በዚህና በሌሎች ምክንያት ሴኔቱ (የሕግ መወሰኛው ምክር ቤት) ምን ሊወስን እንደሚችል ለመገመት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በግሌ ይሄንን የውሳኔ ሐሳብ ምክር ቤቱ ያለ አንዳች ተቃውሞ ያጸደቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሜሪካ መንግሥት ጨርሶ ተስፋ እንዳይቆርጥ ለማድረግና ላለማሳፈር ያህል በምክር ቤቱ እንዲያልፍ ተደረገ እንጅ በሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አልፎ በፕሬዚዳንቱ (በሊቀ ሥልጣናቱ) ተፈርሞ ተፈጻሚ ለማድረግ በማሰብ ከምክር ቤቱ አሳልፈውታል ብየ እንዳላምን ከዚህ ቀደም የነበረው የሎቢ (የአግባቢ) ጨዋታ አባዜያቸውና የወያኔ አሜሪካ የጥቅም ትስስር ጉዳይ ከልክሎኛል፡፡
ለአሜሪካ መንግሥት ከሕዝብ ልጆች የውሳኔ ሐሳቦች ሲቀርቡ ይሄ HR 128 የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ተቆርቋሪ ዜጎች ከሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከበፊት ጀምሮ ለበርካታ ጊዜያት የአሜሪካ መንግሥት ለወያኔ የሚያደርገውን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያላገናዘበ ድጋፍና እርዳታ እንዲያቆም፣ የወያኔ ባለሥልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የባንክ (የቤተንዋይ) ሒሳባቸው እንዳይንቀሳቀስ፣ ከሀገር ወደ ሀገር የመዘዋወር ነጻነታቸው እንዲገደብ ወዘተረፈ. የሚጠይቁ በርካታ የውሳኔ ሐሳቦች ሲቀርቡና ወያኔ በቀጠራቸው ሎቢዎች (አግባቢዎች) እንዲጨናገፉ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ለአሜሪካ መንግሥት ሲቀርቡ ከነበሩት የውሳኔ ሐሳቦችም ከፊሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫና ባሳደረ ቁጥር ሁኔታውን ለመቆጣጠር በማሰብ ሆን ተብሎ በራሱ በአሜሪካ መንግሥት አቀናባሪነት ግንጽ ባልሆነ መንገድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በድንገት የውሳኔ ሐሳብ ጥያቄውን እንዲያቀርቡ ወይም እንዲያነሡ እየተደረገና ሒደቱም ረጅም ጊዜ እንዲወስድ እየተደረገ የኢትዮጵያ ሕዝብ አጉል ተስፋ እንዲሰንቅና እንዲጠብቅ ሲደረግ ይቆይና መጨረሻ ላይ እዚህ ግባ በማይባል ምክያያት፣ አንዳንዴም ያለምንም ምክንያት የት እንደደረሰ ሳይታወቅ በሎቢዎች (በአግባቢዎች) ተሳቦ ተዳፍኖ እንዲቀር እየተደረገ ወያኔ ጊዜ እንዲገዛና ዕድሜው እንዲራዘም ሲደረግ እንደቆየ እናውቃለን፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ የውሳኔ ሐሳብ ወይም የረቂቅ ሕግ ጨዋታ ነገር ዛሬ እዚህ ላለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ የውሳኔ ሐሳብ በተንቀሳቀሰ ቁጥር ወያኔ የሚያሰማው ቁጣ፣ ኩርፊያም በሉት ማስጠንቀቂያ እና ይሄንን ተከትሎ የሚመጣው የአሜሪካ መንግሥት መለዘብ ብዙ ነገሮችን ይናገራል፡፡ አንዱና ዋነኛው የሚነግረን ነገር ወያኔና አሜሪካ የመሠረቱት ግንኙነት ሕገወጥ የጥቅም ግንኙነት መሆኑን፣ ለሰብአዊና ለዲሞክራሲያዊ መብቶች ቅንጣት እንኳ ታክል ቦታ የማይሰጥ ግንኙነት መሆኑን ጥርት አድርጎ ይናገራል ያሳያል፡፡
እንዲህ ባይሆንማ ኖሮ ወያኔም “ሰብአዊ መብትን ማክበሩን፣ ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) መብትን ማስፈኑን፣ ተጠያቂነት ያለው አሥተዳደር መመሥረቱን …… !” አረጋግጥ! ተብሎ ሲጠየቅ ቅንጣትም ሳያፍር ወንጀለኛነቱን ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ “እንዲህ ብላቹህ የምታስገድዱኝ ከሆነማ እናንተን አላገለግልም፣ በፀረ ሽብር ዘመቻው አልተባበርም!” ብሎ ለመመለስ ባልደፈረ የአሜሪካ መንግሥትም “አይ በቃ እንዲህ የሚያኮርፍብን ከሆነማ እንተወው!” እያለ ወያኔ ለ27 ዓመታት ያህል አረመኔያዊ ግፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየፈጸመና አንባገነንነቱ በሚገባ እየታወቀ ግንኙነታቸው ያለምንም ችግር ምንም እንዳልተፈጠረ እስከዛሬ ደርጅቶ ጠንክሮ ሊቀጥል ባልቻለም ነበረ፡፡
አሁን ወያኔ እየተናገረ እንዳለው ለለውጥ ቁርጠኛ ቢሆንና እንዲያከብር የተጠየቃቸውን መብቶች የማክበር፣ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ቀና ፍላጎት ቢኖረው ኖሮ ይሄ የውሳኔ ሐሳብ ፈጽሞ ፈጽሞ የሚያሠጋውና የሚያሳስበው ባልሆነ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ የሠፈሩ ሐሳቦችን በሙሉ ተሿሚው ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ባቀረቡት ጽሑፍ ላይ “በጽናትና በቁርጠኝነት እናደርጋለን!” እየተባለ ተለፍፎባቸው የነበሩ ጉዳዮች ናቸውና፡፡
የአዲሱ ጠ/ሚ ቃል እውነትና በትክክል ሊፈጸም የታቀደ ቢሆን ኖሮ ይሄንን ረቂቅ ሕግ ወያኔ እንደ ጠቃሚና አስፈላጊ ድጋፍ አድርጎ ይመለከተው ይቆጥረው ነበር እንጅ በምንም ተአምር ሊቃወመው አይችልም ነበረ፡፡ ወያኔ እንዲህ ዓይነት የተቃውሞ ወግለጫ በማውጣቱ ያስተላለፈው መልእክት ቢኖር “በተሿሚው ጠ/ሚ በኩል የገባሁት ቃል ሁሉ ውሸት ነው፣ ሕዝብን ለመደለል ነው እንጅ የምፈጽመው አይደለም!” የሚለውን ነውረኛ መልእክት ነው ያስተላለፈው፡፡
እናም ወያኔ ለለውጥ ፈጽሞ ዝግጁና ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ባለሥልጣናቱ እስከዛሬ በፈጸሙት ግፍ፣ ክህደት፣ ወንጀል እና ወደፊትም ሊፈጽሙት በሚያስቡት ግፍ፣ ክህደት፣ ወንጀል ፈጽሞ ተጠያቂ እንዲሆኑ ስለማይፈልግና ስለማይፈቅድም ነው ይሄንንና መሰል ረቂቅ ሕጎችን ወይም የውሳኔ ሐሳቦችን የሚፈራውና የሚቃወመውም፡፡
አሜሪካኖችም “አይ አንተ እየተናገርከው እንዳለኸው ቁርጠኛ የለውጥ ፍላጎት እስካለህ ጊዜና ለተጠያቂነት ጽኑ ፍላጎት እስካለህ ጊዜ እኮ ምንም የሚያሠጋህ ነገር የለም እኮ! እናም በከንቱ ነው የምትሠጋው አትፍራ! ይልቁንም እንደ ቁርጠኛ መንግሥትነትህ ተደሰት!” ብለው አግባብተው ወይም አስረድተው ለማከላከሉ ፊት ሳይሰጡ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ አለን ለሚሉት ቁርጠኝነት በመታመን የሚቀርብላቸውን ረቂቅ ሕግ ያለ አንዳች ማቅማማት በቀጥታ ማጽደቅ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን የግንኙነታቸው መሠረት ኢሰብአዊ፣ ኢዲሞክራሲያዊና ኢየሕግ የበላይነት በመሆኑ ይሄንን ለማለት ዕድል ስለማይሰጣቸው ነው፡፡
ይሄን ይሄንን ጉድ ስለማናውቅ ወይም አሜሪካና ወያኔ ማለት ምንና ምን መሆናቹህን ስለማናውቅ አይደለም ዛሬም እየተማጸናቹህ ያለነው፡፡ ነገር ግን ምናልባት ካለፉት የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት የተሻለ ማሰብና ማገናዘብ ትችሉ እንደሆነ፣ በተሻለ ሰብአዊነትና ኃላፊነት ይሰማቹህ እንደሆነ፣ የቀደምቶቻቹህ ስሕተት የሚጸጽታቹህ እንደሆነ፣ የሀገራቹህ መንግሥት ስም የኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ እንዲህ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ እስከወዲያኛው እንደተበላሸ፣ እንደተጠላ፣ እንደጠለሸ እንዲቀር የማትፈልጉ እንደሆነ ዕድል ለመስጠት ነበር ምንም እንደማናውቅ መስለን አሁንም በሎሌያቹህ በወያኔ ላይ ክስ የምናቀርበውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም በክሱ መሠረትም እርምጃ እንድትወስዱልን የምንገፋፋው፡፡
የአሜሪካ መንግሥት ሆይ! እንዲህ ለዓመታት ኡኡ እያልን የምንጮኸው በየዓመቱ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር መሥሪያ ቤታቹህ በኩል ከሚወጣውና አጥርታቹህ ከምታውቁት የወያኔ ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ግፍ የተለየ ሌላ የማታውቁት የተለየ ግፍና በደል ኖሮ እሱን ልናሳውቃቹህ ስለፈለግን አይደለም ሰርክ የውሳኔ ሐሳብ እያቀረብን ስናስመሰክር የቆየነው፡፡ እናንተ ከእኛ በላይ እያንዳንዷን ነገር ከእኛ ከዜጎች በላይ በሚገባ እንደምታውቁ እናውቃለን!
ስለሆነም ከዚህ በኋላ ማስመሰሉን፣ የሎቢ (የአጋባቢ) ጨዋታውንና በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ መቀለዳቹህን ትታቹህ ይህ አሁን በኮንግረሱ (በምክር ቤቱ) ያለፈውንና ለተፈጻሚነት በሴኔቱ (በሕግ መወሰኛው ምክር ቤቱ) እና በፕሬዚዳንቱ (በሊቀ ሥልጣናቱ) መጽደቅና መፈረም የሚጠብቀውን የHR. 128 የውሳኔ ሐሳብ በማሳለፍ ኃላፊነት እንደሚሰማው ኃያል መንግሥት ልትወስዱ የሚገባቹህን ተገቢ ርምጃ ትወስዱ ዘንድ እጅግ አጥብቀን እንጠይቃለን፣ እንማጸናለን፣ እናሳስባለንም!!!
ይሄንን የውሳኔ ሐሳብ እዚህ ደረጃ ከደረሰ በኋላም በሕግ መወሰኛው ምክር ቤቱ ወይም በፕሬዚዳንቱ (በሊቀ ሥልጣናቱ) ውድቅ የምታደርጉትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መጫወታቹህን የምትቀጥሉ ከሆነ ግን ከዚህ በኋላ የፈለገ ነገር ቢፈጠር፣ ወያኔ ከእስከዛሬው እጅግ የከፋ ምንም ዓይነት አረመኔያዊ ግፍ ቢፈጽምብንም እንኳ ፍርዱን ለእግዚአብሔር እና ለታሪክ እንተዋለን እንጅ ከአሜሪካ መንግሥት ደጅ ፍትሕ ይገኛል ብለን ምንም ዓይነት የውሳኔ ሐሳብ ፈጽሞ የማናቀርብ መሆናችንንና በተለመደው የአስመሳይነት ተግባራቹህ ለማስመሰል ብላቹህ እናንተው ቀጥራቹህ ወይም ገፋፍታቹህ የሆኑ ሰዎች የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርቡ አድርጋቹህ ለምታንቀሳቅሱት የውሳኔ ሐሳብ ምንም ዓይነት ድጋፍና ትኩረት ፈጽሞ የማንሰጥ መሆናችንን ለመጨረሻ ጊዜ አጥብቀን እናሳስባለን!!! የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉልበቱ እግዚአብሔር ነውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ካልቆማቹህ ትወድቃላቹህ!!! አትጠራጠሩ አመናቹህም አላመናቹህ ትወድቃላቹህ!!! ለዚህም ታሪክ፣ እውነትና ፍትሕ ምስክር ይሆናሉ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው