>

አሁንስ ፍትህ አገኝ ይሆን? (ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር የላኩት ደብዳቤ) - በጌታቸው ሽፈራው

አሁንስ ፍትህ አገኝ ይሆን?
(ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ የላኩት ደብዳቤ)
~”ዐቃቤ ህግ ባቀረበው አቤቱታ ጉዳዩን የማየት እንኳን ምክንያት ሳይኖረው የሰበር ሰሚ ችሎት ያለምንም ክርክር “አብረው የተከሰሱት ፍርድ ሳያገኙ ነፃ ማለት የማይቻል ነው” በማለት የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፀናው፡፡ ይህ ለእኔ አሳዛኝ እና አስገራሚ ለህግ ባለሙያዎች እፁብ ድንቅ በሚያሰኝ የሰበር ሰሚ ችሎትን ውሳኔ ለህሊና ፍርድና ለታሪክ እተወዋለሁ፡፡”
~”38 ተከሳሾች በፖሊስ ምርመራ ጊዜ ጥፍራቸው እየተነቃቀለ ጣታቸው እየተሰበረ በሚስማር እየተወገ በካቴና የተሰቀሉበት ጠባሳ እንዳገኘ አረጋግጦ የኢፌድሪ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ አጣርቶ መልስ ሰጥቷል።”
~ለምስክርነት የቀረቡት እስረኞችም በሃሰት እንዲመሰክሩ ከተከሳሾቹ በማያንስ የጭካኔ ቶርቸር እንዲሁም የማታለያ የትፈታላችሁ ቃል ተገብቶላቸው እንደሆነ ምስክሮችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል።” ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ
አሁንስ ፍትህ አገኝ ይሆን?
ለክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ
የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስተር
ከብዙ ወራቶች በፊት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይላሪያም ደሳለኝ አፋጣኝ ፍትህ እንዲሰጡኝ የአቤቱታ ደብዳቤ አቅርቤ እስካሁን መልስ ባለማግኘቴ ምናልባትም ከእርስዎ ላገኝ እችላለሁ የሚል ተስፋ አንግቤ ሌላ የማደርስበት አማራጭ መንገድ በማጣቴ በዚህ አይነት መልክ ለማሳወቅ ተገድጃለሁ፡፡
ሀ. ስለ እኔ የክስ ጉዳዮች ዝርዝርና ጠለቅ ያለ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ያስተላለፍኩትን ደብዳቤ አባሪ አድርጌያለሁ፡፡
ለ. የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ማእረግና ኃላፊነት ከወሰዱ ጥቂት ቀኖች መቆጠራቸው ግልፅ ነው፡፡ የተረከቡት የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ውስብስብ እና ከባድ፣ አንገብጋቢ እና አስቸኳይ መፍትሄ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠንቅቄ እገነዘባለሁ፡፡
ሐ. የእኔ የአንድ ግለሰብ ከሌሎች በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች ለእኔ ቅድሚያ እንዲሰጡኝ ሳይሆን የእኔ ጉዳይ የሚሊዮኖች የሚሊዮኖችም ጉዳይ የእኔ ጉዳይባጭሩ የፍትህ ጉዳይ መሆኑን በማመን
መ. ላለፉት አምስት አመታት እኔ በእስር ቤት በማቆየት ከሃያ በላይ እኔን ተማምነው ሕክምና ያደረኩላቸው ኢትዮጵያውያን የልብ ህሙማን ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ አሁንም መታማቸውና መሰቃየታቸው እየቀጠለ በመሆኑ የአንድ ኢትዮጵያዊ ህይወት ዋጋ የማይወጣለት ክቡር ነገርና መዳን ከስቃይ መታደግ ቢቻልም አለማድረጉ ሰብአዊነት የጎደለው እንደሆነ አምናለሁ፡፡ እርስዎም ቢሆኑ የእኔን አቋም እንደሚካፈሉ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ለመሪነትዎ ለተሸከሙት ኃላፊነት ድምር እሴት እና መርህ እንደሆነ ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ሠ. ባጭሩ ከላይ የጠቀስኳቸው ግብአቶች አፋጣኝ ፍትህ እና መፍትሄ ለመስጠት እንደሚስችሎት ተስፋ አለኝ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር
የቤተሰቦቼ የጓደኞቼ እና የአያሌ የሚያውቁኝም የማያውቁኝም ሰዎች የእንቆቅልሽ መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች እርስዎንም ለደቂቃም ቢሆን እንዲያስቡ፣ እንዲጠይቁ ያደርግዎታል ብዬ ስላሰብኩ አጠር እና ጠቅለል ያለ ገለፃ ሳደርግ እንደድፍረት እንዳይቆጥሩብኝ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ከአምስት አመት በፊት በነ አቶ መላኩ ፈንታ መዝገብ ላይ በሙስና ወንጅ ተከስሼ የፍርድ ቤት ሂደቱ እየተጓተተ ከሶስት አመት በላይ ካስቆጠረ በኋላ በደረሰብኝ አደገኛ በሽታ በህይወት መኖር ያለመኖሬ ከፍተኛ ጥያቄ በሆነበት ወቅት የከፍተኛው ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በተኛሁበት ሆስፒታል ክፍል ድረስ መጥተው በመሰየም ያለምንም ማስረጃ በሰሚ ሰሚ እንደምስክርነት በመመርኮዝ የአራት አመት ከስምንት ወር ፍርድ ተሰጠኝ፡፡
ከህመሜ አገግሜ ይግባኝ ጠይቄ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ክሱን የቀረበውን የምስክርነት “ማስረጃ” ከመረመረ በኋላ እንኳንስ ጥፋተኛ ብሎ ሊያስፈርድ ይቅርና ለማስከሰስ እንኳን የማይችል በሚመስል መልክ ሙሉ በሙሉ ነፃ አደረገኝ፡፡
አቃቤ ህግ ባቀረበው አቤቱታ ጉዳዩን የማየት እንኳን ምክንያት ሳይኖረው የሰበር ሰሚ ችሎት ያለምንም ክርክር “አብረው የተከሰሱት ፍርድ ሳያገኙ ነፃ ማለት የማይቻል ነው” በማለት የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፀናው፡፡ ይህ ለእኔ አሳዛኝ እና አስገራሚ ለህግ ባለሙያዎች እፁብ ድንቅ በሚያሰኝ የሰበር ሰሚ ችሎትን ውሳኔ ለህሊና ፍርድና ለታሪክ እተወዋለሁ፡፡
አሁን ደግሞ በሌለሁበት ማመን በማያስችል ሁኔታ “ገንዘብ ሰጥቶ የግንቦት 7 አባሎች በማደራጀት ማረሚያ ቤት አቃጥሏል” በሚል ክስ ቀርቦብኝ የአቃቤ ህግ የምስክር ብይን በመጠባበቅ ላይ ነኝ፡፡
ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በጠየቀው መሰረት ቢያንስ ከ38 ተከሳሾች በፖሊስ ምርመራ ጊዜ ጥፍራቸው እየተነቃቀለ ጣታቸው እየተሰበረ በሚስማር እየተወገ በካቴና የተሰቀሉበት ጠባሳ እንዳገኘ አረጋግጦ የኢፌድሪ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ አጣርቶ መልስ ሰጥቷል፡፡
ለምስክርነት የቀረቡት እስረኞችም በሃሰት እንዲመሰክሩ ከተከሳሾቹ በማያንስ የጭካኔ ቶርቸር እንዲሁም የማታለያ የትፈታላችሁ ቃል ተገብቶላቸው እንደሆነ ምስክሮችን ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡
የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው ማረጋገጫ ግዙፍ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የተዛባ የፍርድ ሂደት እንደሆነ ለትክክለኛ ፍትህ ክሱ ተቋርጦ ተከሳሾች በነፃ መለቀቅ ይገባቸው ነበር፡፡ሆኖም….
ከላይ ያስቀመጥኩትን ካልኩ በኋላ ወደ እንቆቅልሽ ጥያቄዎች ስገባ እንዲህ አይነት በሃሰት በተቀነባበረ የውሸት ክስ ታስረው ዶ/ር ፍቅሩ የሚሰቃዩት “እነኚህ ሰዎች ምን ፈልገው ነው? መሆኑ ምን አደረኳቸው? ከሳቸውስ የሚፈልጉት ነገር ይኖር ይሆን ወይ?”በሚል ያብሰለስሉታል፡፡
በእኔ በኩል ግልፅ ላደርገው የምፈልገው የቀረኝን እድሜ በእስር ቤት ባሳልፍም ባለሁበት ሁኔታ ህይወቴ እዚሁ ቢያልፍም ስብእናዬን የማይገልፅ የኑሮ መርህዬን የማይፈቅደውን ከእስር ቤት ለመውጣት ስል እንደማላደርገው ነው፡፡
እርስዎም ሆኑ ሌሎች በአፅኖት እንዲገነዘቡልኝ የምፈልገው በንግግርዎ እንደገለፁት እስካሁን የኖርኩትን ወደፊትም የምኖረው እንደ ኢትዮጵያዊ ስሞትም እንደ ኢትዮጵያን ከገነቧት ወደፊትም ከሚያቆዩዋት እንደምደባለቅ ነው፡፡
ፍትህ ብልፅግናና ነፃነት
ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት
ከከበረ ሰላምታ ጋር
ፍቅሩ ማሩ
ከቂሊንጦ እስር ቤት
ግልባጭ:_
ሀ) ለስውይድን ጠቅላይ ሚኒስቴር
ለ) ለስውይድን ኤምባሲ
ሐ) ለኢፌዲሪ ፍትህ ሚኒስቴር
መ) ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ
ሠ)ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን
Filed in: Amharic