈርስና ወደ ጨረታ ሊያመራም እንደሚችል በኩባንያው በተለያዩ
ስፍራዎች የሚሰሩ ሰራተኞች ዘንድ “እንበተን ይሆን?” ከሚል ፍርሃት በሰፊው
እየተወራ ይገኛል።
ብዙዎች ዘንድ ሼሁ ከመንግስት ባለስልጣናት ዘንድ ካላቸው ቅርበት የተነሳ
ሚድሮክ ኩባንያ ፍትሃዊ ያልሆነ ተግባሮችን ሲፈፅም በመንግስት ተቋማት ችላ
እንደሚባል ያወሳሉ። በመጨረሻም የሼሁ ጉዳይ ያሳሰባቸው ግለሰቦች ለውጭ
ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል። ምንጮቻችን ባደረሱን መረጃ
መሰረት ግለሰቦቹ “ሼሁ ለሃገሪቷ ካደረጉት ውለታና እርዳታ አንፃር መንግስት
ተገቢውን ድጋፍ እየሰጣቸው አይደለም” ብለው በደብዳቤያቸው የገለፁ ሲሆን
መንግስትም በዲፕሎማቲክ ደረጃ ከሳውዲ መንግስት ጋር መነጋገር እንዳለበት
አሳስበዋል። እንደምንጮቻችንም ከሆነ ደብዳቤው ውስጥ የተካተቱት የሚድሮክ
ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አዲሱ አረጋ፣የሚድሮክ የህግ ጉዳዮች ሃላፊ አርቲስትና
ጠበቃ አበበ ባልቻ፣ አርቲስት ንዋይ ደበበ፣ ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁን፣አርቲስት
ማህደር አሰፋ፣አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬና ሌሎችም እንዳሉ ታውቋል።