>

አዳራሹ ቤቴ - ዘ ኢትዮጵያ! ደረጄ ደስታ

አዳራሹ ቤቴ ግሩም ነው። ከአፍሪካ አንደኛ ነው ተብሏል። ህንጻውም ዓላማውም ድንቅ ነው። ከ35ሺ ሰው በላይ ይይዛል። ለበዓል ለስብሰባ ለጸሎት ለቴአትር ለኦርኬስትራ ለዳንኪራ እንዲሆን አምሮ የተሰራ ነው። የቅርብ ቀንና የወቅቱን ዝግጅቶች በትላልቅ እሚያሳዩ ግዙፍ ስክሪኖች በየግድግዳው ተደርገዋል። ዓለም ፀሀይ ወዳጆ ከእነጌትነት እንየው ጋር በመሪነት እምትጫወትበት “ቀዳማይ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ዝነኛው ቴአትር ማስታወቂያ በአዳራሹ ስክሪን ጎልቶ ይታያል። ቴዲ አፍሮም “ሆይ በይ አገሬ!” እሚለውን አዲስና ተወዳጅ ዜማውን ይጫወታል። ከአዳራሹ መግቢያ በስተቀኝ ይቅርታ የተባለው ማዕከል መግቢያ ይታያል። ማዕከሉ እስካዛሬ በተገደሉና በታሰሩ ሰዎች ስምና ፎቶግራፍ ዝርዝር ኢግዚብሽን ተሞልቷል። ከግፉና ከተጠቂው ብዛት ለምን በአንድ ስሙ የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ዝርዝርና ፎቶግራፍ አይለጠፍም ያሰኛል። በእርስ በርስ ጦርነት የተላላቁ ኢትዮጵያውያንና ጦርነቶቹን የሚያሳይ “በከንቱ!” የተሰኘው ሙዚያምም ከአዳራሹ ሶስተኛ ፎቅ ይገኛል። “አገር እንደገና” የተባለው የኪነጥበብና የባህል ማዕከልም እሚገኘው እዚያው ሶስተኛው ፎቅ ላይ ነው። ከድሮዎቹ ከነዮፍታሄ በፊት ከነበሩት አንስቶ እንደ በዕውቀቱ ስዩም እስከመሳሰሉት ወጣት ገጣሚያን ድረስ ያሉት ግጥሞች በየመስታውቱ ስክሪን ውስጥ ሆነው ይታያሉ። “ባላገሩ ሳይንስ” የተባለው አገር በቀልና ዓለም አቀፉን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያጣመረው የኤግዚብሽን ማዕከልም ሌላኛው ነው። የነተፈራ ዋልዋ የህዋ ምርምር እዚህ ውስጥ ተካቷል። አራተኛ ፎቅ ላይ “ጉሊት” ከተባለው ሌላኛው የግሎባላይዜሽንና የንግድ ማዕክል ጋር ጎን ለጎን ይገኛል። የተለያዩ ዘርፎች የተካተቱባቸው ማዕከሎቹ እስከ ስደተኛ ፎቅ ድረስ ወደላይ ይገኛሉ፡፡ የዛሬውን በዓለ ሲመት ዝግጅት እሚቀርብበት ግን ከአንደኛው ፎቅ ላይ የሚገኘው አዳራሹ ቤቴ የተሰኘው ትልቁ አዳራሽ ነው። የተለያዩ ዝግጅቶች ተሰናድተዋል።
ታዳጊ ህጻን ናፍቆት እስክንድር ነጋና የእነ አንዱ ዓለም ልጆች የአበባ እቅፍ ይዘው ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመስጠት እየተጠባበቁ ነው። እንግዶች ግን ቦታቸውን ባይዙም ከአዳራሹ ገብተው በየጥጉ በመሆን የየራሳቸውን ወግ ይዘዋል።
አንዳርጋቸው ጽጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዱ አለም፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ፣ ሜጀር ጀነራል ተፈራ ማሞ፣ ፣ ጀነራል አሳምነው ጽጌ፣ የዋልድባ መነኮሳት እንዲሁም ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ሼህ መከተ ሙሄ እና ኡስታዝ ካሚልን አቶ ማሙሸት አማረ፣አቶ ናትናኤል መኮንንና፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ጨምሮ ለበርካታ እሰረኞች ብቻ መቀመጫ ሆኖ በክብር የተከለለው ቦታ እየሞላ ነው። ከእለቱ የክብር ተናጋሪዎችም አብዛኞቹ ከእነዚህ የተወከሉ ናቸው። የአዘጋጅ ኮሚቴዎቹ አባላት ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ትዝታ በላቸው፣ ሀብታሙ አያሌው፣ ገብሩ አስራት፣ አበበ ባልቻ፣ ከባዱ በላቸው፣ ፓስተር ዳንኤል፣ ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ፣ ኤምርያስ ለገሠ፣ ረድዋን ሁሴን፣ ግዛው ለገሠ፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ይገኙበታል። ከመድረኩ ጀርባም ብዙ አርቲስቶች ለሙዚቃ ሥራ ተዘጋጅተዋል ከአንጋፋዎቹ እነ አለማየሁ እሸቴ አስቴር አወቀ ሻምበል በላይነህ ኤፍሬም ታምሩ ነዋይ ደበበ ላንፎንቴዎች ፀሐዬ ዮሐንስ መሀሙድ አህመድ ፣ ዓሊ ቢራ ፣ ሰለሞን ተካልኝ፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ጸጋዬ እሸቱ…. ብዙ ናቸው።
በአግዓዚ ኮማንዶዎች እየታገዙ፣ የዲሲ ግብረኃይል አባላት፣ ቄሮና የአማራው ፋኖዎች፣ ከአዳራሹ በር ያለውን ሥርዓትና ጸጥታ ያስከበራሉ።
ታማኝ በየነ ከመደረኩ ላይ ነው። እባካችሁ እንግዶች እየተቃረቡ በመሆናቸውና ፕሮግራማችንንም ልንጅምር ስለሆነ ወንበሮቻችሁን ያዙ። ወንበር ደግሞ ስላችሁ ሥልጣን እንዳይመስላችሁ…ሲል ሰው ሁሉ ሳቀ!
የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ጅዋር መሃመድ ፣ ወደ ታማኝ መጣና የሆነ ነገር በጆሮው ነገረው። “አንድ ጊዜ እባካችሁ!” አለ ታማኝ እንደገና “ አሁን የቀድሞው የኤርትራው ፕሪዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወቂ ወደ አዳራሹ እየገቡ ስለሆነ ብሎ ሊቀጥል ሲል… አሁንም ጅዋር ሮጠው በመምጣት አቋረጠው። ማረሚያውን ተናገረ። “አይ የኔ ነገር በሉ ይቅርታ ሰውየው ለካ እዚሁ እኛው መካከል ነበሩ። እሳቸው አጀብና ግርግር ሰለማይወዱ ከተቀላቀሉን ቆይተዋል። በዚህ አጋጣሚ እንኳን በመካከላችን ተገኙ ሲል ስለ እንግዳው ተናገረ። ቀደም ሲል የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪ ፕሬዜዳንት መንግሥቱ ኃ/ማያርምን ወደ አዳራሹ ሲገቡ አስተዋውቆ ነበር። አሁን እየገቡ ያሉት “የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ” መሆናቸው እንዲስተካከል ሲል ጠየቀ። ሰው በያለበት ሆኖ እያፏጨ አጨበጨበ። እንዴ ዘንድሮም ታጨበጭባላችሁ እንዴ አለ የመድረኩ መሪ!
ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፈዋል የተባሉትን የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር መምጣት እየተጠበቀ ነው። አዳራሹ ቤቴ በፖለቲካ ድርጅት አባላት አክቲቪስቶች ጋዜጠኞችና በሌሎችም የሙያ እና የህዝብ ተወካዮች ተሞልቷል። አንዳንዶች ከ15 ሺ ሰው በላይ ነው ይላሉ። ሰው ባልተለመደ ሁኔታ ከዝግጅቱ ሰዓት ቀድሞ ስለመጣ የኮክቴል ጨዋታውና ትውውቁ የደራ መስሏል። አዳራሹን ጭምር ላሰሩት፣ እድሜ ለአላሙዲ! ሰውዬው ከመሞቴ በፊት ይህን አይቼ ልሙት ይሉ ነበር ይባላል። እነ አቶ አብነት ድግሱን መሟላቱን እየዞሩ ይከታተላሉ።
ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የኢህአፓዎቹ ኢያሱ ዓለማየሁና መርሻ ዮሴፍ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ልዑል ኤርምያስ፣ በየነ ጴጥሮስ፣ ስብሀት ነጋ የኦነጉ ገለሳ ዲልቦና ሁለት እማላውቃቸው ሰዎች ጋር ሆነው ክብ ሠርተው እየተሳሳቁ ያወራሉ። በዚህ ጊዜ የቀድሞ የደህንነት ሚኒስትሩ ጌታቸው አሰፋ መጥተው ተቀላቀሉ። ይህን ያዩት ኢህአፓው ኢያሱ ይሄን ሰላይ ከዚህ አባሩልኝ እኔ ሰላይ አልወድም ሲል ሁሉም ሳቁ። ባክህ አትለፍልፍ ካሁን በኋላ እሚገድልህ የለም ይልቅ መድሃኒትህን የኛ ልጆች ከፋርማሲ አግኝተውልሃል አሁን መዋጥ ካለብህ ብዬ ነው። ውይ ውይ አዎ ስንት ሰዓት ሆኗል? እዚህኮ ወሬ ይዤ ጨርሶ ረስቼዋለሁ። ከመንጌ የተረፈች ህይወቴን ሆሆ…ሲል ሁሉም ሳቁ። ጌታቸውን ተክትለው መድሃኒቱን ለመዋጥ ሊሄዱ ሲነሱ ፕሮፌሰር መስፍን መጡ። እንዴ እኔ ስመጣ ነው እናንተ እምትሄዱት አሏቸው። አይ አይ መስፍንስ ከመጣ እኔም እሄዳለሁ አሉ ኮ/ል መንግሥቱ መስፍንን በነገር ለመንካት። ምን ከኔ ብትሸሽ እዚህ አዳራሽ ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ አይለቅህም አሉ ፕሮፈሰር መስፍን በቀልድ። አሁንም ሳቅ ሆነ። ወዲያው አስከትለው እኔ እምልህ ውባንቺ መጥታለች እንዴ አላየኋትም አሉ። የመንግሥቱን ባለቤት ማለታቸው ነው። እኔ እንጃ ቅድም እዚያ አካባቢ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ነበረች። ዋይይ ቀዳማይ እመቤቶች መፈላለጋቸው ነው ብለው ስብሐት ነጋ አሽሟጠጡ። ኢሳያስ አፈወርቂ አንተ ደግሞ በቃ ይቺን ሴት አለቃትም ብለሃል አይደል አሉ በነገር ሲነኳቸው። ስብሐት ያልገባቸው መስለው ኮ/ል መንግሥቱ ጀምረውት ወደነበረው ጨዋታ እንዲመለሱ አስታወሷቸው። ስለ ሩሲያ ሲወራ ጨዋታቸው ደርቶ ከፕሬዚዳንት ብሬዥነቭ አድርሷቸው ነበር።
ከወዲያ ጥግ የቀድሞው ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሳሞራ እና ብርሃኑ ነጋ አፍ ለአፍ ገጥመው ያወራሉ። ለማ መገርሳ መጥተው መቀላቀል ይቻላል? አሉ። አሁንማ እናንተ አገሩን ቀላቅላችሁት ማን ይከለክላችኋል አሉ ሳሞራ። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ለማ እየተቃቀፉ ሳቁ። ገዱ አንዳርጋቸው፣  የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ፍቅረሥላሴ ወግደረስ በየተራ እየመጡ ተቀላቀሏቸው። ስዬ አብርሃንና ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስንም፣ ከሩቅ ያየኋቸው መሰለኝ። የሞረሽ አማራው ተክሌ የሻውና አባዱላ ገመዳ ምን እንደሚያስቃቸው እንጃ እየተሳሳቁ መጥተው ተጨመሩ።
ከላይ ከጋዜጠኞቹ ማማ ደግሞ በቀልድና የተረብ ጨዋታው እሚታወቀው አማረ አረጋዊን ከበው ጋዜጠኞቹ እነ ፋሲል የኔዓለም፣ ሚሚ ስብሐቱ፣ ሲሳይ አጌና፣ ዳንኤል ብርሃነና፣ አበበ ገላው፣  ታምራት ገ/ጊዮርጊስ፣ አብይ ኃይሉ፣ የፋናው ወልዱ ይመስል፣ መዓዛ ብሩ፣ መስፍን ነጋሽ ፣ መሳይ መኮንን፣ ኤልያስ ክፍሌ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ሔኖክ ዓለማየሁ ተስፋዬ ገ/አብን ጨምሮ የቪኦ.ኤ. የጀርመን የፋና ፣የኢሳትና የኦ ኤም ኤን ጋዜጠኞች እየተሳሳቁ ያወራሉ። ክንፉ አሰፋ ሁለቱ ዳዊት ከበደዎችና አብርሃም በላይ ተቀላቅለዋል። የኢቲቪ፣ ኢትዮቱብ፣ ዘሀበሻ፣ አባይ ሚዲያ ህብረት ሬድዮና የመሳሰሉ ጋዜጠኞችም ፕሮግራሙን በዌብሳይት በቀጥታ እያስተላለፉ ነው።
የኮ/ል መንግስቱ ባለቤት ወ/ሮ ውባንቺ፣ ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬና ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ አንድ ስድስት እሚሆኑ ሴቶችም ሰብሰብ ብለው ያወራሉ። ሁሉም በአገር ልብሳቸው ዘንጠዋል። በአጠገባቸው እያለፈች የነበረችው ብርቱካን ሚደቅሳ ውይይ ሁላችሁም በጣም ታምራላችሁ እያለች ሰላምታ አቀረበች። ወ/ሮ ውባንቺ በተለይ አቤት ይቺን ልጅ ስወዳት ነይ እስቲ የኔ ቆንጆ ብለው አቅፈው ሳሟት። ጸጉርሽ ደግሞ በጣም ያምራል አሏት። እሷማ እምቢ ብላ እኔ ነኝ በስንት መከራ ማታ ወስጄ ያሰራኋት አሉ ወ/ሮ አዜብ። ከሁሉም በእድሜ ስላነሰች ነው መሰል ሁሉም በፍቅር ዓይን አይዋት። ሰዎች ወደፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ልትሆን ትችላለች አሁንም ለፍትሕ ሚኒስትርነት ታጭታለች እያሉ ያወራሉ።
ዶ/ር መረራ፣ ስዩም መስፍን፣ ኮ/ል ጎሹ ወልዴ፣ ክፍሉ ታደሰ፣ በረከት ስምዖን፣ የኢህአፓው ፋሲካ በለጠ፣ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ፣ የመኢሶኑ ነገደ ጎበዜ፣ ሌንጮ ለታ፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ልደቱ አያሌው፣ አርከበ እቁባይ፣ ያሬድ ጥበቡ ፣ ብርሃነ ገ/ክርስቶስ፣ ነዓምን ዘለቀ፣ አርክበ እቁባይ፣ ዶ/ር ካሳ ከበደ፣ የቀ/ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ፣ ኦባንግ ሜቶ ጄኔራል ጻድቃን፣  አጅብ ብለው በነገደ ጎበዜ ባቀረቡት ሀሳብ ይከራከራሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ቴሌቪዥን እየተከታተለው ነው። ደሬም ከአዳራሹ ጥግ ተቀምጣ እሚሆነውን ሁሉ ታያለች።
…እንዲህ እያልኩ ገና ባዳራሹ ያሉ ብዙ ስሞችን ዘርዝሬ፣ ስለ አዲሱ ጠቅላይ ምኒስትር ማንነት ልንገራችሁ ስል…ነቃሁ። ፍርሃት አነቃኝ።  አሁን ይህን ቅዠት ቢሰማ አገር ምን ይላል ብዬ ፈራሁ። ፈሪ ለናቱ! አልኩና፣ ለእናት ኢትዮጵያ መኖሬን ቀጠልኩ። ሁሉንም ማስደስት እሚፈልግ ሁሉንም ያጣል – እያልኩ፣ ካንዱ ተደርቤ ሌላውን ለመንቀፍ ወደ ሚያስገድደኝ ማህበረሰቤ ተመለስኩ። ከእነዚህ አንዱን መርጦ ያልቆመ፣ አቋም የሌለው እየተባለ ወደሚወገዝበት፣ ቡድን ቡድኑን ወደ እሚያጀግንበት፣ ወንድም ወንድሙን ወደ እሚዘልፍበት፣ አንድነት ከሌላው ጋር ሳይሆን ብቸኝነት ወይም የአንድ እኔ ብቻነት ወደ ሆነበት፣ ስቀለው ውገረው ወደሞላበት፣ ማሸነፍ ብቻ ወደሚቀነቀንበት፣ የኦሮሞ፣ አማራና ትግሬን ጥሎ ማለፍ፣ እውቀት አስመስሎ ለመለፍለፍ ወደሚያስገድደኝ ሌላኛው የህይወትና የእውነት አዳራሽ ተመለስኩ። አዳራሹ ቤቴ!
(በሚሊኒየሙ ለፍቅር እንበድ! በሚል ርዕስ በ2009 ልክ እንዲህ ያለ ህልም በዘኢትዮጵያ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ተጽፎ ነበር።)
Filed in: Amharic